ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ለምን ስለ እናታቸው በአደባባይ አይናገሩም?
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪን ጆንግ ኡን በምሥጢር ከያዟቸው ነገሮች አንዱ የእናታቸው ጉዳይ ነው።
ለ15 ዓመታት በሥልጣን ሲቆዩ አንድም ቀን የእናታቸውን ስም በአደባባይ አንስተው አያውቁም።
በቤተሰብ የዘር ሐረግ ላይ የተመሠረተው አምባገነናዊ አስተዳደር 'ማውንት ፔክቱ' ይባላል። ኮሪያ ከሚገኝ ባሕረ ገብ መሬት ነው መጠሪያውን ያገኘው።
ኮሪያውያን የተገኙት ከዚህ አካባቢ ነው የሚል አፈ ታሪክም ይነገራል። የአገሪቱ መሥራች ኪም ኢል ሱንግ ከጃፓን ቅኝ ገዢዎች ጋር የሽምቅ ውጊያ አድርገው ያሸነፉበት ሥፍራ ነው።
የአገሪቱ መሥራች እናት ካንግ ፓን ሶክ ይባላሉ። የኪም ኢል ሱንግ ምክትል ኪም ጆንግ ኢል እናት ኪም ጆንግ ሶክ ናቸው።
ሁለቱ የመሪዎች እናቶች "የኮሪያ እናት" ተብለው ይታወቃሉ። በተቃራኒው የአሁኑ መሪ ኪም ጆንግ ኡን እናት ኮ ዮንግ ሁይ ብዙም አልተነገረላቸውም።
እናቱ የተገኙት ከከፍተኛው መደብ ስላልነበረ እና ውሽማ በመሆናቸውን ለአስተዳደሩ ስጋት እንደሆኑ ይቆጠራሉ።
የታሪክ ፀሐፍት ባገኙት መረጃ ኮ የተወለዱት ኦሳካ፣ ጃፓን በአውሮፓውያኑ 1952 ነው። ቤተሰቦቻቸው የተወለዱት እንደ ጠላት ይዞታ ከሚቆጠረው አሁን ደቡብ ኮሪያ ውስጥ በሚገኘው ጄጁ ደሴት ነው።
ጃፓን አካባቢውን ከ1910 እስከ 1945 በቅኝ ግዛት ይዛለች። የኮ ወላጆች እንደ ስደተኛ ይቆጠራሉ። የዚህ አካባቢ ተወላጆች ወደ ሰሜን ኮሪያ ሲመለሱ ብዙዎች ይቀኑባቸው ነበር።
ከካፒታሊስቷ ጎረቤት አገር ገንዘብ፣ ልብስ እና የቤት ቁሳቁስ ወደ ሰሜን ኮሪያ ወስደዋል።
በሰሜን ኮሪያ በውጭ አገር ዕሳቤ "ተበርዘዋል" ተብለው የተፈረጁ ሰዎች "ጂያዎፖ" ተብለው ይጠሩ ነበር። የኮ ቤተሰቦችም በዚህ ፍረጃ ተካትተዋል።
የሰሜን ኮሪያ ማኅበራዊ መደብ "ሶንግበን" ይባላል። የኮ ወላጆች "ዛይኒቺ" በተባለው መደብ ሥር ናቸው። በመንግሥት ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ሲሆን፣ ጥሩ ዩኒቨርስቲዎች እንዳይገቡ እና ጥሩ ሥራ እንዳያገኙ ይታገዳሉ።
ሰሜን ኮሪያ የበላይ እና የበታች የሆኑ ተዋረዳዊ ማኅበረሰብ ያላት አገር ናት። ሰዎች በመደብ ወይም በጎሳ እንደሚፈረጁ ተንታኞች ይናገራሉ።
