ቀጥታ, ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በቅርቡ ካልከፈተች “በጣም ከባድ ጥቃት” ይደርስባታል ሲሉ አስጠነቀቁ

ዶናልድ ትራምፕ የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ "በቅርቡ" ይከፈታል አለበለዚያ ኢራን "በጣም ከባድ ጥቃት ይደርስባታል" ሲሉ ዛቱ። በሁለቱ አገራት መካከል ስምምነት ሊፈረም ይችላል የሚለው ተስፋ እየጨመረ በመጣበት በአሁኑ ወቅት የዓለም ነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ቅናሽ አሳይቷል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. አሜሪካ በኢራን ጦርነት ረዥም ርቀት የሚወነጨፉ ሚሳዔሎቿን ተጠቅማ ጨርሳለች ተባለ

    የአሜሪካ ወታደር መሣሪያ እየጫነ

    የፎቶው ባለመብት, Centcom/Reuters

    አሜሪካ ከኢራን ጋር በምታደርገው ጦርነት ረዥም ርቀት የሚወነጨፉ እና ዒላማቸውን ለይተው የሚመቱ ሚሳዔሎቿን ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ መጠቀሟን ሁለት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ምንጮችን ጠቅሶ በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ዘገበ።

    ምንጮቹ አክለውም አሜሪካ ዒላማቸውን ለይተው የሚመቱ እና ዘመናዊ ምድር ለምድር የሚወነጨፉ የሮኬት ሚሳዔሎቿን ተጠቅማለች ብለዋል።

    አሜሪካ ያሏትን የረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳዔሎቿን በሙሉ ተጠቅማ ማጠናቀቋን ቀድሞ የዘገበው ሮይተርስ የዜና ወኪል ነው።

    ሲቢኤስ ከዚህ ቀደም የረዥም ርቀት ሚሳዔሎች እና ከምድር ወደ ኤር ተምዘግዝገው ዒላማቸውን በመለየት የሚመቱ መሣሪያዎች ክምችት በመቀነሱ የትራምፕ አስተዳደር ከኢራን ጋር የምታደርገውን ጦርነት ለማቆም መገደዱን ዘግቦ ነበር።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናት በመጋዘን ውስጥ የሚገኙት ዒላማቸውን ለይተው የሚመቱ እና ዘመናዊ ምድር ለምድር የሚወነጨፉ የሮኬት ሚሳዔሎች ቁጥር ውስን መሆኑን ገልፀዋል።

    ባለሥልጣናቱ አክለውም ፓትሮይት እና ተርሚናል ሃይ አልቲትዩድ ኤሪያ ዲፌንስ (ቲኤችኤኤዲ) የሚባሉት መሳሪያዎች በፍጥነት አምርቶ መተካት አንደማይቻል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

    ሐምሌ ወር ላይ አንድ የምርምር ቡድን ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት አሜሪካ 2330 ፓትሮይት ሚሳዔሎች የነበራት መሆን ገልጾ በሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ ግን ከ827 እስከ 759 መካከል ብቻ ቀርተዋታል ብሏል።

    ይኸው ጥናት ከጦርነቱ በፊት 452 ቲኤችኤኤዲ የተባለው መሣሪያ እንደነበራት አስታውሶ በሐምሌ ወር መጨረሻ ግን ከ278 እስከ 234 ባለው ውስጥ ብቻ እንደቀራት መዝግቧል።

    ሌላ በቅርቡ ይፋ የሆነ ጥናት አሜሪካ ያሏትን የመሣሪያ ክምችቶች ከጦርነቱ በፊተ ወደነበረው ለመመለስ እስከ 2029 አጋማሽ ድረስ እንደሚወስድባት ይፋ አድርጓል።

    የፔንታጎን ቃል አቀባይ ሼን ፓርኔል ለሲቢኤስ ኒውስ በሰጡት ምላሽ “የአሜሪካ ጦር በዓለም ላይ ከፍተኛ አቅም ካላቸው መካከል ነወ። ፕሬዚዳንቱ ባዘዙ ሰዓት የሚሰጠውን ተልእኮ ለመፈጸም የሚያስችል አቅም አለው” ብለዋል።

    አክለውም “ውጤታማ ዘመቻዎችን አድርገናል” በማለት “ሕዝባችንን እና ፍላጎታችንን ለመከላከል የሚያስችል በቂ መሣሪያ ታጥቀናል” ብለዋል።

    ከዚህ ቀደም የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር የሆኑት ፒት ሄግሴት የጦሩ የመሣሪያ ክምችት ቀንሷል የሚለውን አስተያየት ውድቅ አድርገው ነበር።

  2. ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በቅርቡ ካልከፈተች “በጣም ከባድ ጥቃት” ይደርስባታል ሲሉ ትራምፕ አስጠነቀቁ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ዶናልድ ትራምፕ የሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ "በቅርቡ" ይከፈታል አለበለዚያ ኢራን "በጣም ከባድ ጥቃት ይደርስባታል" ሲሉ ዛቱ።

    በሁለቱ አገራት መካከል ስምምነት ሊፈረም ይችላል የሚለው ተስፋ እየጨመረ በመጣበት በአሁኑ ወቅት የዓለም ነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ቅናሽ አሳይቷል።

