በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የእናት ጡት ወተት ባንክ ተከፈተ

በጠርሙስ ሆነው ማቀዝቀዣ ውስጥ የተቀመጠና የተለገሰ የእናት ጡት ወተት

የፎቶው ባለመብት, DR. Fitsum W/Gabriel

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነ የእናት ጡት ወተት ባንክ በሐዋሳ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ውስጥ ተከፈተ።

ባለፈው ሳምንት ሰኔ 6/2018 ዓ.ም ከሌሎች የሆስፒታሉ ፕሮጀክቶች ጋር በጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ ተመርቆ የተከፈተው ባንኩ የጨቅላ ሕፃናትን ሞት እንደሚቀንስ ተስፋ ተጥሎበታል።

ባንኩ ከለጋሽ እናቶች የተሰበሰበ ወተት የደኅንነት ሂደቶችን አልፎ የሚጠራቀምበት ሲሆን፣ ወተቱ በተለያየ ምክንያት ከእናቶቸቻው የጡት ወተት ማግኘት ለማይችሉ ጨቅላ ሕፃናት ያቀርባል።

የሃሳቡ አመንጪ በዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሉ የጨቅላ ሕፃናት ሰብ ስፔሻሊስት እና የኮሌጁ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ዶ/ር ፍፁም ወልደ ገብርኤል ለቢቢሲ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕረሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ባንኩን በመክፈት ከአፍሪካ ዘጠነኛዋ አገር ሆናለች።

ከዘጠኙ ግዛቶቿ በሰባቱ 20 የሚጠጉ የጡት ወተት ባንኮች ያሏትን ደቡብ አፍሪካ እና ኬንያን ጨምሮ በርካታ አገራት አገልግሎቱን ይሰጣሉ።

ዶ/ር ፍፁም በሆስፒታሉ ብቸኛ የጨቅላ ሕፃናት ሰብ ስፔሻሊስት ያደረጋቸውን ትምህርታቸውን በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን አጠናቀው ወደ አገራቸው ሲመለሱ የተመለከቱት ችግር ነበር ይህን ባንክ ለማቋቋም ምክንያት የሆናቸው።

ዶ/ር ፍፁም እንደሚሉት በሆስፒታሉ በተለይ ያለ ቀናቸው የሚወለዱ ጨቅላ ሕፃናት የእናታቸውን ወተት አያገኙም፤ እናቶችም በተለያየ የጤና እክል ምክንያት ወተት ማመንጨት ሳይችሉ ይቀራሉ።

በዚህም ምክንያት ጨቅላ ሕፃናቱ ለረዥም ጊዜ ወተት ሳያገኙ በደም ሥር በሚሰጥ ፈሳሽ ብቻ ሕክምና ያገኛሉ።

ይህ ግን ለተለያየ ኢንፌክሽን ብሎ ለሞት ይዳርጋቸዋል። ሕፃናቱ ማደግ በሚገባቸው ልክም አያድጉም።

ይህንን ለማስቀረት በማለም ነው በደቡብ አፍሪካ የትምህርት ቆይታቸው ያዩትን ተሞክሮ ወደ አገራቸው ያመጡት።

የዓለም ጤና ድርጅት ከሁለት ዓመት በፊት ባወጣው መረጃ በአውሮፓውያኑ 2022 በዓለም 2.3 ሚሊዮን ሕፃናት በተወለዱ በመጀመሪያቹ 28 ቀናት ሞተዋል። ይህ ማለት በአንድ ቀን 6 ሺህ 500 አዲስ የተወለዱ ሕፃናት ይሞታሉ ማለት ነው።

አብዛኞቹ ሞቶች የተመዘገቡት ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት ሲሆን፣ አዲስ ከሚወለዱ 1000 ሕፃናት 27ቱ ይሞታሉ።

ከሞታቸው ምክንያቶች መካከል ያለቀን መወለድ፣ የእናት ጡት ወተት ካለማግኘት እንዲሁም በሌሎች ምክንያቶች በሚመጣ ኢንፌክሽን እና በወሊድ ጊዜ የሚያጋጥም ውስብስብ ችግር መሆኑ ይጠቀሳል።

ማቀዝቀዣ ውስጥ የተቀመጠን ወተት የምትመለከት የምታስተካክል ባለሙያ

የፎቶው ባለመብት, DR. Fitsum W/Gabriel

የጡት ወተት መለገስ የሚችለው ማን ነው?

