እስከ 100 ቢሊዮን ዶላር የሚገመተው የኢራን የታገደ ሀብት የት ነው ያለው?

የእስላማዊ ኢራን መንግሥት መሥራች አያቶላህ ሩሃለህ ኻሜኒ ከጀርባቸው የተለያየ ቀለም ለቸላው ኮንቴነር የጫነ መርከብ በባሕር ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

የታገዱ የኢራን ሀብቶችን የማስለቀቅ ጉዳይ በኢራን እና በምዕራቡ ዓለም ግንኙነት ውስጥ እጅግ አከራካሪ እና ውስብስብ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ነው።

የካቲት ላይ የተነሳውን ጦርነት ለማስቆም ባለመው እና ከአሜሪካ ጋር በተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ውስጥም ቁልፍ ጉዳይ ሆኖ ሰፍሯል።

ቴህራን በማዕቀብ እና ባንኮች ላይ በተጣለው ገደብ ምክንያት ልታንቀሳቅሰው ያልቻለችውን ሀብቷን ለማስለቀቅ ለረጅም ጊዜ ስትሞክር ቆይታለች።

ምንም እንኳ አብዛኛው ሀብት የተያዘው በአሜሪካ ባይሆንም፤ የማስለቀቁ ጉዳይ ላይ የዋሽንግተን ሚና ግን ወሳኝ ነው።

ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ከዚህ ገንዘብ ውስጥ መለቀቁ፤ ለዓመታት በማዕቀቦች፣ በኢኮኖሚ መገለል፣ በከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እና በገንዘብ ዋጋ መውረድ ለተጎዳው የኢራን ምጣኔ ሀብት ወሳኝ ይሆናል።

ከየካቲት አንስቶ በአሜሪካ እና በእስራኤል የተከፈተባት ጦርነትም ኢኮኖሚውን ይበልጥ ጫና ውስጥ ከትቶታል።

ይሁን እንጂ በዕግድ ላይ ባለው የኢራን ሀብት ጉዳይ ባለበት የሕግ፣ የፋይናንስ እንዲሁም ፖለቲካዊ እንቅፋቶች የተነሳ ገንዘቧን ለማስለቀቅ የተፈረመው ስምምነት ወደ ተግባር ለማውረድ ጊዜ የሚወስድ እና ውስብስብ ሂደት መሆኑ አይቀርም።

እነዚህ ሀብቶች በትክክል ምንድናቸው? የኢራንስ ምን ያህል በቀላሉ ልታገኘው ትችላለች?

የሀብቶቹ ዝርዝር ምንድነው?

ከነዳጅ ማጣሪያ ፊት ለፊት የሚውለበለብ የኢራን ባንዲራ

የፎቶው ባለመብት, Bloomberg via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የታገደው የኢራን ሀብት የነዳጅ ሽያጭ ገቢዎችን እንዲሁም የነዳጅ፣ ጋዝ እና ኤሌክትሪክ ኤክስፖርት ገንዘብን ያካትታል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እስካሁን ድረስ የታገደውን የኢራን ሀብት አጠቃላይ ዋጋ የሚገልጽ ይፋዊ ቁጥር የለም። ነገር ግን ከ27 እስከ ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

ሀብቱ የሚገኘው በአንድ፣ ማንቀሳቀስ በሚቻል አካውንት ውስጥ አይደለም። የኢራን ሀብት ሲባል የነዳጅ ሽያጭ ገቢዎችን እንዲሁም የነዳጅ፣ የጋዝ እና የኤሌክትሪክ ኤክስፖርት ገንዘብን ያካትታል።

በዚህ ውስጥ በውጭ አገር ባንኮች ውስጥ የሚገኙ የኢራን የውጭ ምንዛሬ ክምችቶች እንዲሁም በሕግ ክርክሮች ምክንያት የተያዙ ሀብቶች እዚህ ውስጥ ይጠቃለላሉ።

ኢራን በውጭ አገር ከሸጠችው ነዳጅ የሚሰበሰበው ክፍያ በአብዛኛው የሚቀመጠው በገዢው አገር ውስጥ ባሉ የባንክ ሂሳቦች ነው። ቴህራን ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች ግን የአገሪቱ መንግሥት በሽያጭ ያገኘውን ገቢ እንዳያንቀሳቅስ አግዶታል።