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እና የገንዘብ ሚኒስትሩ ስኮት ቤሴንት መርከቦች ከዚህ ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ በወሽመጡ በኩል ያለ ምንም ችግር ማለፍ እንዲችሉ የሚያደርግ ውይይት መካሄዱን እና አንዳንድ ለውጦች መታየታቸውን ከገለጹ በኋላ ፕሬዝዳንቱ ለፎክስ ኒውስ ቃለ መጠይቅ ሰጥተዋል።

    የዓለም ነዳጅ አቅርቦት ሊሻሻል እንደሚችል ዜና ከተሰማ በኋላ የአንድ በርሜል የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በ5 በመቶ ገደማ ቀንሶ 80 ዶላር (60 ፓውንድ) ተሽጧል።

    ነገር ግን ባለፉት ወራት የተደረጉት ውይይቶች ግጭቱን ለማርገብ አለመቻላቸው የነዳጅ ገበያው እንዲዋዥቅ አድርጎታል፣ በዚህም ምክንያት አሽከርካሪዎች በነዳጅ ዋጋ መጨመር ተጎድተዋል።

    ትራምፕ ትናንት በካሊፎርኒያ ጉብኝት እያደረጉ በነበረበት ወቅት "በጣም ጥሩ ውይይት እያደረግን ነው" ሲሉ ኢራን ለወራት የዘለቀውን ግጭት ለማስቆም ስምምነት ላይ ለመድረስ ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) "በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ ደቡባዊ ክፍል ባለው ዓለም አቀፍ የውሃ መስመር በኩል ለማለፍ ለሚፈልጉ የንግድ መርከቦች ሁሉ ነፃ እና ክፍት ነው" ብሏል።

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከኢራን እና ኦማን ጋር ተጨማሪ መርከቦችን በባሕረ ሰላጤው ውስጥ ስለማሳለፍ የሚደረጉት ውይይቶች ለውጥ መታየት ጀምረዋል ሲሉ ተደምጠዋል።

    ማርኮ ሩቢዮ ለጋዜጠኞች “በእነዚያ ውይይቶች ላይ መሻሻሎች ታይቷል፤ ግን እስካሁን የመጨረሻ ውሳኔ ላይ አልደረስንም። ይህ በቅርቡ እንደሚከናወን ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ ተናግረዋል።

    ቤሴንት በበኩላቸው የሆርሙዝን የባሕር ወሽመጥ እንደገና ለመክፈት የሚያስችል ስምምነት ማክሰኞ ወይም ረቡዕ ሊደረስ ይችላል ሲሉ ተደምጠዋል።

    "ዛሬ [ማክሰኞ] ወይም ነገ [ረቡዕ] ወሽመጡን ለመክፈት እና ግጭቱን አርግቦ ወደ መደበኛ ሁኔታ ለመሸጋገር ስምምነት ላይ ልንደርስ እንችላለን" ሲሉ ለሲኤንቢሲ ተናግረዋል።

    ኢራን በወሽመጡ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን ቀረጥ እንድታስከፍል ይፈቀድ እንደሆን ተጠይቀው "የመንቀሳቀስ ነፃነት ይሆናል" ሲሉ መልሰዋል።

    የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ድርድር እየተካሄደ መሆኑን ቢገልጹም፣ሊፈረም የሚችለው ስምምነት ምን ሊመስል እንደሚችል ዝርዝር መረጃ አልወጣም።

    ኢራን ከአሜሪካ ጋር ድርድር እንዳልተቀመጠች እንዲሁም ምንም ዓይነት ዕቅድ እንደሌላት ገልጻ በምትኩ ከኦማን ጋር እየተነጋገረች መሆኑን አስታውቃለች።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ በኩል ለሚያልፉ መርከቦች አዲስ አሰራር መዘርጋትን በተመለከተ ከኦማን ጋር የተደረጉት ውይይቶች አዎንታዊ ነበሩ ብለዋል።

    በዋሽንግተን እና ቴህራን መካከል ቁልፍ አሸማጋይ የሆነችው ኳታር ከሌሎች አደራዳሪዎች ጋር በመሆን ለጦርነቱ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ለማግኘት ጥረት እያደረገች መሆኑን ገልጻለች። ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ምንም ዓይነት ቀጥተኛ ውይይት እንዳልታቀደች አስታውቃለች።

    ግጭቱ እየገፋ ሲሄድ አሜሪካ ዒላማውን ለይቶ የሚመቱ የረጅም ርቀት ሚሳኤሎቿን ክምችት በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ ተጠቅማለች ሲሉ ለጉዳዩ ቀጥተኛ ቅርበት ያላቸው ሁለት ምንጮች ለቢቢሲ የአሜሪካ የዜና አጋር ሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል በሚደረገው ድርድር ማዕከላዊ ነጥብ ነው።

    ግጭቱ በየካቲት ወር መጨረሻ ከመጀመሩ በፊት በወሽመጡ በኩል አንድ አምስተኛ የሚሆነውን የዓለም አቀፍ የነዳጅ እና ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦቶችን ይጓጓዙ ነበር።

  3. የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመክፈት የሚያስችል ስምምነት ከኢራን ጋር ረቡዕ ሊፈረም ይችላል ተባለ

    የአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ስኮት ቤሴንት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አሜሪካ እና ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመክፈት የሚያስችል ስምምነት ዛሬ ማክሰኞ ወይንም ረቡዕ ዕለት ሊፈራረሙ እንደሚችሉ የገንዘብ ሚኒሲትሩ ስኮት ቤሴንት አስታወቁ።

