አሜሪካ የኢራን ግዙፍ የክሪፕቶ መገበያያ ከአብዮታዊ ዘቡ ጋር ግንኙነት አለው በሚል ማዕቀብ ጣለች
አሜሪካ ማክሰኞ ዕለት የኢራን ግዙፍ የክሪፕቶከረንሲ መገበያያ የቴህራን መንግሥት እና ስማቸው በጥቁር መዝገብ ላይ የሰፈሩ ኩባንያዎች የምዕራባውያንን ማዕቀብ ለማለፍ ያገለግላል በሚል ማዕቀብ ጣለች።
ሮይተርስ የዜና ወኪል በግንቦት ወር ኖቢቴክስ (Nobitex) የሚባለው የክሪፕቶከረንሲ መገበያያ ከአገሪቱ ሕጋዊ የገንዘብ ሥርዓት ጋር በትይዩነት ለማዕከላዊ ባንኩ እና ለአብዮታዊ ዘቡ እያገለገለ መሆኑን በመጥቀስ ዘግቦ ነበር።
ዘገባው አክሎም ኖቢቴክስ ኢንተርኔት በተዘጋበት ወቅትም አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን አመልክቶ በሚሊዮን ዶላሮች የሚቆጠሩ ግብይቶችን ማካሄዱን አሳይቷል።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሴንት ማክሰኞ ዕለት ባወጡት መግለጫ “የኢራን ኢኮኖሚ እየተንኮታኮተ ባለበት ወቅት አገዛዙ ለራሱ እኩይ አጀንዳው የዲጂታል መገበያያዎችን ማዕቀብ ለማምለጥ እና ሃብት ከአገር ውጭ ለማሻገር መጠቀም መርጧል” ብለዋል።
የሮይተርስ ዘገባ እንደሚያሳየው ኖቢቴክስ ከኢራናውያን ቤተሰቦች በተገኙ ወንድማማቾች የተመሠረተ ሲሆን፣ ከአዲሱ ጠቅላይ መሪ ጋር ጥብቅ ቁርኝት አላቸው።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ሁለቱ ወንድማማቾች ላይ ማዕቀብ መጣሉን ማክሰኞ ዕለት አስታውቋል።
ኖቢቴክስ ለኢራን መንግሥት “ጠንካራ ድጋፍ” እየሰጠ ነው፤ እንዲሁም ለአብዮታዊ ዘቡ እና ለአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ “በርካታ ቁጥር ያለው” የዲጂታል ግብይቶችን አመቻችቷል ብሏል።
"በኢራን ውስጥ አሜሪካ ጦርነት መክፈቷን ተከትሎ ኖቢቴክስ የኢንተርኔት አገልግሎት ቢቋረጥም የአገዛዙን ሀብት ለመከላከል በኢራን ውስጥ ንብረቶችን እና ገንዘቦችን ለማንቀሳቀስ ሚና ተጫውቷል።"