
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሰኞ ምሽት በተካሄደው የባሎን ዶር ሽልማት ላይ ፈረንሳያዊው እግርኳስ ተጫዋች ኪሊያን ምባፔ የተናገረው በቻይና ማኅበራዊ
ሚዲያ ላይም ትልቅ የውዝግብ ርዕስ ሆኖ ነበር።
ለዚህም መነሻው ምባፔ “በጣም የሚያስቀው” ሜም ምን እንደሆነ በቀልድ ሲናገር የሚያሳየው ቪዲዮ፣ ከቻይናው የቀድሞ መሪ ማኦ ዜዱንግ ምሥል ጋር የሚመሳሰል አንድ የራሱ ምሥል ተጣምሮ የቀረበበት ምሥል መታየቱ ነው።
በዚህም ሳቢያ የቻይና ኩባንያዎች ከምባፔ ጋር ያላቸውን ስምምነት አንድ በአንድ ያቋረጡ ሲሆን የመንግሥታዊ የቴሌቪዥን አካል
የሆነው የቻይና ሚዲያ ቡድን የስፔን ላሊጋ ጨዋታዎችን ሥርጭት እንዲያቋርጥ አድርጓል።
ነገር ግን ከባድ የኢንተርኔት ቁጥጥር በሚደረግባት ቻይና ብዙዎች በእርግጥ ምን እንደተፈጠረ እና ምባፔ ምን እንዳለ
አላወቁም ነበር።
ሁኔታው "የቻይናን ሕዝብ ስሜት ጎድቷል" የሚለው ክስ ብቻ እጅግ ትልቅ ቁጣ ለመቀስቀስ በቂ ምክንያት ሆኖ ቀርቧል።
ይህ ከተፈጠረ በኋላ ብዙም ሳይቆይ፣ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ካሉ ታላላቅ የእግር ኳስ ከዋክብት አንዱ የሆነው ምባፔ፣
አስተያየቱ "ባልተገባ ሁኔታ ተወስዷል" በማለት "ከልብ ይቅርታ" ጠይቋል።
ክለቡ ሪያል ማድሪድ እና የስፔን ከፍተኛ ሊግ ላሊጋም በተመሳሳይ መልኩ ይቅርታ ጠይቀዋል።
ቻይና በዓለማችን በጣም ተወዳጅ ለሆነው የእግር ኳስ ስፖርት ፣ እጅግ ትልቅ ገበያ እንደሆነች ይታወቃል።

የፎቶው ባለመብት, Weibo
የምስሉ መግለጫ, ምባፔ አስቆኛል ያለው ሜም የእሱ እና የቀድሞው የቻይና መሪ ፎቶ አብሮ የቀረበበት ነውሆኖም የቻይና ሚዲያ ቡድን የላሊጋ ጨዋታዎችን ሥርጭት እንደገና መጀመሩን ወይም አለመጀመሩን እስካሁን በይፋ አላሳወቀም።
በበይነመረብ ላይ የተቀሰቀሰው ቁጣም እስከ አሁን አልበረደም።
ምባፔ በቃለ መጠይቁ ውስጥ ማኦን በስም ባይጠራም፣ ብዙዎች የኮሚኒስት ቻይናን መሥራች የሚያካትት ማንኛውም ቀልድ ገደብ ያለፈ እንደሆነ ይሰማቸዋል።
በርካታ ቻይናውያን በቻይና የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ በምባፔ ላይ ቁጣቸውን እየገለጹ ቢሆንም ፈረንሳዊው አጥቂ በትክክል ምን እንደተናገረ አሁንም እየጠየቁ ነው።
ምባፔ ታላቁን የቻይና መሪ በሚያመልክት ሁኔታ ቀልዷል በሚል የተቀሰቀሰውን ቁጣ ሲገልጹ ቻይናውያን የማኦ ዜዱንግን ስም ከመጥቀስ ተቆጥበዋል።
በቻይና ውስጥ በእጅጉ በሚከበሩት ማኦ ላይ መጥፎ ነገር መናገርም ሆነ ማድረግ ከባድ ቅጣትን ያስከትላል። የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫም ሆነ በምባፔ፣ በሪያል ማድሪድ እና በላሊጋ የተሰጡት የይቅርታ መግለጫዎች ማኦን በቀጥታ በስም አልጠቀሱትም።
ከ40 ዓመታት በፊት ያረፉት ማኦ ዜዱንግ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲን በእርስ በርስ ጦርነቱ ወቅት ወደ ድል የመሩ ሲሆን፣ የቻይና ሕዝባዊ ሪፐብሊክንም መሥርተዋል።
በሥልጣን ዘመናቸው “ታላቁ እመርታ” እና “የባህል አብዮት” የመሳሰሉ ዘመቻዎችን ያካሄዱ ሲሆን፣ እነዚህም በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለረሃብ እና ሞት ዳርገዋል።
ቢሆንም ግን ማኦ ዜዱንግ አሁንም በቻይና ውስጥ በከፍተኛ ክብር የሚታዩ ታሪካዊ መሪ ተደርገው ይቆጠራሉ።