ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ባለፉት 30 ዓመታት በኢትዮጵያ የተፈጠሩ ተጠቃሽ አምስት የፖለቲካ ጥምረቶች ከምን ደረሱ?
ሰባት የተለያየ ፍላጎት እና አመለካከት ያላቸው ታጣቂ ቡድኖች በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራውን የፌደራል መንግሥት በማስወገድ "አካታች የሽግግር መንግሥት" ለመመሥረት ዓላማ አድርገው "ትብብር ለኅልውና" የተባለ ጥምረት መፍጠራቸውን ይፋ አድርገዋል።
ስብስቡ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን)፣ ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነሠ)፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ)፣ የአፋር ብሔራዊ አንድነት አብዮታዊ ግንባር፣ የቤኒሻንጉል ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ እና የጉሙዝ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄን በአባልነት የያዘ መሆኑ ተገልጿል።
ታጣቂ ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም ያንጸባርቁ የነበረው አቋም አንዳቸውን ከሌላቸው የሚያለያዩዋቸው ዕሳቤዎች እንዳሉዋቸው በግልጽ የሚያሳይ ቢሆንም፤ አሁን ላይ በትብብር ለመሥራት መወሰናቸውን ይፋ አድርገዋል። በእርግጥ እነዚህ ቡድኖች የሚያመሳስሏቸው የጋራ አቋሞች እና አካሄዶችም አሏቸው።
ጥምረቱን በተመለከተ እስካሁን ከፌደራል መንግሥቱ በይፋ የተባለ ነገር ባይኖርም የጥምረቱ አባል ከሆኑት መካከል ህወሓት፣ ኦነሠ እና አፋብን "ከኤርትራ እና ከግብፅ" ጋር በመሆን የአገሪቱን ሰላም እና አንድነት ለማናጋት እየሠሩ ነው ሲል መንግሥት ከዚህ በፊት መወንጀሉ አይዘነጋም።
'በፖለቲካ ቋሚ ወዳጅም፣ ቋሚ ጠላት የለም' እንደሚባለው በኢትዮጵያ ታሪክ ተጻራሪ አቋም ያላቸው ቡድኖች በተለያዩ ወቅቶች ጥምረት/ ቅንጅት/ሕብረት መሥርተው ለጋራ ዓላማ ሲሰባሰቡ ቆይተዋል።
እንዲህ ያሉት ስብስቦች 'የጠላቴ ጠላት...' በሚለው ዕሳቤ አብዛኛውን ጊዜ 'የጋራ ጠላትን ማስወገድ' ዒላማቸው አድርገው እንደሚነሱ እና በሒደት ከማሕበራቱ ጀርባ ያሉ ቡድኖች በየፊናቸው እንደሚጓዙም ይስተዋላል።
በትግራይ ጦርነት ወቅት የተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች እና የፖለቲካ ፓርቲዎችም ጥምረቶች ሲፈጥሩ ነበር። ከዚህ ቀደም ሲል በነበሩት ዓመታት ደግሞ በተለይም አገር አቀፍ ምርጫ ሲቃረብ ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ አቋም ያላቸው ፓርቲዎች ገዢውን ፓርቲ ለመገዳደር በጋራ ለመሥራት ከስምምነት ይደርሳሉ።
ከወታደራዊው ደርግ መንግሥት ውድቀት ዋዜማ አንስቶ ወደ አራት አሥርታት በሚጠጋ ጊዜ ውስጥ በተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች ከተፈጠሩ ሕብረቶች መካከል ጎላ ጎላ ያሉትን አምስት የፖለቲካ ጥምረቶች መለስ ብለን ቃኝተናል።
1. ኢሕአዴግ
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) እንደ ጥምር ግንባር የተመሠረተው ግንቦት 1981 ዓ. ም. በትግራይ ክልል፣ በተምቤን ዓዲ ገዛዕቲ በሚባል አካባቢ ነበር።
የአራት የብሔር ድርጅቶች ስብስብ የሆነው ኢሕአዴግ በቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የአገሪቱን የፖለቲካ አቅጣጫ በመቅረጽ በኩል ከሌሎቹ በተለየ በጉልህ የሚጠቀስ ፓርቲ ነው።
በዘመኑ ወደ ስድስት ሚለየን ገደማ አባላት እንዳሉት ይነገርለት የነበረው ግንባሩ ከግራ ዘመም ፓለቲካዊ መርኅ በሚመነጨው አብዮታዊ ዴሞክራሲ በተባለው ርዕዮቱ ሲመራ ቆይቷል።
የግንባሩ አስኳል የሆነው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የደርግ ሥርዓትን በመቃወም ጠብመንጃ አንስቶ ጫካ የገባ ሲሆን፣ ኋላ ላይ ራሱ ደግፎ ያቋቋማቸውን እና ከዓላማው ጋር የሚስማሙ ቡድኖችን አካቶ ነው ኢሕአዴግን የመሠረተው።