ዶንግያንግ ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩት ዶ/ር ጄዩንግ ዮንግ-ቴ "ዜጎች በቤተሰቦቻቸው መደብ ምክንያት የሚቀጡበት ሥርዓት ነው" ይላሉ።
ኮ 10 ዓመት ሲሞላቸው ቤተሰቦቻቸው ሰሜን ኮሪያ ሄዱ። ከ1959 እስከ 1984 ድረስ ከጃፓን ወደ ኮምኒስቷ ሰሜን ኮሪያ ከተሰደዱ 93 ሺህ ኮሪያውያን መካከል ይገኙበታል።
በወቅቱ "ምድራዊ ገነት" የሚል ንቅናቄ ነበር። ወደ ሰሜን ኮሪያ የሚመለሱ ኮሪያውያን ነጻ ሕክምና፣ ትምህርት እና ሥራ እንደሚያገኙ ተነግሯል።
ኮ እና ሌሎችም በእሳቸው መደብ ሥር ያሉ ኮሪያውያን የጠበቃቸው ግን የስቃይ ኑሮ ነበር።
ኮ የወቅቱ የአገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኢልን ትኩረት ሳቡ። በእርግጥ መሪው በይፋ ስለ ባለቤታቸው ተናግረው ባያውቁም ከከፍተኛ መደብ ከተገኙት ኪም ዮንግ ሱክ ጋር በትዳር ተጣምረው እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።
የትዳር አጋራቸውን የመረጡላቸው አባታቸው ነበሩ። ኮ የዝነኛው ማንሳውድ የተባለው የኪነጥበብ ቡድን አባል የነበሩ ሲሆን፣ "በውበታቸው እና በዳንስ ችሎታቸው" የመሪውን ቀልብ እንደገዙ በአውሮፓውያኑ 2025 ስለ ኮ መጽሐፍ ያሳተሙት ዮጂ ጎሚ ይናገራሉ።
ኮ ከመሪው ጋር ትዳር ባይመሠርቱም ጥምረታቸውን አገዛዙ ዕውቅና ሰጥቶታል።
ኪም ባለ ትዳር ቢሆኑም በኮ ፍቅር እንደወደቁ ይነገራል። ነገር ግን መሪው ይፋዊ ሚስት ስለነበራቸው ኮ እና ሦስት ልጆቻቸው ቤተ መንግሥት መኖር አልቻሉም።
ከመዲናዋ ፒዮንግያንግ 210 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የወደብ ከተማ ዎንሰን ይኖሩ ጀመር።
በኖርዘርን ሪሰርች አሶሴሽን የሚሠሩት ኪም ሁያንግ-ሱ "ኪም ጆንግ ኡን የተወለዱት በይፋ ከሚታወቁት ሚስት አይደለም። የኮ 'ከጋብቻ ውጭ የተወለዱ ልጅ' ናቸው" ይላሉ።
"የአገዛዙ የዘር ሐረግ የተከበረ ተደርጎ ይወሰዳል። ስለዚህ መሪው ከዝቅተኛ መደብ ጋር መጣመራቸው የሚታሰብ አይደለም" በማለትም ያክላሉ።
ከትዳር ውጭ የተወለዱ ልጆች በአገሪቱ የተገለሉ ናቸው።
ኪም ጆንግ ኡን ከዋና ከተማዋ ተገልለው ነው ያደጉት። በወቅቱ ከሚኖሩበት ከተማ ወደ ጃፓን የሚጓዝ መርከብ ነበር።
እናታቸው ከጃፓን የሚመጡ ሰዎችን በቀላሉ እያገኙ እቃ ይቀበሉ ነበር።
ታሪካቸውን የጻፉት አጥኚ "ኮ አገሯ ጃፓን በጣም ይናፍቃት ነበር። ልጆቿን ጃፓንኛ አስተምራለች" ይላሉ።