    ቤሴንት ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ቃለ ምልልስ ወቅት ከስምምነት ላይ ከተደረሰ የንግድ መርከቦች በነጻነት መንቀሳቀስ ይችላሉ ብለዋል።

    የገንዘብ ሚኒስትሩ ለሲኤንቢኤስ እንደተናገሩት “ከኢራናውያን ጋር እየተነጋገርን ነው፤ ወሽመጡን ለመክፈት እና ግጭቱን ለመቀነስ ዛሬ ወይንም ነገ ከስምምነት ላይ የመድረስ ዕድል አለን” ብለዋል።

    ኢራን በወሽመጡ ከሚያልፉ መርከቦች ቀረጥ መሰብሰብ ይፈቀድላት እንደሆን ተጠይቀው ሲመልሱ “በነጻነት መንቀሳቀስ ሊሆን ይችላል” ብለዋል።

    ቤሴንት በፐርዢያ ባሕረ ሰላጤ ቆመው የሚገኙ በሺህዎች የሚቆጠሩ መርከቦች ማለፍ ከቻሉ የዓለም ነዳጅ ዋጋ በፍጥነት እንደሚቀንስ ተናግረዋል።

    "ጉዳዩ የኤነርጂ ብቻ አይደለም፤ ማዳበሪያን፣ የተጣሩ ምርቶችን እና የተለያዩ የኢንዱስትሪ ጋዞችንም ያካትታል" ብለዋል።

    "የእነዚህ ምርቶች ዋጋ ሲቀንስ ግዙፍ የተረጋጋ የንግድ እንቅስቃሴ ልናይ እንችላለን።"

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት ሆርሙዝን እንደገና ለመክፈት የሚያስችል ድርድር እንዲኖር በማሰብ በኢራን ላይ ሊያደርጉት የነበረውን ከፍተኛ ጥቃት ሰርዘዋል።

    ትራምፕ ከዚህ ቀደም ግጭቱን ለመፍታት የሚያስችል ስምምነት እንደሚኖር በተደጋጋሚ ቢጠቁሙም፣ ከቴህራን ጋር ያለው ውጊያ ግን እንደገና እየተባባሰ መምጣቱ ይታወሳል።

    አሜሪካ እና ኢራን ሰኔ 10 2018 ዓ.ም. የሆርሙዝ ወሽመጥን የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመው ነበር።

    ስምምነቱ ከመፍረሱ በፊት የተወሰኑ የንግድ መርከቦች መተላለፍ ችለው ነበር።

    በሁለቱ አገራት መካከል የሚካሄደው ጦርነት ዳግምበማገርሸቱ በወሽመጡ በኩል የሚያልፉ መርከቦች ተስተጓጉለዋል።

  4. ኳታር በኢራን እና አሜሪካ መካከል የሚደረገው ንግግር ለውጥ ማሳየቱን ገለጸች

    ኢራን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ኳታር አደራዳሪዎች በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም በሚያደርጉት ጥረት ውጤት እያገኙ መሆናቸውን አስታወቀች።

    ኳታር ይህንን ካለች በኋላ የዓለም ነዳጅ ዋጋ በፍጥነት ቅናሽ አሳይቷል።

    ትራምፕ ሰኞ ዕለት ከቴህራን ጋር ንግግር መጀመሩን ተናግረው ኢራን ከእውነተኛ ስምምነት ላይ ለመድረስ ይህ “የመጨረሻ ዕድሏ” ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    የኢራን ባለሥልጣናት ግን ከአሜሪካ ጋር ምንም ዓይነት ድርድር እየተካሄደ አለመሆኑን በመናገር ያስተባብላሉ።

    ቴህራን ከኦማን ጋር በሆርሙዝ ወሽመጥን በሚመለከት እየተነጋገረች መሆኗን በመግለጽ በዚህ ሳምንት ሌላ ምንም ዓይነት ውይይት እንደሌለ ጠቅሳለች።

    ትራምፕ ሰኞ ዕለት በኦቫል ኦፊስ ለተገኙ ጋዜጠኞች “ድርድሩ እየተካሄደ ነው” ብለው ንግግሩ የተጀመረው በኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ እና ኳታር ጥያቄ መሠረት መሆኑን አስታውቀዋል።

    “ስምምነቱን ለመፈረም ይህ [ለኢራን] የመጨረሻ ዕድል ነው" ብለዋል።

    የኳታር ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማጄድ አል አንሳሪ ዲፕሎማቶች “በጣም ጥሩ ደረጃ” ላይ ደርሰዋል ብለዋል።

    አንሳሪ ማክሰኞ ዕለት ኳታር፣ ፓኪስታን እና ኦማንን ጨምሮ አደራዳሪዎች በዋሺንግተን እና ቴህራን መካከል ረቂቅ የሰላም ዕቅድ ለማለዋወጥ እየሠሩ መሆኑን አብራርተዋል።

    አንድ ከፍተኛ የፓኪስታን ባለሥልጣን “ከጀርባ ብዙ ነገር እየሆነ ነው. . . ሁለቱም ወገን እያነጋገርን ነው። አሁን ዋነኛ ግባችን ሁለቱም አካላት ቢያንስ ንግግር እንዲጀምሩ ማድረግ ነው” ብለዋል።