በዚህም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴብ)፣ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት(ኦሕዴድ) እንዲሁም የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ከህወሓት ጋር በመሆን ኢሕአዴግን ተቀላቅለዋል።
ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያን በበላይነት የመራው ኢሕአዴግ የአራት ዋነኛ ፓርቲዎች ግንባር ከመሆኑ በተጨማሪ የሐረሪ፣ የአፋር፣ የጋምቤላ፣ የሶማሊ እና የቤኒሻንጉል ክልል ገዢ አምስት ፓርቲዎችን ደግሞ በአጋር ደርጅትነት አቅፎ ነበር።
ኢሕአዴግ በጥብቅ ማዕከላዊነት በአንድ ዓይነት አመለካከት የተዋቀረ ግንባር በመሆኑ በሒደት ስብስቡ ከስም ባሻገር አንድ እስከመሆን ደርሰው ነበር። ነገር ግን ኋላ ላይ ግን ግንባሩ ለ30 ዓመታት ከሚጠጋ አንድነት በኋላ በአባላቱ መካከል የተፈጠረው ልዩነት ጎልቶ የአመራር ለውጥ በማምጣት የኢሕአዴግ ፍጻሜ ሆኗል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ ኢሕአዴግ ከስሞ በርካታ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የብሔር ፓርቲዎችን በማቀፍ አንድ ወጥ አገራዊ ፓርቲ ለመሆን ያለመው ብልጽግና ፓርቲ ተፈጥሯል።
2. ቅንጅት
ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ወደተካሄደው ሦስተኛው አጠቃላይ አገራዊ ምርጫ እንሻገር። ምርጫ 97 በአገሪቱ ታሪክ ያልታየ እንዲሁም ያልተደገመ ጠቅላላ ምርጫ እንደሆነ ይነገርለታል።
ለዚህም ምክንያቱ ኢሕአዴግ የፖለቲካ መድረኩን በመክፈት ነጻ ምርጫ ለማድረግ መዘጋጀቱ እና በዚህ የተበረታቱት ታዋቂ ምሁራን እና ፖለቲከኞች ለምርጫው በተደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸው ነው።
በምርጫ 97 ጎልቶ የወጣው ቅንጅት ለአንድነት እና ዴሞከራሲ ፓርቲ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በዋነኛነት ይጠቀሳል።
ቅንጅት (ቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ) ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አንድ ላይ በማሰባሰብ ገዢውን ፓርቲ በጠንካራ ሁኔታ በመፎካከር እንዲሁም በአዲስ አበባን ከተማ በከፍተኛ ሁኔታ የሕዝብ ድጋፍ እና ድምጽ በማግኘት ይታወሳል።
በኢንጂነር ኃይሉ ሻውል ይመራ የነበረው ቅንጅት ተቀራራቢ የፖለቲካ አቋም ያላቸው ፓርቲዎችን በማሰብሰብ ነበር የተመሠረተው።
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ - መድህን (ኢዴፓ-መድህን)፣ ቀስተ ደመና ለፍትሕ እና ለዴሞክራሲ (ቀስተ ደመና) እና የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሊግ (ኢዴሊ) የቅንጅቱ አባላት ነበሩ።
ከምርጫው አስቀድሞ በተካሄዱ የቅስቀሳ እና የድጋፍ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ በተለይ በአዲስ አበባ በርካታ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች የቅንጅትን አርማ ይዘው አደባባይ ወጥተዋል።
ከኢሕአዴግ ጋር ከፍተኛ ፉክከር ያደረገው ቅንጅት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት መቀመጫዎችን ሙሉ በሙሉ አሸንፎ ነበር። ነገር ግን ከምርጫው ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ውዝግብ እና ግጭት ምክንያት አመራሮቹ ለእስር ተዳርገዋል።
ከመንግሥት የደረሰበትን ጫና ተከትሎ ቅንጅቱ ከመዳከሙ ባሻገር ለምርጫ የተሰባሰቡት አባላቱ አንድነታቸውን ጠብቆ መዝለቅ ሳይችል በተለያዩ አቅጣጫዎች ተበትነዋል።
በዚህም የቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ አብዛኞቹ አመራሮቹ ከፖለቲካው የራቁ ሲሆን፤ አዲስ ፓርቲ የመሠረቱ፣ ወደ ትጥቅ ትግል እና ወደ ስደት ያቀኑም ይገኙበታል።
3. ሕብረት
ምርጫ 97 ከፈጠራቸው የፖለቲካ ጥምረቶች መካከል ከቅንጅት ባሻገር ተጠቃሽ የሆነው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ሕብረት (ሕብረት) ነው።