ለመጀመሪያ ጊዜ የኢራን ሀብቶች የታገዱት በአውሮፓውያኑ 1979 በቴህራን ይገኝ የነበረው አሜሪካ ኤምባሲ ሠራተኞች በታገቱበት ወቅት ነው። ኋላ ላይ በተደረጉ ስምምነቶች አማካኝነት የተወሰኑ ሀብቶች ቢለቀቁም፤ በ1979 የእስላማዊ አብዮት ከመፈንዳቱ በፊት ከተገቡ ወታደራዊ ውሎች ጋር የተያያዙ አንዳንድ ገንዘቦች እስካሁን እንደተያዙ ናቸው።

ኢራን ላይ ጥብቅ የኒውክሌር ማዕቀቦች በተጣሉበት እና ከዓለም አቀፉ የባንክ ሥርዓት እንድትገለል በተደረገበት ከአውሮፓውያኑ 2011 እስከ 2012 ባለው ጊዜ ውስጥ ደግሞ ሁለተኛው ዙር መጠነ ሰፊው የሀብት ዕገዳ ተግባራዊ ሆኗል።

የትራምፕ አስተዳደር 2018 ላይ አሜሪካን በ2015 ከተፈረመው የኒውክሌር ስምምነት ካስወጣ በኋላ ዕገዳዎቹ ይበልጥ ጠብቀዋል።

የሚጣለው ገደብ እየሰፋ ሲመጣ፤ በውጭ አገር ተይዞ ያለው ገቢ መጠንም ጨምሯል። ከዚህ ገንዘብ ውስጥ የተወሰነው ይፋዊ ዕገድ የተጣለበት ሲሆን፣ የተወሰነው ደግሞ ጥቅም ላይ የሚውልበት መንገደን በተመለከተ ገደብ ተቀምጦበታል።

በመካከለኛው ምሥራቅ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ምክር ቤት የኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት ፍሬደሪክ ሽናይደር እንደሚናገሩት ኢራን ላይ የተጣሉ "የተለያዩ የዕገዳ ዓይነቶች" አሉ። ባለሙያው፤ በይፋ የታገዱ፣ ወደ ኢራን ሊመለሱ የማይችሉ ገቢዎች እንዲሁም በፍርድ ቤት ክርክሮች ምክንያት የተያዙ ገንዘቦች ሲሉ ይገልጿቸዋል።

የተያዘው ገንዘቡ የት ነው?

የኢራን ገንዘብ የሚገኝባቸውን አገራት የሚያሳይ ካርታ

አብዛኞቹ የታገዱ ኢራን ሀብቶች የሚገኙት ከአሜሪካ ውጪ ነው።

የኢራን ነዳጅ ዋነኛ ሸማች የሆነችው ቻይና ከፍተኛውን ድርሻ ትይዛለች። ቻይና ውስጥ የሚገኘው የኢራን ገንዘብ ከ20 እስከ 50 ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን ይገመታል።

ኢራቅ ሌላኛው ትልቅ መጠን ያለው የኢራን ገንዘብ የሚገኝባት አገር ነች። በጋዝ እና በኤሌክትሪክ የወጪ ንግድ ምክንያት ኢራቅ ውስጥ የተቀመጠው የቴህራን ገንዘብ ከ10 እስከ 15 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ ይችላል።

ደቡብ ኮሪያ ይዛ የነበረው ስድስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ የኢራንን የነዳጅ ገቢ በ2023 በኳታር ወደሚገኙ ሂሳቦች እንዲተለላፍ መደረጉን የአሜሪካ ኮንግረስ መረጃ ያሳያል።

ይሁን እንጂ ቴህራን ይህንንም ገንዘብ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ማግኘት እንደማትችል አሜሪካ ገልጻለች። ይህም ገንዘቡ ኳታር ውስጥ እንዲቀመጥ አድርጎታል።

ሕንድ፣ ጃፓን እና ሉክሰምቡርግን ጨምሮ በተለያዩ አገራት ውስጥም የኢራን ሀብት ተቀምጧል።

ከሌሎቹ ጋር ሲነጻጸር አሜሪካ ውስጥ የተያዘው ገንዘብ አነስተኛ ነው። በአሜሪካ ኮንግረስ መረጃ መሠረት ዋሽንግተን ውስጥ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ገደማ የኢራን ሀብት ይገኛል።

ከዚህ ገንዘብ ውስጥ አብዛኛው በፍርድ ቤት ውሳኔ እና በካሳ ክፍያ ምክንያት የተያዘ በመሆኑ ይህንን ገንዘብ የመልቀቅ ጉዳይ ቀላል አይሆንም።

አሜሪካ ያላት ሚና ምንድነው?

