ቀጥታ, ስፔን በኢራን ጦርነት በሚሳተፉ የአሜሪካ አውሮፕላኖች ላይ የአየር ክልሏን ዘጋች

ስፔን በኢራን ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ የአሜሪካ አውሮፕላኖች በግዛቷ እንዳያልፉ የአየር ክልሏን መዝጋቷን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ እና የመከላከያ ሚኒስትር ማርጋሪታ ሮቤልስ አስታወቁ።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ በእስራኤል ከ6 ሺህ በላይ ሰዎች ሆስፒታል ገብተዋል

    ሆስፒታል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ሁለተኛ ወሩን በጀመረው እስራኤል ከኢራን ጋር ከምታካሂደው ጦርነት ጋር በተያያዘ ከስድስት ሺህ በላይ ሰዎች ለሕክምና ወደ ሆስፒታሎች መወሰዳቸውን የአገሪቱ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

    እስካሁን ሆስፒታል ከገቡት መካከል 121 ሰዎች አሁንም ድረስ ሕክምና እየተደረገላቸው ነው። ከመካከላቸውም አንዱ በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሲሆን 16 ደግሞ ከባድ የሚባል ጉዳት የደረሰባቸው መሆናቸውን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

    ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ደግሞ 232 ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በመላው አገሪቱ ወደ ሆስፒታሎች መሄዳቸውን የእስራኤል ጤና ሚኒስቴር ጨምሮ አሳውቋል።

    እስራኤል ከአሜሪካ ጋር በማበር በኢራን ላይ ጥቃት መክፈቷን ተከትሎ ኢራን በእስራኤል ላይ የአጸፋ ጥቃቶችን እየፈጸመች ትገኛለች።

    በሚሳዔሎች እና በድሮኖች የሚፈጸሙት ጥቃቶች በተለያዩ የእስራኤል አካባቢዎች ውስጥ የሚገኙ ቦታዎችን ዒላማ ያደረጉ ናቸው።

  2. ትራምፕ የኢራንን ኻርግ ደሴት ለምን ይፈልጉታል?

    የኻርግ ደሴት ካርታ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር በቅርብ ስምምነት ላይ የማይደረስ ከሆነ የኻርግ ደሴትን ጨምሮ ሌሎችም ዒላማዎችን እንደሚመቱ አስጠንቅቀዋል።

    ለመሆኑ ኻርግ ደሴት ምንድን ነው?

    ኻርግ ደሴት ከኢራን ባሕር ዳርቻ 28 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። መጠኑ አነስተኛ ቢሆንም በኢራን የነዳጅ እና የጋዝ አቅርቦት ቁልፍ ቦታ የሚሰጠው ነው።

    ከኢራን ድፍድፍ ነዳጅ 90 በመቶው የሚተላለፍበት ሥፍራም ነው።

    ለኢራን ቁልፍ የሆነው በእዚህ ደሴት ላይ የሚፈጸም ጥቃት የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የምጣኔ ሃብት መስመርን ክፉኛ ያናጋል።

    ይህም ጦርነቱን የመቀጠል አቅምን እንደሚያሳጣው የደኅንነት ተንታኝ ሚኬይ ኬይ ይናገራሉ።

    በዚህ ደሴት ላይ የሚፈጸም ጥቃት የኢራንን የነዳጅ ሽያጭ የሚያቃውስ ከመሆኑም ባሻገር አሜሪካ የእግረኛ ጦር እርምጃ ለመውሰድ እንዲቀልላት ያስችላል።

    ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን እንድትከፍት ለማስገደድም አሜሪካ ልትጠቀምበት እንደምትችል ተንታኞች ይናገራሉ።

    ሆኖም ግን የአሜሪካ ዘመቻ ቀላል አይሆንም። እግረኛ ጦር ወደ ደሴቱ እንዲደርስ በባሕር ወይም በአውሮፕላን ረዥም ርቀት መጓዝ ይጠበቅበታል።

    ኢራን በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ለኻርግ ደሴት የምታደርገውን ጥበቃ አጠናክራለች። በርካታ ወታደሮች እና የአየር መከላከያዎች እንደተሰማሩ የሲኤንኤን ምንጮች ገልጸዋል።

    ኻርግ ደሴት ያለውን ቁልፍ ሚና ለመረዳት ይህንን ዘገባ ያንብቡ- አሜሪካ በኢራኗ ኻርግ ደሴት ላይ የፈጸመችው ጥቃት በጦርነቱ ሂደት ላይ ምን ውጤት ይኖረዋል?