የአሁኑ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ ልደቱ አያሌው፣ ኃይሉ ሻውል እና ያዕቆብ ኃይለማሪያም በቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ ጥላ ሥር ሲሰባሰቡ፤ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ እና ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ደግሞ ሌሎችንም አካተው ሕብረትን በመመሥረት ወደ ምርጫው ገብተው ነበር።
በሕብረት ሥር የተሰባሰቡት ፓርቲዎች ብሔር ተኮር የሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የነበሩ ሲሆን፤ የድጋፍ መሠረታቸውም በተለይ ኦሮሚያ እና የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ነበሩ።
ትንንሽ ግን ብዙ ፓርቲዎች ባሉበት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ የተሻለ ፉክክር ለማድረግ እና ተጽዕኖ ለመፍጠር በሚል ከተመሠረቱ ጥምረቶች አንዱ ሕብረት ነበር።
በወቅቱ የሕብረት አባላት የነበሩ እና መቀመጫቸውን በባሕር ማዶ አድርገው የነበሩ የረዥም ጊዜ የፖለቲካ ልምድ የነበራቸው እንደ መኢሶን፣ ኢሕአፓ እና መድኅንን የመሰሉ ፓርቲዎችም የስብስቡ አካል ነበሩ።
በአገር አቀፍ ምርጫው የተሳተፉት ግን ኢትዮጵያ የነበሩት ፖለቲከኞች ብቻ ናቸው።
እንደ ቅንጅት ሁሉ ሕብረት የሚያካሂዳቸው የምርጫ ክርክሮች በቴሌቪዥን የቀጥታ ሥርጭት እንዲሁም በራድዮም ሲተላለፉ የበርካቶችን ቀልብ ስቦ ነበር።
ሕብረት በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር የሚንቀሳቀሱ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች ስብስብ ከመሆኑ አንጻር በተለይ ኢሕአዴግ በጠላትነት የሚመለከታቸው ኢሕአፓ እና መኢሶን በሕብረቱ ውስጥ መግባታቸው ስብስቡን ጥርስ አስነክሶበት ነበር።
በፕሮፌሰር መረራ ጉዲና የሚመራው ኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ፣ በፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ ፓርቲ እንዲሁም የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ሕብረት እና የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ፓርቲ የሕብረቱ አባላት ነበሩ።
4. የፌዴራሊስ ኃይሎች ጥምረት
ሦስት አሥርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ኢትዮጵያን በበላይነት ሲመራ የነበረው ህወሓት በአጋሮቹ ተገፍቶ ወደ ዳር ሲወጣ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ኢሕአዴግ ለገነባው ፌደራላዊ ሥርዓት ስጋት ነው ሲል ቆይቷል።
ይህንንም ተከትሎ በአዲሱ አስተዳደር ላይ ቅሬታ ያቸላውን ኃይሎች በማሰባሰብ የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረትን በ2011 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ መቀለ ውስጥ መመሥረቱን አስታውቋል።
ወደ 25 የሚጠጉ አባላት እንዳሉት የተነገረለት ጥምረቱ የተመሠረተው "አገርን ለማዳን" እንደሆነ እና በስብስቡ ውስጥ ያሉ ኃይሎችም "ለኅብረ ብሔራዊ ፌደራል ሥርዓት ዘብ የሚቆሙ" መሆናቸው በወቅቱ ተገልጾ ነበር።
የኢትዮጵያ ፌደራሊስት ኃይሎች ጥምረት ለአገር መድኅን የተባለው የፖርቲዎች ስብስብ ህወሓት ከ25 ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በመሆን የመሠረተው ቢሆንም፤ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ህወሓት እና የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሕብረት (ኢዴሕ) ከጥምረቱ መተዳደሪያ ደንብ ውጪ ሆነው ተገኝተዋል በሚል ከአባልነት መሰረዛቸው ተገልጿል።
በአንድ ምርጫ ምልክት እንደሚወዳደሩ ሲገልጹ የነበሩት ፓርቲዎች ከጊዜ በኋላ እርስ በርስ ሲካሰሱ እና የተናጠል መግለጫ ሲሰጡም ነበር።