ዶ/ር ፍፁም እንዳሉት የእናት ጡት ወተት ለመለገስ የራሱ የሆኑ ሒደቶች አሉት።

አሁን በሐዋሳ ኮንፕሪሄንሲቭ ሆስፒታል ውስጥ በተከፈተው ባንክ የጡት ወተት ልገሳ የሚያደርጉት ወደ ሆስፒታሉ ለወሊድ አገልግሎት የሚሄዱ እናቶች ናቸው።

ሆኖም እነዚህ እናቶች ወተታቸውን መለገስ የሚችሉት ልጃቸውን በበቂ መግበው የሚተርፋቸው ከሆነ ብቻ ነው።

ይህ ከሆነ ለመለገስ ብቁ ናቸው ተብሎ ይታያል።

ከዚያም ፈቃደኝነቷ ይጠየቃል። ለመለገስ ፈቃደኛ ከሆነች ኤችአይቪን ጨምሮ በጡት ወተት ሊተላለፉ የሚችሉ በሽታዎች እንደሌሉባት ለማረጋገጥ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ምርመራ ይደረግላታል።

የጡት ወተቷ ጤናማ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ወተቷን መለገስ በምትችልበት ሰዓት ይሰበሰባል።

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ እና ሎሎች የጡት ወተቱ የተቀመጠበትን ማቀዝቀዣ ሲጎበኙ

የፎቶው ባለመብት, DR. Fitsum W/Gabriel

የምስሉ መግለጫ, የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ የእናት ጡት ወተት ባንኩን እና ሌሎች የሆስፒታሉን የጤና ፕሮጀክቶች መርቀዋል

ከዚያም ወተቱ ተቀነባብሮ [ፓስቸራይዝድ] ተደርጎ በባንኩ ማቀዝቀዣ ውስጥ ይቀመጣል።

የጡት ወተቱ ከዜሮ በታች -20 ዲግሪ ሴንት ግሬድ በማቀዝቀዣ ውስጥ ለስድስተት ወራት ያህል መቆየት ይችላል።

ይህ ከለጋሽ እናቶች የተገኘ ጤናው የተጠበቀ ወተትም በተለያየ የጤና እክል ምክንያት በቂ ወተት ማመንጨት የማይችሉ እናቶች ጨቅላ ልጆች ይሰጣል።

ወተቱ ከመሰጠቱ በፊት እነዚህ እናቶች የምክር አገልግሎት የሚያገኙ ሲሆን፣ ለጨቅላ ልጃቸው እንዲሰጥ በፊርማቸው በማረጋገጥ መፍቀድ ይኖርባቸዋል።

አሁን ላይ የጡት ወተቱ የሚሰበሰበው ወደ ሆስፒታሉ ከሚሄዱ ወላዶች ሲሆን፣ የሚለገሰውም እዚያው ሆስፒታል ለተኙ ጨቅላ ሕፃናት ብቻ እንደሆነም ዶ/ር ፍፁም ተናግረዋል።

ነገር ግን ወደፊት ማንኛዋም ብቁ የሆነች እናት መለገስ የምትችልበት ዕድል እንደሚመቻች ገልጸዋል።

በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎችም አገልግሎቱን ለማስፋፋት ዕቅድ ያለ ሲሆን፣ የጤና ፖሊሲ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ በጥናት ላይ የተመሠረቱ ውይይቶች እንደሚካሄዱም ጠቁመዋል።