  3. ስፔን በኢራን ጦርነት በሚሳተፉ የአሜሪካ አውሮፕላኖች ላይ የአየር ክልሏን ዘጋች

    የስፔን የበረራ መቆጣጠሪያ ማማ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የስፔን የበረራ መቆጣጠሪያ ማማ

    ስፔን በኢራን ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ የአሜሪካ አውሮፕላኖች በግዛቷ እንዳያልፉ የአየር ክልሏን መዝጋቷን የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር ማርጋሪታ ሮቤልስ አስታወቁ።

    ሚኒስትሯ ጨምረውም አሜሪካ በስፔን ግዛት ውስጥ የሚገኙ የጦር ሰፈሮቿን ከኢራን ጦርነት ጋር በተያያዘ ጥቅም ላይ እንዳታውል ማዘዛቸውን እና “ይህንንም ከመጀመሪያው ለአሜሪካ መንግሥት አስታውቀናል” ብለዋል።

    በስፔን ውሳኔ ላይ አሜሪካ እስካሁን አስተያየት ያልሰጠች ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ግን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ስፔን በኢራን ጦርነት ላይ ተቃውሞዋን በማሰማቷ ሙሉ የንግድ ማዕቀብ እንደሚጥሉ ዝተው ነበር።

    በኢራን ላይ ከተከፈተውን ጦርነት ከመጀመሪያው አንስቶ በመቃወም ዋነኛው የሆኑት ስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ አሜሪካንን እና እስራኤልን “ግድየለሽ” እና “ሕገወጥ” በማለት ገልጸዋቸዋል።

    በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስፔን አንዳሉሺያ ግዛት ውስጥ የሚገኙትን ከአሜሪካ ጋር በጋራ የሚያስተዳድሯቸውን ሮታ እና ሞሮን የተባሉ የጦር ሰፈሮችን አሜሪካ እንዳትጠቀም ከልክለዋል።

    የአሁን የአየር ክልል እገዳ ይፋ ከመሆኑ ከቀናት በፊት ከኢራን ጦርነት ጋር በተያያዘ ነዳጅ ጫኝ አውሮፕላኖችን ጨምሮ ሁሉም የአሜሪካ የበረራ ዕቅዶችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውድቅ አድርገዋል።

    አሜሪካ በሌሎች የአገራት ከሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች የሚነሱ ወታደራዊ አውሮፕላኖች በስፔን የአየር ክልል ላይ ማቋረጥ ወይም ለአስቸኳይ ጊዜ ለማረፍ ወሳኝ ነው።

    የስፔን ውሳኔ የአሜሪካ አውሮፕላኖች ተጨማሪ ርቀትን እንዲጓዙ ሊገደዱ ይችላሉ።

  4. ትራምፕ የሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲከፈት ያስቀመጡትን ቀነ ገደብ ያራዘሙባቸው ቀናት

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሆርሙዝ ወሽመጥ በአፋጣኝ የማይከፈት ከሆነ የኢራንን የነዳጅ እና ኤሌክትሪክ ይዞታዎች “እንደሚያጋዩ” እንዲሁም “ሙሉ በሙሉ እንደሚያወድሙ” አስጠንቅቀዋል።

    ፕሬዝዳንቱ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያቸው መሰል ዛቻ ሲያሰሙ የአሁኑ የመጀመሪያቸው አይደለም። ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን እንድትከፍት ያስቀመጡትን ቀነ ገደብ ሲያራዝሙ ቆይተዋል።

    ትራምፕ የሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲከፈት አስቀምጠዋቸው የነበሩ ቀነ ገደቦችን ያራዘሙባቸው ቀናት ዝርዝር የሚከተው ነው፦

    መጋቢት 12/2018 ዓ.ም.፡ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በ48 ሰዓታት ውስጥ እንድትከፍት ጊዜ የሰጡት ትራምፕ ይህ ካልሆነ ግን “የኢራንን የተለያዩ የኃይል ተቋማት መትተን እናወድማለን። የምንጀምረውም ከትልቁ ነው” ብለዋል።

    መጋቢት 12/2018 ዓ.ም፡ ሁለቱ አገራት “በጣም ጥሩ እና ውጤታማ” ንግግር ማድረጋቸውን ተናግረዋል። በኃይል አቅርቦት መሠረተ ልማት ላይ “የሚፈጸም ማንኛውንም ዓይነት ወታደራዊ ጥቃት” ለአምስት ቀናት ማራዘማቸውን ገልጸዋል።