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አብዛኛው ሀብት የሚገኘው ከአሜሪካ ውጪ ቢሆንም፤ ዋሽንግተን በጣለቻቸው 'የሁለተኛ ደረጃ ማዕቀቦች' ምክንያት ከፍተኛ ተጽዕኖ አላት

አብዛኛው ሀብት የሚገኘው ከአሜሪካ ውጭ ቢሆንም፤ ዋሽንግተን በጣለቻቸው 'የሁለተኛ ደረጃ ማዕቀቦች' ምክንያት ከፍተኛ ተጽዕኖ አላት።

አሜሪካ የጣለቻቸው ማዕቀቦች ዒላማ ያደረጉት ኢራንን ብቻ ሳይሆን ከእርሷ ጋር የንግድ ልውውጥ የሚያደርጉ የውጭ አገር ባንኮች፣ ኩባንያዎች እና መንግሥታትንም ጭምር ነው።

ኢራን ገንዘቧን እንድታንቀሳቅስ እገዛ ያደረገ የትኛውም ተቋም ከአሜሪካ የፋይናን ሥርዓት ይታገዳል ወይም ቅጣት ይጣልበታል።

በዚህም የተነሳ የኢራንን ገንዘብ የያዙ አገራት ብዙውን ጊዜ ያለ አሜሪካ ግልጽ ፈቃድ ሀብቱን ለመልቀቅ ወይም ለማስተላለፍ ያመነታሉ።

ኢራን ከስምምነቱ ምን ልታገኝ ትችላለች?

ከአሜሪካ ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ኢራን ኢኮኖሚያዊ እፎይታ ልታገኝ የምትችልባቸውን ሁለት መንገዶች አስቀምጧል።

  • የኢራን ነዳጅ እና የፔትሮሊየም ምርቶችን ለውጭ ገበያ እንድታቀርብ እንዲሁም እንደ የባሕር ጉዞ፣ ኢንሹራንስ እና የባንክ አገልግሎት ያሉ ተያያዥ አገልግሎቶችን እንድትሰጥ የሚያስችል የማዕቀብ ማላላት እርምጃ
  • የታገዱ ገንዘቦችን ማግኘት እና የኢራን ማዕከላዊ ባንክ ገንዘቡ በሚውልበት መንገድ ላይ የበለጠ ቁጥጥር እንዲኖረው ማድረግ

በተጨማሪም ስምምነቱ ከቀጣናው አጋሮች ጋር በመተባበር የኢራንን ኢኮኖሚ መልሶ ለመገንባት እና ለማልማት የሚያስችል ቢያንስ 300 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሠፊ የመልሶ ግንባታ እንደሚካሄድ ይጠቁማል።

ለኢራን ቀጥታ ክፍያ እንደማይፈጽም በአጽንኦት የገለጸው የአሜሪካ መንግሥት፤ ይልቁንም በመሠረተ ልማት፣ በኤነርጂ፣ በትራንስፖርት እና በሌሎች ዘርፎች ላይ ኢንቨስት እንደምታደርግ አስታውቃለች።

በቴህራን ከሕንጻ የሚወጣ ጭስ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኢራን ባለሥልጣናት በጦርነቱ የደረሰው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት 300 ቢሊዮን ዶላር እንደሚገመት ይናገራሉ። የአገሪቱ ኢኮኖሚ በዚህ ዓመት በ10 በመቶ ይቀንሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል

ገንዘቡ ለኢራን ሊደርስ ይችላል?

ኢራን ገንዘቡን የማግኘት ዕድሏ አሁንም የተገደበ ሊሆን እንደሚችል ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የሚገኘው 'ቦርስ ኤንድ ባዛር ፋውንዴሽን' የባለሙያዎች ቡድን (ቲንክ ታክን) መሥራች ኤስፋንድያር ባትማንግሄሊጅ ይናገራሉ።

እንዲህ ዓይነት ስምምነቶች "ውስብስብ እንቅፋቶች" እንደሚያጋጥሟቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል። ኢራን ገንዘቡን ከተወኑ አገራት ጋር በሚኖራት ግብይት ልትጠቀምበት ብትችልም፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተላለፍ እንደሚያዳግታት አስረድተዋል።

የኢኮኖሚ ባለሙያው ፍሬደሪክ ሽናይደር በበኩላቸው ከዚህም የበለጠው ትልቁ ተግዳሮት ከኢራን ጋር የሚፈጸም ማንኛውም ስምምነት ምን ያህል ይቆያል የሚለው ላይ ያለው እርግጠኝነት ማጣት እንደሆነ ይናገራሉ።