    ትራምፕ እሁድ ዕለት ከቴህራን ጋር ንግግር እንደተጀመረ በመጥቀስ ለመፈጸም አስበውት የነበረውን “መጠነ ሰፊ ጥቃት” መሰረዛቸውን ተናግረዋል።

  5. የኢራን ፕሬዝዳንት ከሥልጣን ስለመልቀቃቸው የተሰራጨውን ዘገባ አስተባበሉ

    የኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን

    የኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ከአሜሪካ ጋር እየተባባሰ ባለው ወታደራዊ ውጥረት መካከል የሥልጣን መልቀቂያ አቀረቡ ተብሎ የተሰራጨውን ዘገባ አስተባበሉ።

    ፕሬዝዳንቱ በቴሌቭዥን በተላለፈ ማብራሪያቸው "ከኃላፊነት የምለቅ ከሆነ ለሕዝብ አሳውቃለሁ። ከሥልጣን አለቅቅም ትግሉን እቀጥላለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።

    ፕሬዝዳንቱ​ ከከፍተኛው መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ እና ከጦር ኃይሎች ጋር አለመግባባት ተፈጠረ የሚሉትን ዘገባዎች አስተባብለው፣ “በሙሉ ስምምነት እና ቅንጅት እየሠራን ነው” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።

    ​“ማንኛውም አለመግባባት ቢፈጠር እንኳን የጦር ኃይሉ ከኻሜኒ ጎን እንደሚቆም ሁሉም ያውቃል” ሲሉ ተደምጠዋል። የኢራን ተቃዋሚ የመገናኛ ብዙኃን ከዚህ ቀደም ፔዜሽኪያን ለኻሜኒ የሥልጣን መልቀቂያቸውን በተደጋጋሚ አቅርበዋል ሲሉ ዘግበው ነበር።

    ዋሽንግተን እና እስራኤል በቴህራን ላይ የጋራ ጥቃት ካደረሱበት ከየካቲት ወር ጀምሮ ኢራን ከአሜሪካ ጋር በግጭት ውስጥ ትገኛለች።

    ኢራን የአሜሪካ ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት ባላቸው የባህረ ሰላጤው አገራትን በድሮን እናበሜሳይል በመደብደብ የአፀፋ ምላሽ ስትሰጥ ቆይታለች።

    አሜሪካእና ኢራን በሚያዚያ ወር ላይየተኩስ ማቆም ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።

    ሁሉቱ ሀገራት ጦርነት ለማስቆም እና ዘላቂ የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ በፓኪስታን አሸማጋይነት የተዘጋጀ የመግባቢያ ሰነድ በሰኔ ወር ተፈራርመው እንደነበር አይዘነጋም።

    ሆኖም ስምምነቱ ባለፈው ወር የፈረሰ ሲሆን፣ ግጭቱን ለመፍታት ንግግሮች እየተደረጉ ነው በሚሉ ዘገባዎች መካከል የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕየቦንብ ድብደባውን በድንገት ከማቆማቸው በፊት ሁለቱ ሀገራት ለሁለት ሳምንታት ያህል ጥቃት ተለዋውጠዋል።

  6. የየመን ሁቲዎች የሳዑዲ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ጥቃት ፈጽመናል አሉ

    የመን ተጣቂዎች በመኪና ላይ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የሁቲ ቃል አቀባይ የሳዑዲ አረቢያ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን አስታወቁ።

    የየመን ታጣቂዎች ማክሰኞ ዕለት በደቡባዊ ሳዑዲ አረቢያ የሚገኘው በናጅራን አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የድሮን ጥቃት መፈጸማቸውን ገልጸዋል።

    የሁቲዎች ወታደራዊው ቃል አቀባይ የሆኑት ያህያ ሳሬ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጥቃቱ ዒላማውን መምታቱን ተናግረዋል።

    የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት እስካሁን ድረስ ሁቲዎች ፈጸምነው ስላሉት ጥቃት ያሉት ነገር የለም።

    የሁቲ ቃል አቀባይ የሳዑዲ ድሮኖች የየመን ግዛቶች በሆኑት ሳዳ እና ሃጃህ አየር ክልል ላይ ጥሰው በመግባታቸው የአጸፋ ምላሽ መስጠታቸውን ተናግረዋል።

    ሳሬ ወደፊት የመንን አየር ክልል ጥሶ መገኘት “ምላሽ ሳይሰጠው እና ቅጣት ሳይቀበሉ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም” ብለዋል።

  7. በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ የተጋረጠው ስጋት መባባሱን ተንታኞች ተናገሩ

    መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በአሁኑ ወቅት የተጋረጠቸባው ስጋት የኢራን ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ ከታዩት የከፋው መሆኑን ባለሙያዎች ተናገሩ።

    ባለሙያዎቹ ይህን ያሉት ሌላኛው ወሳኝ የቀጣናው የባሕር መስመር በሆነው ቀይ ባሕር ላይ ድንገተኛ ጥቃቶች ከተፈፀሙ በኋላ ነው።

    ቀይ ባሕር ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ከዘጋች በኋላ አንዳንድ መርከቦች ሲጠቀሙበት የነበረ አማራጭ መሥመር ነው።

    የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የሆርሙዝ ወሽመጥን እንደገና ለመክፈት ከኢራን ጋር ንግግር እየተደረገ ነው ቢሉም ኢራን ይህንን አስተባብላለች። ይሁን እንጂ የመስመሩን ደኅንነት ለማስጠበቅ ከኦማን ጋር እየተነጋገረች እንደሆነ ገልጻለች።

    ኬፕለር በተባለው የመርከቦችን እንቅስቃሴ የሚከታተል ተቋም ተንታኝ የሆኑት ማቲው ራይት ፣ “የድፍድፍ ነዳጅ ንግድ ቀውሱ ከጀመረ ወዲህ እጅግ አስከፊው ጊዜ ላይ ይገኛል” ብለዋል።

    በኢራን እና በአሜሪካ መካከል ዳግም ግጭት ከተቀሰቀሰ አስንቶ በወሽመጡ የሚያልፉ መርከቦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።

    ቅዳሜ ዕለት በሆርሙዝ ወሽመጥ ያለፉት መርከቦች ቁጥር 11 ሲሆኑ እሑድ ማለፍ የቻሉት ስምንት መርከቦች ብቻ ናቸው።

    እንደ ኬፕለር ከሆነ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በቀን ከ100 በላይ መርኮቦች ያልፉ ነበር።

    20 በመቶ የሚሆነው የዓለም ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ በወሽመጡ በኩል ነበር የሚተላለፈው።

    ሰኔ ወር ላይ በኢራን እና በአሜሪካ መካከል የተደረሰው ጊዜያዊ ስምምነት የመርከቦቹን ቁጥር ከፍ አድርጎት የነበረ ቢሆንም ግጭቱ ዳግም ከተቀሰቀሰ በኋላ እንቅስቃሴው እንደገና በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።

    በርካታ መርከቦችም በቀላሉ እንዳይለዩ ወሽመጡን በሚያቋርጡበት ጊዜ መልዕክት መቀበያ እና ማስተላለፊያ መሣሪያቸውን (ሲግናላቸውን) ለማጥፋት ተገደዋል።

    ከሳዑዲ አረቢያ ነዳጅ የጫኑ አንዳንድ መርከቦች አማራጭ በሆነው እንዲሁም ሳዑዲ እና ሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ መካከል በሚገኘው የቀይ ባሕር መስመር አልፈዋል።

    ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የየመን ሁቲ ተዋጊዎች በሳዑዲ መርከቦች ላይ በፈፀሟቸው ድንገተኛ ጥቃቶች ምክንያት ስጋቱ ተባብሷል።

    የሁቲ አማጺያን የሳዑዲ መርከቦች በቀይ ባሕር ላይ እንዳይንቀሳቀሱ እገዳ መጣሉን ከሁለት ሳምንት በፊት ያስታወቀ ሲሆን የዩናይትድ ኪንግደም የባሕር ትራንስፖርት ተቋም ባለፈው ሳምንት በርካታ ጥቃቶች መፈፀማቸውን ገልጿል።ተጨማሪ ያንብቡ፦ ኢራንን በመደገፍ በቀይ ባሕር ላይ መርከቦችን እንደሚያጠቁ ያሳወቁት የየመን ሁቲዎች እነማን ናቸው?

  8. ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአሁኑ ድርድር ኢራን “ ጥሩ ሰነድ መፈረም የምትችልበት የመጨረሻው ዕድል ነው” አሉ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ከቴህራን ጋር 'ድርድር ተጀምሯል' በሚል አቋማቸው የጸኑት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ አሁን የሚደረገው ንግግር ኢራን “ጥሩ ሰነድ መፈረም የምትችልበት የመጨረሻው ዕድል” መሆኑን ተናገሩ።

    ኢራን በበኩሏ በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚደረግ የመርከብ ጉዞን ለማስጀመር የሚያስችል ጊዜያዊ መስመርን በተመለከተ ከኦማን ጋር እየተደራደረች መሆኑን አስታውቃለች።

    ቴህራን ይህንን ያስታወቀችው ፕሬዝዳንት ትራምፕ የኢራንን ጦርነት ለመቋጨት የሚካሄደው ንግግር ሰኞ ዕለት እንደሚጀመር እና ለድርድርሩ ሲባል አገሪቱ ላይ ሊፈጸም የነበረ "ከባድ" ጥቃት እንዲቆም ማድረጋቸውን ከገለጹ በኋላ ነው።

    ትራምፕ ድርድሩ ላይ የትኛዎቹ አካላት እንደሚሳተፉ በግልጽ አልተናገሩም። ኢራን ግን ከአሜሪካ ጋር እየተደራደረች እንዳልሆነ፣ ለድርድር የመቀመጥም እቅድ እንደሌላት ገልጻለች።

    ኢራን ተሳትፎ እንደሌላት መግለጿ የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ያስቆጣ ይመስላል። ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ የኢራን አመራር "ለማመን በማይቻል ደረጃ ቀጣፊ ነው” ሲሉ ዘልፈዋል።

    ቆይቶም በዋይት ሀውስ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ንግግሩ እየተካሄደ ነው በሚለው አቋማቸው ጸንተው ታይተዋል።

    “እየተነጋገርን ካልሆነ ስትጠይቁኝ ‘እየተነጋገርን አይደለም’ እላለሁ። ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት እየተነጋገርን ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