    መጋቢት 17/2018 ዓ.ም፡ ትራምፕ ያስቀመጡትን ቀነ ገደብ በ10 ቀናት እንደሚያራዝሙ አስታውቀዋል። እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት የኢራን መንግሥት ያቀረበውን ጥያቄ ተከትለው መሆኑን ገልጸዋል። ቀነ ገደቡን ወደ መጋቢት 28 አሸጋግረውም ነበር።

    ዛሬ፡ ትራምፕ ከኢራን አዲስ አመራሮች ጋር “ቆፍጠን ያለ ውይይት” ማድረጋቸውን አስታውቀዋል። ውይይቱ “በኢራን እየፈጸምን ያለውን ወታደራዊ ኦፕሬሽን ሊያስቆም ይችላል” ብለዋል። ሆኖም ግን “በአጭር ጊዜ ውስጥ ስምምነት ላይ የማይደረስ ከሆነ አሜሪካ ተወዳጅ ‘ቆይታዋን’ ታገባድዳለች” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

  5. የእስራኤል ነዳጅ ማጣሪያ ላይ በተፈጸመ ጥቃት የእሳት አደጋ ተከሰተ

    በተነሳው የእሳት አደጋ ምክንያት ከነዳጅ ማጣሪያው ጭስ ወደላይ ሲወጣ የሚያሳይ ምሥል ወጥቷል።

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, በተነሳው የእሳት አደጋ ምክንያት ከነዳጅ ማጣሪያው ጭስ ወደላይ ሲወጣ የሚያሳይ ምሥል ወጥቷል።

    ከኢራን የተተኮሰ ሚሳዔል በእስራኤል የአየር መከላከያ ከከሸፈ በኋላ የተፈጠረው ስብርባሪ በነዳጅ ማጣሪያ ተቋም ላይ ማረፉን ተከትሎ የእሳት አደጋ መነሳቱ ተገለጸ።

    ‘ባዛን ኦይል’ የተባለው የእስራኤል ነዳጅ ማጣሪያ ተቋም ውስጥ ዛሬ የነዳጅ ታንከር እና የኢንዱስትሪ ሕንጻ ላይ በሚሳዔል ስብርባሪ ጉዳት ደርሷል።

    በተነሳው የእሳት አደጋ ምክንያት ከነዳጅ ማጣሪያው ጭስ ወደ ሰማይ ሲወጣ የሚያሳይ ምሥል ወጥቷል።

    የአገሪቱ የእሳት እና አደጋ መከላከያ ባወጣው መግለጫ መሠረት በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት የለም። ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው የእሳት አደጋ ሠራተኞች እሳቱ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይስፋፋ እያደረጉ ነው።

    በተቋሙ ውስጥ በተለያየ ቦታ ሆነው በእሳት አደጋው ምክንያት መውጣት ያልቻሉ ሰዎችን ለማትረፍም ርብርብ እየተደረገ ነው ተብሏል።

    ሚሳዔሉ ከየት እንደተተኮሰ ግልጽ አይደለም። ሆኖም ግን ጦርነቱ ከተነሳ ወዲህ ኢራን እና ሄዝቦላህ በእስራኤል ላይ ጥቃት መፈጸም ቀጥለዋል።

  6. ኢራን በሆርሙዝ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን ለማስከፈል ሕግ ልታጸድቅ ነው

    የኢራኑ የፓርላማ አባል (መጅሊስ) አላዲን ቦሩጄርዲ

    የፎቶው ባለመብት, Corbis via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የኢራኑ የፓርላማ (መጅሊስ) አባል አላዲን ቦሩጄርዲ

    የኢራኑ የፓርላማ (መጅሊስ) አባል አላዲን ቦሩጄርዲ ወሳኙን የሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥን በተመለከተ የተዘጋጀውን አዲስ ሕግ "በተቻለ ፍጥነት ይጸድቃል" አሉ።

    በታቀደው “አዲስ አሠራር” መሠረት “ያለ ኢራን ፈቃድ” ምንም ዓይነት ጭነት በሆርሙዝ በኩል እንዲያልፍ እንደማይፈቀድ ቦሩጄርዲ ተናግረዋል።