ከአውሮፓውያኑ 1988 እስከ 2001 በጃፓን ተወዳጅ የሆነውን ምግብ ሱሺ፣ ለኪም ጆን ኢል ያበስል የነበረው ሼፍ ኬንጂል ፉጂሞቶ በጻፈው መጽሐፍ ኮ "ጃፓንኛ በመዝፈን ድንቅ ነበረች። የጃፓን ብልጽግናም ያስቀናት ነበር" ብሏል።
ኪም ጆንግ ኡን ከታላቅ ወንድማቸው ጋር ጃፓን፣ ቶኪዮ የሚገኘውን የልጆች መዝናኛ ዲዝኒላንድ መጎብኘታቸውን የጃፓን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ስለ ኮ መጽሐፍ ያሳተሙት ዮጂ ጎሚ እንደሚሉት ኮ ከፀሐፊያቸው ጋር በምሥጢር ጃፓንን ጎብኝተዋል።
ስለ ኪም ጆንግ ኡን መጽሐፍ ያሳተሙት በስደት የሚኖሩት የሰሜን ኮሪያ ዲፕሎማት ሩዩ ሁዩን-ው "ኪም ኢል ሱንግ በመሪነት ዘመናቸው ኮ የልጃቸው ሚስት እንደሆነች አልተቀበሉም ነበር" ይላሉ።
የመሪው አባት ለኮ ዕውቅና ቢሰጡ ኖሮ ከኪም ጆንግ ኡን ጋር አብረው ይታዩ እንደነበር በሴጆንግ ኢንስቲትዩት የሚሠሩት ዶ/ር ቼዎንግ ሴዎንግ-ቻንግ ይናገራሉ።
ኪም ጆንግ ኢል ግን ኮን ያምኗቸው ነበር። የአገሪቱ የእጅ አዙር መሪ ሲሆኑም አብረዋቸው ወታደራዊ ቅኝት ያደርጉ ነበር።
ፖሊሲዎች ላይ ከመወሰናቸው በፊት ኮ አስተያየት እንዲሰጧቸው ይጠይቁ እንደነበር የኪም ጆን ኢል ሼፍ የነበሩት ኬንጂል ፉጂሞቶ ይናገራሉ።
በአውሮፓውያኑ 2011 ኪም ጆንግ ኢል ከሞቱ በኋላ በተለቀቀ ዘጋቢ ፊልም ላይ ኮ እና መሪው የአገር ውስጥ ጉብኝት ሲያደርጉ ታይተዋል።
ዘጋቢ ፊልሙ በይፋ ባይለቀቅም በአውሮፓውያኑ 2012 ለፓርቲው አመራሮች ቀርቧል። ኋላ ላይ ግን ፊልሙ ሾልኮ በመውጣቱ ብዙዎች ተመልክተውታል።
ሴጆንግ ኢንስቲትዩት የሚሠሩት ዶ/ር ቼዎንግ ሴዎንግ-ቻንግ "ሰዎች ስለ ኮ የማወቅ ጉጉታቸው በመጨመሩ አገዛዙ በፍጥነት ዘጋቢ ፊልሙን ሰረዘ" ይላሉ።
ኮ የመጡበት የቤተሰብ ታሪክ አገዛዙ ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ እንደሆነ በማመን ለመሸፋፈን እንደተሞከረ ያስረዳሉ።
ከትዳር ውጭ የተወለዱት ኪም ጆንግ ኡን እንዴት ሥልጣን ያዙ? የሚል ጥያቄ መነሳቱም አይቀርም።
ኪም ጆንግ ኡን ለኮ ሁለተኛ ልጅ ናቸው። ለአባታቸው ደግሞ የመጨረሻ ልጅ።
ኮ ልጃቸው ኪም ጆንግ ኡን ሥልጣን እንዲረከብ ማድረጋቸውን የታሪክ ፀሐፍት ይናገራሉ።
ኪም ጆንግ ኡን ሥልጣን ካልያዙ ቤተሰባቸው አደጋ ውስጥ እንደሚወድቅ ታናሽ እህታቸውም እንደነገሯቸው ስለ መሪው መጽሐፍ ያሳተሙት አና ፊፊልድ ይገልጻሉ።
የኪም ጆንግ ኢል የመጀመሪያ ልጅ ኪም ጆንግ ናም ቤተሰባዊ አገዛዝ ላይ ጥያቄ በማንሳቱ ከአስተዳደር ውጭ እንዲሆን ተደርጓል።