    “እየተነጋገርን ያለነውም በኢራን ጥያቄ ነው" ያሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኳታር፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና "በርካታ አገራት" ለድጋፍ እንደሚያደርጉ አንስተዋል።

    እነዚህ አገራት ለኢራን “የመጨረሻ ዕድል” መስጠት እንደሚፈልጉ ተናግረዋም። ኢራኖች “ጥሩ ሰነድ መፈረም የሚችሉበት የመጨረሻ ዕድል ይህ ነው" ብለዋል።

    አሜሪካ ኢራን ለመውሰድ ካቀደችው እርምጃ ከመተግበሯ በፊት የቀረበ “የመጨረሻ ዕድል” መሆኑንም አክለዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የስምምነቱን “ወሰኖች” በተመለከተ ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረው ነበር።

    የሚደረገው ስምምነት በኢራን የተዘጋው እና የነዳጅ ዋጋ እንዲንር ምክንያት የሆነው ሆርሙዝ ወሽመጥ መልሶ እንዲከፈት እንደሚያደርግም ጠቅሰዋል።

    ትናንት ሰኞ ቴህራን ውስጥ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኤል ባጋይ ግን አገሪቱ ከአሜሪካ ጋር ንግግር እያደረገች አለመሆኑን ተናግረዋል።

    ይሁን እንጂ በሆርሙዝ ወሽመጥ ደኅንነቱ የተጠበቀ ጉዞ እንዲደረግ የሚያስችል “ጊዜያዊ የባሕር መጓጓዣ መስመር” የሚመሠረትበትን መንገድ በተመለከተ ከኦማን ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ገልጸዋል።

    ትራምፕ ድርድር እየተካሄደ መሆኑን በድጋሚ ከተገናሩ በኋላ በዓለም አቀፍ ገበያ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ መለኪያ የሆነው ብሬንት ዋጋው በ4.5 በመቶ ወርዶ በበርሜል 83.98 ዶላር ተሽጧል።

  9. የአሜሪካ ጦር ኢራንን ለመቅጣት “ያልተለመዱ ሐሳቦች” እንዳሉት ተዘገበ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, AP

    የአሜሪካ ጦር ኢራንን ለመቅጣት እና ጫና ለማሳደር “በፈጠራ የተሞሉ እና ያልተለመዱ” ሐሳቦችን እየተመለከተ እንደሚገኝ ሲኤንኤን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮችን ጠቅሶ ዘገበ።

    በአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) አመራር የሆኑ የሲኤንኤን ምንጭ እንደጠቆሙት፤ “ኢራን ላይ ጫና ለማሳደር እና ለመቅጣት አዳዲስ መንገዶች እየተመለከትን ነው” የሚል ኢሜል ተልኳል።

    የአሜሪካ ጦር ስትራቴጂውን መለወጥ ስላለበት ሁሉንም ዓይነት መንገዶችን እየተመለከተ መሆኑን ሌላ የሲኤንኤን ምንጭ ጠቅሰዋል።

    የአሜሪካ ጦር ሐሳቦች በኢሜል እንዲላኩለት መጠየቁ የተለመደ አሠራር እንዳልሆነ ወታደራዊ ባለሥልጣን መናገራቸው በዘገባው ተጠቅሷል።

    የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ ቃል አቀባይ ብራድ ኩፐር በበኩላቸው “በፈጠራ የተሞሉ መንገዶች ማሰብ እና መተግበር በጦሩ ታሪክ የተለመደ ነው” ብለዋል።

    “ከፍተኛ የኦፕሬሽን ውጤት ለማግኘት” በየትኛውም ወታደራዊ ማዕረግ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ወታደሮች ሐሳብ እንደሚሰበስቡ ገልጸዋል።

    የሲኤንኤን ምንጭ “በስተመጨረሻ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ስምምነት ላይ መድረስ ይፈልጋሉ። ስለዚህም ጫና ማሳደሪያ እና ከዚህ ሁኔታ መውጫ መንገድ ይፈልጋሉ። አንዳንዴ የተለመደው አካሄድ ሲሟጠጥ በፈጠራ የተሞላ አስተሳሰብ ያስፈልጋል” ብለዋል።

  10. የፍርድ ሒደት እየተካሄደ ሳለ የሱዳን ጦር ባደረሰው የድሮን ጥቃት 35 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

    የሱዳን ሰንደቅ አላማ

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    በሰሜን ሱዳን ዳርፉር ግዛት ባህላዊ የፍርድ ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ሳለ የሱዳን ጦር በፈጸመው የድሮን ጥቃት 35 ሰዎች መገደላቸውን የመብት ተሟጋች ተቋም አስታወቀ።

    ትናንት እሑድ ከሰዓት በተፈጸመው ጥቃት በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን የሱዳን የመብት ተሟጋች ተቋም ገልጿል።

    በንጹኃን ላይ የሚፈጸም ጥቃትን የሚከታተለው ‘ዘ ኢመርጀንሲ ሎየርስ ግሩፕ’ እንዳለው የድሮን ጥቃቱ የተፈጸመው ጋህራ አል-ዛዊያ በተባለ መንደር ነው።

    መንደሩ በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) ቁጥጥር ሥር የሚገኝ ነው። ስለተፈጸመው የድሮን ጥቃት የሱዳን ጦር አስተያየት አልሰጠም።