    ኢራን በባሕረ ሰላጤው ላይ አዲስ የጉዞ ክፍያ ለመጀመር እንደምትፈልግም ተናግረዋል።

    "ደኅንነትን መጠበቅ እና ለሚያልፉ መርከቦች አገልግሎት መስጠት ወጪዎችን የሚጠይቅ በመሆኑ፣ በወሽመጡ በኩል የትራንስፖርት ክፍያ ለመሰብሰብ የሚያስችል ማዕቀፍ መዘርጋት አለበት" ብለዋል።

    ኢራን ከኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች መስፋፋት ጋር በተያያዘ ከፈረመችው ስምምነት የምትወጣበት “ጊዜው ደርሷል” ሲሉም ተናግረዋል።

    እስራኤል እና አሜሪካ በኢራን የኒውክሌር መሳሪያዎች ላይ የፈጸሙት ጥቃትን ተከትሎ በስምምነቱ ውስጥ መቆየት “ተገቢነቱ” እንዳልታያት አስረድተዋል።

  7. የኢራቅ አየር ኃይል በሚሳዔል ተመታ

    ጉዳት የደረሰበት የኢራቅ ጦር አውሮፕላን

    የፎቶው ባለመብት, Iraqi Ministry of Defence

    የምስሉ መግለጫ, ጉዳት የደረሰበት የኢራቅ ጦር አውሮፕላን

    የኢራቅ መከላከያ ሚኒስቴር ሞሐመድ አላ የአየር ኃይል ጦር ሰፈር የሚሳዔሎች ጥቃት እንደተፈጸመበት እና የአገሪቱ አየር ኃይል አውሮፕላን ጉዳት አንደደረሰበት ገለጸ።

    ጥቃቱ ዛሬ ማለዳ በባግዳድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን አጠገብ በሚገኘው የጦር ሰፈር ላይ መፈጸሙን የገለጸው ሚኒስቴሩ የተጎዳ ወይንም የሞተ ሰው የለም ብሏል።

    የኢራቅ መከላከያ ሚኒስቴር በድረገፁ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አውግዞ “ወታደራዊ ተቋም እና የመከላከያ አቅም ላይ ያነጣጠረ የፈሪ እና የወንጀል ድርጊት” ሲል ኮንኖታል።

    ዛሬ ማለዳ የሶሪያ ጦር ከኢራቅ ጋር በሚወሰንበት ድንበር አቅራቢያ በርካታ የድሮን ጥቃቶችን ማክሸፉን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

  8. ስድስት የእስራኤል ወታደሮች ሊባኖስ ውስጥ ጉዳት ደረሰባቸው

    የእስራኤል ጦርን እና ሄዝቦላህ በደቡባዊ ሊባኖስ የሚያደረጉትን ውጊያ ተከትሎ ቴል አቪቭ በአካባቢው ከፍተኛ ድብደባ እየፈጸመች ነው

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ጦርን እና ሄዝቦላህ በደቡባዊ ሊባኖስ የሚያደረጉትን ውጊያ ተከትሎ ቴል አቪቭ በአካባቢው ከፍተኛ ድብደባ እየፈጸመች ነው

    የእስራኤል ጦር ስድስት ወታደሮቹ በተለያየ ጊዜ በሊባኖስ ውስጥ ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታወቀ።

    በደቡባዊ ሊባኖስ በትናንትናው ዕለት ሁለት የእስራኤል ወታደሮች ጸረ ታንክ ከተተኮሰባቸው በኋላ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ጦሩ በሰጠው መግለጫ ገልጿል።

    የእስራኤል መከለከያ አክሎም የተተኮሰ ድሮን በአቅራቢያቸው የወደቀ ሦስት የጦሩ አባላት በተጨማሪ ጉዳት እንደደረሰባቸው እና አንዱ ከፍተኛ ጉዳት ማስተናገዱን ገልጿል።

    በተጨማሪም አንድ ወታደር “በዘመቻ ላይ በተፈጠረ አደጋ” ጉዳት የደረሰበት መሆኑን አስታውቆ ሁሉም ወታደሮች ወደ ሕክምና ተቋም ተወስደዋል ብሏል።

    እስራኤል በሊባኖስ ወታደራዊ ዘመቻ ዳግም የጀመረችው በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ ሮኬቶችን ወደ ሰሜናዊ እስራአል ማስወንጨፉን ተከትሎ ነው።