ኪም ጆንግ ናም ውጭ አገር በመማሩ እና አኗኗሩም ከቤተሰቡ የተለየ ስለሆነ አመለካከቱ መለወጡ ይነገራል።
የኮ የመጀመሪያ ልጅ ጆንግ ቹል ከፍተኛ ኦፒየም የተባለው አደንዛዥ ዕጽ ሱስ ስላበት ለመሪነት አልታጨም።
ኪም ጆንግ ኡን የመሪነት ባህሪ ስላላቸው እና ፉክክር ስለሚወዱ በአባታቸው ተመራጭ ሆነዋል።
ኪም ጆንግ ኡን እና ታላቅ ወንድማቸው ስዊትዘርላንድ ውስጥ ሲማሩ የኮ እህት እና ባለቤት ይንከባከቧቸው ነበር።
በ1998 ኮ የጡት ካንሰር እንዳለባቸው ሲነገራቸው ግን ጥንዶቹ ወደ አሜሪከ ሸሹ።አገዛዙ "እንደማይፈልጋቸው" በማመን መሸሻቸውን ለዋሽንግተን ፖስት በ2016 በሰጡት ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል።
ጥንዶቹ የፈሩት ያለ ምክንያት አይደለም። ኪም ጆንግ ኡን ሥልጣን ሲይዙ አጎታቸውን ያስገደሉ ሲሆን፣ ታላቅ ወንድማቸውም ማሌዥያ ውስጥ ተገድሏል።
ኮ የሞቱት ከኪም ጆንግ ኢል ቀድመው ነው። ፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ ሕይወታቸው ሲያልፍ በሰሜን ኮሪያ መገናኛ ብዙኃን ምንም አልተባለም።
ኪም ጆንግ ኡን የቤተሰባቸውን ጉዳይ በምሥጢር መያዝ ስለሚፈልጉ ልደታቸው እንደ ብሔራዊ ክብረ በዓል አይከበርም።
አያታቸው እና አባታቸው ልደታቸውን ብሔራዊ ክብረ በዓል አድርገዋል።
ኪም ጆንግ ኡን የልደታቸውን ቀን ካነሱ ስለ እናታቸው መናገራቸው አይቀርም። ስለ እናታቸው ካወሩ ደግሞ ከፒዮንግያንግ ውጭ ማደጋቸው አይሸሸግም።
እውነታውን ይፋ ካወጡ አስተዳደራቸው ላይ ጥያቄ እንደሚነሳ አጥኚዎች ይናገራሉ።
ኪም ጆንግ ኡን መሪ ቢሆኑም የቤተሰባቸው መደብ በማኅበራዊ መዋቅሩ አናሳ አድርጎ እንደሚያሳያቸው የቀድሞው ዲፕሎማት ይናገራሉ።
ዶ/ር ቼዎንግ በበኩላቸው ኪም ጆንግ ኡን ቤተሰባቸውን በምሥጢር ይዘው ባለቤታቸው ሪ ሶል ጁን ለሕዝብ ማስተዋወቃቸውን ይናገራሉ። ልጃቸው ጁ አይ በአደባባይ አብራቸው የምትታይ ሲሆን ሥልጣን እንደምትረከብ ይጠበቃል።
የደቡብ ኮሪያ የስለላ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ የቀድሞ ድምጻዊት ባለቤታቸው ከከፍተኛ-መካከለኛ መደብ ነው የተወለደችው።
አንዳንድ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት አባቷ የዩኒቨርስቲ መምህር ነበሩ። ቻይና ውስጥም ክላሲካል ሙዚቃ ማጥናቷም ይነገራል።
ነገር ግን አሁንም ድረስ ኪም ጆንግ ኡን ስለ እናታቸው ይናገሩ ይሆን? የሚለውን ለማወቅ ከባድ ነው።