    አርኤስኤፍ አብዛኛውን የዳርፉር አካባቢ ይቆጣጠራል።

    ለሦስት ዓመታት በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል።

    ኤኤፍፒ ያነጋገራቸው የዐይን እማኝ “የእሑዱ የፍርድ ሥነ ሥርዓት የማኅበረሰብ መሪዎች በተገኙበት ዛፍ ሥር እየተከናወነ ነበር” ብለዋል።

    አራት የጎሳ መሪዎች እና ሁለት የአርኤስኤፍ ኮማንደሮች በጥቃቱ ከተገደሉት መካከል እንደሚገኙበት የዐይን እማኙ ገልጸዋል።

    የግል ሚዲያ የሆነው ዳርፉር 24 ድረ ገጽ አንድ ነዋሪን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ሁለት ድሮኖች በአካባቢው በርረው “ከአራት ሚሳዔል በላይ” ተኩሰዋል።

    የመብት ተሟጋች ቡድኑ የድሮን ጥቃቱን አውግዞ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቋል።

    ንጹኃን ዜጎችን እና መሠረተ ልማትን ዒላማ ማድረግ “ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ጋር የሚጻረር” እንደሆነም ገልጿል።

  11. ኢራን ከአሜሪካ ጋር እየተነጋገርኩ አይደለም አለች

    የአሜሪካ እና የኢራን ባንዲራዎች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ኢራን ሰኞ ዕለት ከአሜሪካ ጋር ምንም ዓይነት ንግግር እያካሄደች አለመሆኗን ገልጻ፣ ከኦማን ጋር በሆርሙዝ ወሽመጥ ደኅንነቱ የተጠበቀ ጉዞ እንዲደረግ የሚያስችል “ጊዜያዊ የባህር መጓጓዣ መስመር” ለመመስረት እየሰራሁ ነው አለች።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኤል ባጋይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ቴህራን ከሙስካት ጋር የምታደርገው ንግግር ቁልፍ በሆነው የባሕር መስመር ላይ ጊዜያዊ የመርከቦች መንቀሳቀሻ ለመመስረት ያለመ ነው ብለዋል።

    ከኢራን መንግሥት ጋር ቅርበት ያለው ፋርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ባጋይ “ከኦማን ጋር የምናደርገው የአሁኑ ውይይት በሆርሙዝ ባህር ወሽመጥ ውስጥ የመርከቦችን ደኅንነቱ የተጠበቀ ጉዞ ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ ነው” ብለዋል።

    “በሆርሙዝ ባህር ወሽመጥ ውስጥ የመርከብ ጉዞ ደኅንነትን ለማረጋገጥ እንዲቻል፣ ከኦማን ጋር በመተባበር በተቻለ ፍጥነት ጊዜያዊ የመተላለፊያ መስመር ለመዘርጋት እየሰራን ነው” ሲሉም አክለዋል።

    ባጋይ በቴህራን እና በዋሽንግተን መካከል ንግግር እየተደረገ ነው የሚሉ ዘገባዎችን ውድቅ በማድረግ “ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ድርድር እያደረግን አይደለም” ብለዋል።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር ሰኞ ከሰዓት በኋላ ውይይት እንደሚጀመር ትናንት እሁድ ተናግረው ነበር። ትራምፕ፣ በሆርሙዝ ጉዳይ እና የኢራንን "ኒውክሌር ማስወገድ" በተመለከተ በቅርቡ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚቻል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል ።

    ባጋይ “አሜሪካ ጥቃቷን እና ክልከላዋን እስከቀጠለች ድረስ [በሆርሙዝ ያለው ሁኔታ ላይ] የሚለወጥ ነገር አይኖርም” ብለዋል።

  12. ዩክሬን የሩሲያን ነዳጅ ማጣሪያ እና አየር ማረፊያ መምታቷን ስትገልጽ፤ ሞስኮ ስምንት ሰዎች መገደላቸውን አስታወቀች

    የዩክሬን ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Zelenskiy / Official

    ዩክሬን ወደ ሩሲያ ግዛት ዘልቃ በመግባት በፈጸመቻቸው ጥቃቶች የአገሪቱን ዋነኛ የነዳጅ ማጣሪያ እና የሩሲያ ስትራቴጂካዊ አቪዬሽን የሚገኝበትን አየር ማረፊያ መምታቷን ገልጻለች።

    ከዩክሬን ድንበር 600 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙት የኤንግልስ አየር ማረፊያ እና የነዳጅ ማጣሪያ መመታታቸውን የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቭሎዲሚር ዜሌንስኪ ተናግረዋል።

    እነዚህ መሠረተ ልማቶች የሩሲያን ጦርነት በገንዘብ ለመደገፍ እንደሚያገለግሉም ጠቅሰዋል። ፕሬዝዳንቱ ኤንግልስ አየር ማረፊያ እና ሳራቶቭ ነዳጅ ማጣሪያንም “ስትራቴጂካዊ ተቋማት” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

    ካሉጋ ግዛት ውስጥ የሚገኝ የነዳጅ ዴፖ እና በብራያንስክ ያለ የድሮን ማስወንጨፊያ ስፍራም ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።

    ሩሲያ በበኩሏ ዩክሬን በፈጸመቻቸው ጥቃቶች ስምንት ሰዎች መገደላቸውን እንዲሁም 635 ድሮኖችን መምታቷን እና መጥለፏን አስታውቃለች።