    ሄዝቦላህ የኢራኑ ጠቅላይ መሪ መገደላቸውን ተከትሎ ለቴህራን ያለውን አጋርነት ለመግለጽ በሚል ሚሳዔሎችን ማስወንጨፍ ጀምሯል።

    እስራኤል ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሊባኖስ ባካሄደችው ዘመቻ ከ1000 በላይ ሊባኖሳውያን መገደላቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል።

    እስራኤል በተጨማሪም ደቡባዊ ሊባኖስን የመቆጣጠር ፍላገት እንዳላት በመግለጽ በሄዝቦላህ ታጣቂዎች ላይ የእግረኛ ጦሯን አሰማርታለች።

    እስራኤል በቤይሩት በፈጸመችው የአየር ድብደባ የወደመ ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, እስራኤል በቤይሩት በፈጸመችው የአየር ድብደባ የወደመ ሕንጻ
  9. የቡድን ሰባት አገራት ሚኒስተሮች የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ላይ ሊወያዩ ነው

    የፈረንሳይ መንግሥት የቡድን ሰባት አገራት ሚኒስቴሮች ዛሬ ተገናኝተው በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ የሚገኘው ጦርነት የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ላይ እንደሚመክሩ አስታወቀ።

    እስራኤል እና አሜሪካ የካቲት 21 2018 ዓ.ም. በኢራን ላይ የከፈቱትን ጦርነት ተከትሎ ቴህራን በባሕረ ሰላጤው የሚገኙ አገራት እና መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ፈጽማለች።

    ይህም በመላው ዓለም የኤነርጂ አቅርቦት በማስተጓጎሉ የነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ ዋጋ ጨምሯል።

    ከዚህም አገር ተያይዞ የምግብ እንዲሁም የአፈር ማዳበሪያ እና ሌሎች ቁሳቁሶች ዋጋ ላይ ጭማሪ ይታያል የሚል ፍራቻ በየአገራቱ እየተስተዋለ ነው።

    የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር በበኩላቸው ዛሬ ከተለያዩ የንግድ ማኅበረሰቦች ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ተገናኝተው በጦርነቱ ተጽዕኖ ዙሪያ እንደሚነጋገሩ ተገልጿል።

    ኪር ስታርመር የሚያገኟቸው የቢዝነስ ማኅበረሰብ አባላት ከፍተኛ የኢነርጂ፣ የመርከብ ጭነት እና የፋይናንስ አገልግሎት ኃላፊዎችን መሆኑ ተጠቅሷል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢራን ጦርነት ዙሪያ በጽህፈት ቤታቸው ከንግድ ማኅበረሰቡ ጋር የሚያደርጉት ውይይት የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት ያስከተለው ኢኮኖሚያዊ ጫናን ያነሳሉ ተብሏል።

    በለንደን የሚገኝ ገበያ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

  10. ትራምፕ በኢራን ለረዥም ጊዜ ሲፈልጓቸው የነበሩ ዒላማዎች መመታታቸውን እና መውደማቸውን ተናገሩ

    እሁድ ዕለት በቴህራን የተፈጸመ ጥቃትን ተከትሎ የተነሳ እሳት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, እሁድ ዕለት በቴህራን የተፈጸመ ጥቃትን ተከትሎ የተነሳ እሳት

    ፕሬዚዳንት ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በኢራን የሚገኙ “በርካታ ዒላማዎች” መውደማቸውን ገለጹ።

    ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ “በኢራን ትልቅ ቀን ነው። ለረዥም ጊዜ ስንፈልጋቸው የነበሩ በርካታ ዒላማዎች በታላቁ፣ በዓለም ላይ ካለው ምርጡ እና አውዳሚው ጦራችን ተመትተዋል፤ ወድመዋል።

    ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ጦሩ በኢራን የሚገኙ ከ9 ሺህ በላይ ዒላማዎችን መደብደቡን ገልጾ ነበር።

  11. ትራምፕ 'ከኢራን ዩራኒየም ለማውጣት' ዘመቻ እያሰቡ ነው - ዎል ስትሪት ጆርናል

    የአሜሪካ ጦር ጄቶች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከኢራን 1,000 ፓውንድ ዩራኒየም ለማውጣት የሚያስችል ወታደራዊ ዘመቻ ለማካሄድ እያሰቡ ነው ሲል ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል።

    ስማቸው ያልተጠቀሱ የደህንነት ባለሥልጣናትን የሚጠቅሰው የዎል ስትሪት ዘገባ፣ ይህ ዘመቻ "የአሜሪካን ወታደሮች ለቀናት ወይም ከዚያ በላይ አገሪቱ ውስጥ ሊያስቆያቸው ይችላል።"