ጨቅላ ሕፃናቱ የጡት ወተቱ የሚሰጣቸው ለምን ያህል ጊዜ ነው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሕፃናት በተወለዱ በአንድ ሰዓት ውስጥ የእናት ጡት ወተት ማግኘት አለባቸው። ይህም እንገር የሚባለውንና ለልጆቹ ጤና ልክ እንደ ክትባት የሚጠቅመውን ንጥረ ነገር እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።

ከዚያም እስከ ስድስት ወር ድረስ ያለ ተጨማሪ ምግብ፣ ከስድስት ወር በኋላ ደግሞ ከተጨማሪ ምግብ ጋር እስከ ሁለት ዓመት ድረስ የእናት ጡት ወተት እንዲመገቡ ይመከራል።

የጡት ወተት ባንኩ አገልግሎት የሚሰጠው ግን ያለ ቀናቸው ተወልደው የእናት ጡት ወተት ማግኘት ላልቻሉ ጨቅላ ሕፃናት ብቻ ነው። ልገሳው የሚደረገውም ከአምስት እስከ ሰባት ቀን ድረስ ብቻ ነው።

"በዚህ ጊዜ እናቶች ልጆቻቸውን ለመመገብ ዝግጁ ይሆናሉ ተብሎ ይታሰባል።" ብለዋል ዶ/ር ፍፁም።

ሆኖም እናቶቸቻውን በተለያየ ምክንያት በሕይወት ያጡ ጨቅላ ሕፃናት በሆስፒታሉ ውስጥ በሚቆዩበት ጊዜ ባንኩ የጡት ወተት ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ገልጸዋል።

"የጡት ወተት ልገሳው የሚሰጠው እናቶች ማጥባት እስከሚችሉበት ወይም እናቶቻቸውን ያጡ ጨቅላ ሕፃናት ዘላቂ ምግብ እስከሚያገኙ ድረስ እንደ ድልድይ ነው።"

ይህ ከለጋሽ የሚገኝ ወተት ከጥቅሙ ባሻገር ጎንዮሽ ጉዳት ያለውን እና ተበጥብጦ የሚሰቸጣውን የዱቄት ወተት እንደሚያስቀርም ዶ/ር ፍፁም አክለዋል።

ጨቅላ ሕፃናት ከእናታቸው ወተት ማግኘት ካልቻሉ ከሌሎች እናቶች የተሰበሰበ እና ጤንነቱ የተጠበቀ ወተት ማግኘት እንዳለባቸውም ይመክራሉ።

በኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ 2024/25 የወጣው የሕዝብ እና ጤና ጥናት እንደሚያመለክተው ከሚወለዱ 100 ሕፃናት 25ቱ ይሞታሉ።

ቁጥሩ ቀደም ብሎ ከነበሩት ዓመታት የቀነሰ ቢሆንም አሁንም አሳሳቢ ነው ያሉት ዶ/ር ፍፁም በ2030 ወደ 15 ዝቅ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

"ይህንን ከምናሳካበት መንገዶች መካከል አንዱ ደግሞ የጡት ወተት ምገባ ነው" ብለዋል።

እንደ ዶ/ር ፍፁም ከሆነ የእናት ጡት ወተት ባንክ ከ20 እስከ 30 በመቶ የሚሆን የጨቅላ ሕፃናትን ሞት መቀነስ ይቻላል ተብሎ ይታሰባል።

ከልገሳ የሚገኝ ወተት ከእናታቸው የጡት ወተት ማግኘት ላልቻሉ ጨቅላ ሕፃናት ጉዳት የሚያስከትሉ ወተቶችን እና በደም ሥር የሚሰጡ ፈሳሾችን የሚያስቀር ሲሆን፣ ከጡት ወተት ወሳኝ ንጥረ ነገር እንዲያገኙ ያደርጋል።