    በተጨማሪም በሩሲያ ትልቁ የኦንላይን ችርቻሮ ንግድ ኩባንያ የሆነው ‘ዋይልድቤሪስ’ መጋዘን እንደተመታ ተገልጿል።

    በሌላ በኩል ሞስኮ በጥቁር ባሕር የሚገኙ የዩክሬን ወደቦች እና ሁለት መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተናግራለች።

    ዩክሬንም በሰሜን ምሥራቅ ካርኪቭ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ የፖስታ ተርሚናል ላይ በተፈጸመው የሩሲያ ጥቃት አንድ ሰው መገደሉን ገልጻለች።

    በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የሚገኙ ሠፊ የጦር ግንባሮች እንቅስቃሴ ሳይታይባቸው ባሉበት ቢሆኑም፣ ሁለቱም ወገኖች በዋና ዋና ከተሞች፣ በኤነርጂ መሠረተ ልማቶች እና መጋዘኖች ላይ የሚፈጽሟቸውን ጥቃት አጠናክረዋል።

    ጦርነቱን ለመቋጨት በአሜሪካ የሚመራው የሽምግልና ሂደት እስካሁን ድረስ ውጤት አላመጣም።

  13. ትራምፕ ዛሬ ከኢራን ጋር አዲስ ንግግር እንደሚጀመር ጠቆሙ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በኢራን ላይ ሊፈጸም የነበረ “መጠነ ሰፊ” ጥቃት እንዲቀር ማድረጋቸውን ያስታወቁት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ዛሬ ሰኞ አዲስ ንግግር ለመጀመር ከቴህራን ጋር እንደሚቀመጡ ተናገሩ።

    ትራምፕ “ጥቃቱ ምን ያህል ሰፊ እንሚሆን ያውቁታል፤ ምክንያቱም ዐይናቸው ስር የሚሆነው እያዩ ነበር” ሲሉ እሁድ ዕለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። “[ከቴህራን ጋር] በድርድር መልክ እያየተነጋገርን ነው። ነገ [ሰኞ] ከሰዓት በኋላ ይጀምራል።”

    ፕሬዝዳንት ይህንን ከማለታቸው አስቀድሞ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ የድርድሩ "ማዕቀፎች" ላይ ስምምነት በመደረሱ ኢራን እና የመካከለኛው ምሥራቅ አጋሮች ማንኛውን ጥቃት "እንዲቆም" መጠየቃቸውን ጽፈዋል።

    ኢራን ለትራምፕ አስተያየት እስካሁን ምላሽ አልሰጠችም። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጦርነቱ ሊጠናቀቅ የተቃረበበት ጊዜ እንደቀረበ በተደጋጋሚ የተናገሩ ቢሆንም ጥቃት እና የአጸፋ እርምጃዎች ሲፈጸሙ ቆይተዋል።

    ትራምፕ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ ከቴህራን ጋር ስምምነት የሚደረስበትን የጊዜ ገደብ ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

    “ሁኔታው እንዴት እንደሚሄድ እናያለን። በፈለግነው ጊዜ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነን… ሰዎችን መግደል አልፈልግም” ብለዋል።

    ትራምፕ አክለውም የሳዑዲ አረቢያው አልጋ ወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን እንዲሁም የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ኳታር ቅዳሜና እሁድ ጥቃት እንዳይፈጸም ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ተናግረዋል።

    "ሁላችንም ጥቃቱን ለመጀመር ተዘጋጅተን ነበር" ሲሉ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ "አጋሮቻችን ጥቃቱ እንዲዘገይ የጠየቁበት ምክንያት ስምምነት እንዳለ ስለሚያስቡ ነው" ብለዋል። "በሆርሙዝ ላይ ስምምነት አለ፣ እና በኒውክሌር ላይ ስምምነት ይኖራል" ብለዋል።

    ትራምፕ ይህንን ይፋ ካደረጉ በኋላ ሰኞ ጠዋት በእስያ ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ቀንሷል።

    የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ በበርሜል በ4.5 በመቶ ቅናሽ አሳይቶ በ83.98 ዶላር ተሸጧል።

    ኢራን በአሜሪካ እና እስራኤል ለተከፈተባት ጦርነት ምላሽ ስትሰጥ በወሰደችው እርምጃ የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አስመዝግቧል።

    በዓለም ላይ ካለው ድፍድፍ ዘይትና ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ውስጥ 20 በመቶ የሚሆነው የሚመጣው ከባሕረ ሰላጤው አገራት ነው።

    የኢራን የዜና ወኪል የሆነው ሜህር፣ ቴህራን አሜሪካ ተጨማሪ ወታደራዊ እርምጃ እንዳትወስድ ጠይቃለች መባሉን አስተባብሏል። አክሎም የትራምፕ ንግግር "አዲስ ውሸት ብቻ ነው" ብሏል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ እሁድ ዕለት በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ላይ ከኦማን ጋር የተደረገው ድርድር "ወደ መጠናቀቁ እየሄደ ነው" ማለታቸውን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ንግግሩ ሰኞ ዕለት የሚካሄድበትን ቦታም ሆነ ሊሳተፉ የሚችሉ ባለሥልጣናትን እስካሁን ይፋ አላደረጉም።