ዋሽንግተን፤ ኢራን ላይ ከጣለቻቸው ማዕቀቦች የተወሰኑት በኮንግረስ ሕግ ሆነው ወጥተዋል። ይህም ፕሬዝዳንቱ ማዕቀቡን በጊዜያዊነት ከማላላት ባለፈው በራሳቸው ሙሉ ለሙሉ እንዳያነሱት ያግዳቸዋል።

የኢኮኖሚ ባለሙያው፤ ጊዜያዊ የማዕቀብ ማላላት እርምጃ ለምን ያህል ጊዜ ሊቆይ ይችላል የሚለው ጥርጣሬ እንደሚፈጥር ያክላሉ።

በ2015 የተፈጸመውን የኒውክሌር ስምምነት ተከትሎ ኢራን የተወሰነውን ገንዘቧን ባገኘችበት ወቅትም የአሜሪካ መንግሥት የተከተለው ተመሳሳይ አካሄድ ነው።

በወቅቱ ባንኮች ጉዳዩን በጥንቃቄ ሲመለከቱ የቆዩ ሲሆን፣ 2018 ላይ ደግሞ አሜሪካ ከስምምነቱ ወጥታ በድጋሚ ማዕቀቦቹን ጥላለች።

የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ባለፈው ሳምንት ባወጣው ዘገባ፤ አሜሪካ ከታገደው ሀብት ውስጥ 12 ቢሊዮን ዶላር እንዲለቀቅ እንደተስማማች ገልጿል። ዋሽንግተን ግን ማረጋገጫ አልሰጠችም።

በተጨማሪም አሜሪካ ከኢራን ውስጥ ሀብት የተወሰነውን ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ለደረሰባቸው ጉዳት ለባሕረ ሰላጤው አገራት ካሳ ለመክፈል ልትጠቀምበት ትችላለች የሚለው ጉዳይ የጥርጣሬ ፈጥሯል።

የአሜሪካ የግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሴንት ሰኔ መጀመሪያ ላይ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት አንድ ጽሑፍ፤ ለእንዲህ ዓይነት ጉዳቶች ክፍያ የሚፈጸመው "ከኢራን አካውንቶች በሚወሰድ ገንዘብ" እንደሆነ ገልጸው ነበር።

የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዜም ጋሪባባዲ ግን የቴህራን ሀብት "የዋሽንግተን የጦርነት ምርኮም ሆነ፤ ለአጋሮቿ ክፍያ የሚውል ገንዘብ እንዳልሆነ" በመግለጽ ተቃውመውታል።

ለኢራን ኢኮኖሚ ምን ለውጥ ያመጣል?

የዓለም ባንክ በ2024 ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ኢራን ኢኮኖሚ 475 ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን ይገመታል።

የኢራን ባለሥልጣናት በጦርነቱ የደረሰው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት 300 ቢሊዮን ዶላር እንደሚገመት ይናገራሉ። በዚህ ዓመት አገሪቱ ኢኮኖሚ በ10 በመቶ ይቀንሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።

ከታገደው ሀብት ውስጥ የተወሰነው እንኳ ከተለቀቀ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የአጭር ጊዜ እፎይታ ሊሰጥ ይችላል።

የኢራን የንግድ ምክር ቤት አባል ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ ባለው የውጭ ምንዛሬ እጥረት በርካታ ትዕዛዞች እንዲቆሙ ወይም ለረጅም ጊዜ እንዲዘገዩ የሚያደረግ ደረጃ" ደርሷል።

በዚህም የተነሳ "ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት ምርቶች መሠረታዊ ሸቀጦች እና ምግብ ብቻ" እንዲሆኑ መገደቡን ገልጸዋል።

ኢራን በቢሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬ ካገኘች የአገሪቱን ገንዘብ ሪያል ዋጋን ማረጋጋት እንዲሁም ኢኮኖሚው ላይ ያለውን ጫና መቀነስ እንደሚቻል ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የዚህ ገንዘብ መምጣት ብቻውን ግን ኢኮኖሚው ያሉበትን ጥልቅ መዋቅራዊ ችግሮች እንደማይፈታ አስጠንቅቀዋል።

ቴህራን ውስጥ የሚገኘው የኢማም ሳዲቅ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚ ፕሮፌሰር የሆኑት ካምራን ኔድሪ "ከማንኛውም የመልሶ ግንባታ ፕሮግራም በፊት የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር እና የኑሮ ውድነት ቀውስን መቅረፍ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል" በማለት ይከራከራሉ።

ሪፎርም ሳይደረግ የፋይናንስ አቅም ወደ ኢኮኖሚው ማስገባት ገንዘቡ ሊያስገኝ የሚችለውን ጥቅም እንደሚቀንስም አንስተዋል።