    ትራምፕ እስካሁን ውሳኔ ላይ ባይደርሱም ግን "ባለሥልጣናቱ እንደሚሉት፣ ሃሳቡ በአጠቃላይ ክፍት ነው፣ ምክንያቱም ይህ ሃሳብ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳትሰራ ለመከላከል ያላቸውን ዋና ዓላማ ለማሳካት ይረዳል።"

    ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡት ዋይት ሐውስንና ፔንታጎንን ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።

    ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው ወደ ክልሉ የተሰማሩ ወታደሮች "በኢስፋሃን የኑክሌር ጣቢያ ላይ በኢራን ከፍተኛ የበለፀገችውን ዩራኒየምን ለማነጣጠር በሚደረገው ተልዕኮ ላይ ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ" ነገር ግን እነዚህ ወታደሮች የዃርግ ደሴትን ለመያዝ ወይም የሆርሙዝን የባህር ወሽመጥ ለመጠበቅ ሊያገለግሉ ይችላሉ።

    ኒውዮርክ ታይምስ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ እንደዘገበው ትራምፕ "በኢስፋሃን ውስጥ በሚገኝ ተራራ ስር በብዛት ተከማችተው እንደሚገኙ የሚታመኑ ቦምብ ለማምረት የቀረቡ የኒውክሌር ቁሶችን ለመቆጣጠር እና ለማጥፋት" የሚያስችል ዘመቻ ለማካሄድ "በግልጽ እያሰቡ ነው"።

    ሁለቱም የዜና አውታሮች ዘመቻው ውስብስብ እና ከፍተኛ አደጋ እንደሚኖረው ይጠቁማሉ።

  12. አሜሪካ የኢራን ኻርግ ደሴትን ለመቆጣጠር ያሰበችው ለምንድን ነው?

    የኻርግ ደሴትን የሚያሳይ የሳተላይት ምስል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ትራምፕ ለፋይናንሻል ታይምስ እንደተናገሩት አሜሪካ በኢራን የባሐር ዳርቻ ላይ የምትገኘዋን አነስተኛ ደሴት፣ ኻርግን ልትቆጣጠር ትችላለች።

    አሜሪካ በደሴቲቱ ላይ ዓኗን የጣለችው የአገሪቱ ኢኮኖሚ የደም ስር የሆነው ነዳጅ ዋነኛ መተላለፊያ በመሆኑ ነው።

    አሜሪካ ደሴቲቱን በቁጥጥሯ ስር ብታውል የኢራንን የነዳጅ ሽያጭ ማስተጓጎል ብቻ ሳይሆን ወደ አገሪቱ ሰፋፊ አካባቢዎች ጥቃት ለመፈጸምም ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላታል።

    ደሴቲቱን መቆጣጠር የእስላማዊ ሪፐብሊክ አብዮታዊ ዘብ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ማቋረጥ ያስችላል፤ ይህም ጦርነት ለማካሄድ እንደሚያስቸግረው የደህንነት ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ማይኪ ኬይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    ደሴቲቱን ለመቆጣጠር የሚደረግ ማንኛውም የአሜሪካ ዘመቻ ትንሽ እንደሚሆን ይጠበቃል ያሉት ደግሞ የስኩል ኦፍ ዋር ፖድካስት አቅራቢ አሮን ማክሌን ናቸው።

  13. ትራምፕ በኢራን “የስርአት ለውጥ አድርገናል” አሉ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ ኤርፎርስ ዋን ላይ ሆነው በሰጡት ቃለ ምልስ ወቅት በኢራን የስርዓት ለውጥ ለማምጣት የነበራቸውን ፍላጎት አሳክቻለሁ ብለው እንደሚያምኑ ተናገሩ።

    ባለፈው ሳምንት በተመሳሳይ ለፎክስ ኒውስ “የስርዓት ለውጥ አድርገናል ማለት ትችላለህ ምክንያቱም ሁሉም ተገድለዋል” ብለው ነበር።

