የምርጫ ውዝግብ በገጠማት ሶማሊያ በፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግሥት አቅራቢያ ተኩስ ተሰማ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሹ ውስጥ በሚገኘው ቤተ መንግሥት አቅራቢያ ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ መሰማቱ ተዘገበ።

ከሶማሊያ ፕሬዝዳንታዊ መቀመጫ 'ቪላ ሶማሊያ' ቅርብ ርቀት ላይ በአንዳንድ የመዲናዋ አካባቢዎች ተኩስ የተነሳው አገሪቱ ከምርጫ ሒደት ጋር በተያያዘ የፖለቲካ ውጥረት ውስጥ ባለችበት ወቅት ነው።

የሥልጣን ዘመናቸው የተጠናቀቀው የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ሥልጣናቸውን ለማራዘም ያደረጉትን ሙከራ ተከትሎ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።

በአገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት የፕሬዝዳንቱ የሥልጣን ዘመን ያበቃው ግንቦት 7/2018 ዓ.ም. ነው።

በዋ ናከተማዋ ዳብካ እና ሳይድካ በተባሉ አደባባዮች መካከል ባለው አካባቢ የተኩስ ድምጽ መሰማቱ ተገልጿል።

አካባቢው ለቤተ መንግሥቱ ቅርብ የሆነ ስትራቴጂያዊ ሥፍራ ነው።

ሳይድካ አደባባይ ወደ ቪላ ሶማሊያ ከሚወስዱ ዋነኛ መንገዶች አንዱ ነው።

ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ መሰማቱ ሪፖርት ከተደረገ በኋላ የሶማሊያ የፀጥታ ባልደረቦች ምላሽ መስጠታቸው ተገልጿል።

ተቃዋሚ ፖለቲከኞች የሆኑት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሐሰን አሊ ካሂር እና የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሻሪፍ ሼኽ አሕመድ እንዲሁም ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ መሐመድን ጨምሮ ሌሎችም የምርጫ ጉዳይን በተመለከተ ለማሸማገል ጥረት እያደረጉ ነው።

ሆኖም ግን እየተደረጉ ያሉት ውይይቶች ተቃዋሚዎች ለማካሄድ ያሰቡትን ሰላማዊ ሰልፍ ማስቀረት እንዳልቻለ ተገልጿል። ግጭት እንዳይከሰት ለማድረግ ስምምነት ላይ ለመድረስ የተደረገው ጥረትም ውጤታማ አለመሆኑ ተጠቁሟል።

የቀድሞው የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐሰን አሊ ካሂር ፌስቡክ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ እንደገለጹት ፕሬዝዳንቱ ትዕዛዝ በሰጧቸው የፀጥታ አካላት ጥቃት ደርሶባቸዋል።

"የሥልጣን ዘመናቸው ባበቃው ፕሬዝዳንት ትዕዛዝ ጥቃት ተፈጽሞብናል። የሞቱትን ሰዎች ፈጣሪ ይቅር እንዲላቸው እንዲሁም የተጎዱት በፍጥነት እንዲያገግሙ እፀልያለሁ" ብለዋል።

"በዚህ ክስተት ለሚፈጠው ሞት እና ውድመት ኃላፊነቱን የሚወስዱት ሰላማዊ ተቃውሞ ልናካሂድ ስንል ጥቃት የከፈቱብን ፕሬዝዳንቱ ናቸው" ሲሉም አክለዋል።

ተቃዋሚዎች የፊታችን አርብ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያካሂዱ አስታውቀዋል።

የባናዲር ክልላዊ አስተዳደር የተቃውሞ ሰልፍ እንዲካሄድ ፈቅዷል። ለደኅንነት ሲባል ተቃውሞው የተመደበለት ቦታ ላይ ብቻ ተወስኖ እንደሚካሄድ በክልሉ አስተዳደር ተገልጿል። በሰልፉ ወቅት መሣሪያ መታጠቅም ተከልክሏል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ዛሬ ረቡዕ የተለቀቁ ምሥሎች እንደሚያሳዩት ከተቃዋሚዎች ጋር ቅርበት ያላቸው ሰዎች ወታደራዊ መለያ አድርገው በከፍተኛ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ሞቃዲሹ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ያሳያሉ።

ከሰሞኑ የተነሳው ውጥረት ከሶማሊያን የምርጫ ሒደት ጋር ይገናኛል።

የፕሬዝዳንቱ የሥልጣን ዘመን ማብቃቱን ተከትሎ መንግሥት እና ተቃዋሚዎች ያደረጉት ድርድር እስካሁን ከስምምነት አላደረሳቸውም።

የታቀዱት ሰልፎች በሰላም ስለመጠናቀቃቸው ግልጽ አይደለም።

በቤተ መንግሥቱ አቅራቢያ በተነሳው ተኩስ ምክንያት ሞት ወይም ጉዳት ስለመድረሱ አሁን ላይ ከባለሥልጣናት የወጣ መረጃ የለም።