ከህወሓት በተጨማሪ የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር፣ የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የቤንሻንጉል ሕዝቦች ነጻነት ንቅናቄ፣ የጋምቤላ ሕዝቦች ነጻነት ጦር የቅማንት ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የሲዳማ ብሔራዊ ነጻነት ግንባር እንዲሁም ሌሎችም ፓርቲዎች የስብስቡ አባል ነበሩ።
በጥምረቱ መካከል ክፍፍል ሲፈጠር አንደኛው ወገን ህወሓት "ሕብረቱን የራሱ ጥገኛ አድርጎ ሊጠቀምበት እየተንቀሳቀሰ ነው" ሲል ከስሷል።
ሌላኛው ወገን ደግሞ "በአክራሪ አሀዳውያን እና ፀረ ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ኃይሎች" ምክንያት ጥምረቱ ስጋት እንዳጠላበት በመግለጽ ወንጅሏል።
በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መሪዎች መካከል የተፈጠረው ውዝግብ ተባብሶ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ የትግራይ ኃይሎች ወደ አዲስ አበባ በተቃረቡበት ጊዜም በህወሓት መሪነት አሜሪካ ውስጥ አንድ ስብስብ ይፋ ተደርጎ ነበር።
ስብስቡ ከአዲስ አበባው መንግሥት መውደቅ በኋላ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት የተፈጠረ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ውጪ ሌሎቹ አባላቱ እምብዛም የሚታወቁ አልነበሩም።
ነገር ግን የትግራይ ኃይሎች ግስጋሴ ተገትቶ ተዋጊው ወደ ትግራይ ከተመለሰ እና ጦርነቱ በፕሪቶሪያ ስምምነት ካበቃ በኋላ ዋሽንግተን ውስጥ የተሰባሰቡት የሽግግር መንግሥት መሥራች ቡድኖች የት እንደደረሱ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።
5. ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት
ባለፈው ዓመት ግንቦት ላይ የተካሄደውን ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ግብ አድርጎ የተመሠረተው ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ስብስብ የአምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕብረት ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እንዲሁም እናት ፓርቲን ጨምሮ አምስት ፓርቲዎችን ያሉት ስብስቡ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ያገኛቸውን ሰባት ወንበሮች እንደማይረከብ ማስታወቁም አይዘነጋም።
ጥምረቱ በተደጋጋሚ ያወጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች እንዳልተሟሉ በመግለጽ ከምርጫው ራሱን እንደሚያገልል ሲያሳውቅ ቆይቶ፤ ከምርጫው ከሁለት ቀን በኋላ ደግሞ ቢያሸንፍም ምክር ቤት እንደማይገባ ገልጾ ነበር።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው አጠቃላይ የምርጫ ውጤት እንደሚያሳየው፤ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ሁለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና አምስት የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎችን አሸንፏል።
ጥምረቱ 1,032 ዕጩዎችን በማቅረብ ከብልጽግና እና ከኢዜማ ቀጥሎ ከፍተኛ ተመራጮችን ለተለያዩ ምክር ቤቶች ያስመዘገበ ሦስተኛው ፓርቲ ነው።
በአዲስ አበባ፣ በአማራ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች በአጠቃላይ ሰባት ወንበሮችን ያሸነፈው ትብብሩ፤ ምርጫውን "የጨረባ" ሲል አውግዟል።
ስብስቡ አገር አቀፉን ምርጫ "እጅግ የተወሳሰበውን የአገራችንን ችግር ከድጡ ወደ ማጡ ከመውሰድ በዘለለ ዲሞክራሲን አያዋልድም" በማለትም አጣጥሎታል።
ይህ ለምርጫ ተሳትፎ የተፈጠረው ትበብር ከምርጫው ፍጻሜ በኋላ የጎላ እንቅስቃሴ እያደረገ አይደለም። የተመሠረተበትን ዓላማ አጠናቆ መክሰሙም ሆነ ወደ ሌላ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሕብረት ስለመሸጋገሩም የተባለ ነገር የለም።