    አውሮፕላናቸው ላይ እየተሳፈሩ ለጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ የሰጡት ትራምፕ “በሚገባ ካየኸው ግን የስርዓት ለውጥ አድርገናል፤ ያለው ስርዓት ተመትቷል፤ ወድሟል። ሁሉም ሞተዋል። ቀጣዩም ስርዓትም አብዛኛው ሞቷል። ሦስተኛው ስርዓት ከዚህ በፊት እናነጋግራቸው ከነበሩት በተለየ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ነው እየተወያየን ያለነው፤ እጅጉን የተለየ ቡድን ነው፤ ስለዚህ ያንን የስርዓት ለውጥ አድርጌ እወስደዋለሁ። እውነቱን ለመናገር በጣም ምክንያታዊ ናቸው

    “ስለዚህ የስርዓት ለውጥ ያለ ይመስለኛል። ከዚያ የበለጠ ማድረግ አትችልም" ሲሉ ሃሳባቸውን አጠናክረዋል።

    ትራምፕ ለአንድ ወር በዘለቀው ጦርነት ውስጥ በርካታ የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት መገደላቸውን በመጥቀስም “የነበረው ስርዓት በጣም መጥፎ ነበር፤ ፍጹም ጨካኝ. . . ሁለተኛውም ተሾመ፤ እናም ሁሉም ተወገዱ፤ ሁሉም ሞተዋል፤ በውስጡ ትንሽ ትንፋሽ ከቀረችው በስተቀር” ብለዋል።

    ትራምፕ አክለውም ኢራን ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ላይ ትደርሳለች ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል።

    “ከስምምነት ላይ የምንደርስ ይመስለኛል፤ እርግጠኛ ነኝ፤ ግን ላንደርስ የምንችልበትም ዕድል አለ" ብለዋል።

    “ከኢራን ጋር ምን እንደሚሆን አታውቅም፤ ምክንያቱም እንደራደራለን እና ከዚያ እንደበድባቸዋለን” ሲሉ አክለዋል።

  14. ትራምፕ አሜሪካ “የኢራንን ነዳጅ ዘይት ልትወስድ’ እና ኻርግ ደሴትን ልትቆጣጠር ትችላለች አሉ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ዶናልድ ትራምፕ ለፋይናንሻል ታይምስ “ከኢራን የነዳጅ ዘይት ሊወስዱ” እና ምናልባትም የአገሪቱ ዋነኛ የነዳጅ ማከፋፈያ ኻርግ ደሴትን ሊቆጣጠሩ እንደሚችሉ ተናገሩ።

    “እውነቱን ለመናገር የምፈልገው ከኢራን የነዳጅ ዘይት መውሰድ ነው፤ ነገር ግን በዩኤስ ያሉ አንዳንድ የማይረቡ ሰዎች ‘ያንን ለምን ታደርጋለህ?’ ይላሉ። የማይረቡ ሰዎች ናቸው” ብለዋል።

    ትራምፕ ይህ እርምጃቸው ኻርግ ደሴትን መቆጠጣር ማለት ሊሆን እንደሚችልም ተናግረዋል።

    “ምናልባት ኻርግ ደሴተን እንወስድ ይሆናል። ምናልባትም አይሆንም ይሆናል። በጣም በርካታ አማራጮች አሉን” ሲሉ ለፋይናንሻል ታይምስ ተናግረዋል።

    “ምናልባትም እዚያ [ኻርግ ደሴት] ለተወሰነ ጊዜ እንቆያለን ማለትም ሊሆን ይችላል።”

    በደሴቲቱ ላይ ስላለው የኢራን መከላከያ ጦር ሲጠየቁም “ምንም ዓይነት መከላከያ ያላቸው አይመስለኝም። በቀላሉ ልንወስደው እንችላለን” ሲሉ ተናግረዋል።

    ፕሬዚዳንት ትራምፕ ይህንን ያሉት ተጨማሪ 3ሺህ 500 እግረኛ ጦር በመካከለኛው ምሥራቅ መድረሳቸው ከተነገረ እና በአካባቢው እያደገ የመጣው ውጥረት የአሜሪካ ጦርን ለኢራን ጥቃት የበለጠ እያጋለጠው ይሄዳል የሚል ስጋት ባደገበት ወቅት ነው።

    ትራምፕ በፓኪስታን አማካኝነት ከኢራን ጋር የሚካሄደው ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር በጥሩ ሀኔታ እየሄደ መሆኑን ተናግረዋል። ነገር ግን የተኩስ አቁም ስምምነት በቅርቡ ይደረስ እንደሆን ከመናገር ተቆጥበዋል።

    “ከስምምነት ላይ በፍጥነት ሊደረስ ይችል ይሆናል” ብለዋል።