በዩኬ ሴቶችን በዕፅ ማደንዘዝ እና መድፈርን ከሚያበረታቱ ድረ ገጾች ጋር በተያያዘ ስምንት ሰዎች ታሰሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዩናይትድ ኪንግደም ወንዶች ሴቶችን በዕፅ እንዲያደነዝዙ እና እንዲደፍሩ የሚያበረታቱ የኦንላይን ኔትዎርኮች ላይ በተደረገ ምርመራ ቢያንስ ስምንት ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአገሪቱ ብሔራዊ የወንጀል መከላከል ተቋም አስታወቀ።
በቅንጅት የተፈጸሙ ወሲባዊ ጥቃቶችን የሚያሳዩ ምሥሎች ከተለቀቁባቸው ድረ ገጾች ጋር ግንኙነት ያላቸው 270 ሰዎች መለየታቸውንም ተቋሙ ገልጿል።
በተቋሙ ይፋ የተደረገው ይህ ድርጊት ባለቤቷ በተደጋጋሚ በፅዕ እያደነዘዘ በበርካታ ወንዶች እንድትደፈር ያደረጋት ፈረንሳዊቷ ጅዜል ፔሊኮት ታሪክን ያስታወሰ ሆኗል።
እንደ ኤጀንሲው ገለጻ ይህ ዓይነቱ ጥቃት ብዙውን ጊዜ የሚፈጸመው ከሴቶቹ ጋር ለረጅም ጊዜ አብረው በቆዩ አጋሮቻቸው ሲሆን፣ "ብዙውን ጊዜም" ድርጊቱ "ለአስርት ዓመታት" ይቆያል።
በዕፅ አማካኝነት የሚፈጸም ወንጀል የተወሰኑ ግለሰቦች "የተናጠል ባህሪ" ከመሆኑ አልፎ "የተደራጀ እየሆነ መምጣቱን" የብሔራዊ የወንጀል መከላከል ተቋም ምክትል ዳይሬክተር ናይጄል ሌሪ ተናግረዋል።
ካለፈው ጥቅምት አንስቶ ከአንድ የኦንላይን መድረክ እና ተያያዥ ድረ-ገጾች ጋር ግንኙነት ያላቸው 270 ግለሰቦች እንደተለዩ ተገልጿል።
ተቋሙ ጥቃት ከሚፈጸምባቸው ድረ ገጾች ጋር በተያያዘ ያሰባሰባቸው ማስረጃዎች ለበርካታ አገራት ሕግ አስከባሪ አካላት አስተላልፏል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ አራት ምርመራዎች የተከፈቱ ሲሆን፣ ስምንት ተጎጂዎችም ተለይተው ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።
ተጎጂዎችን ለመለየት እና ለመርዳት ከዐቃቤ ሕግ እንዲሁም ከሌሎች የደኅንነት አካላት ጋር በመሆን የተቀናጀ ምላሽ የሚሰጥበት ሥርዓት መዘርጋቱን የወንጀል መከላከል ተቋሙ አስታውቋል።
ባለፈው ሳምንት የብራዚል፣ የካናዳ፣ የፈረንሳይ፣ የሃንጋሪ፣ የኔዘርላንድስ፣ የስፔን እና የአሜሪካ ሕግ አስከባሪ ተቋማት ተወካዮች ለንደን ውስጥ ተሰብስበው ነበር።
የአገራቱ ተወካዮች "ተጠርጣሪ ወንጀለኞች፣ ተጎጂዎች እና የኦንላይን ቡድኖችን የተመለከቱ መረጃዎችን ስለመለዋወጥ" እንደተወያዩ ተገልጿል።
በዚህ ቅንጅት የተነሳም ከ150 በላይ ወንጀለኞች እና ተጎጂዎች የተለዩ ሲሆን፤ አራት አዲስ የኦንላይን ቡድኖችም ተገኝተዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም ዐቃቤ ሕግ የመድፈር እና ከባድ ወሲባዊ ጥቃቶች ቡድን መሪ የሆኑት ሲኦባን ብሌክ፤ "እየተነጋገር ያለንባቸው ወንጀሎች በዘመኑ ካየኋቸው ሁሉ እጅግ የከፉ ናቸው" ብለዋል።
"ተጎጂዎች በገዛ ቤታቸው ውስጥ ከፍተኛ የእምነት ጥሰት ተፈጽሞባቸው እጅግ አስከፊ ለሆነ የወሲብ ወንጀል እየተጋለጡ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።















