አሜሪካ በኢራን ጦርነት ረዥም ርቀት የሚወነጨፉ ሚሳዔሎቿን ተጠቅማ ጨርሳለች ተባለ
አሜሪካ ከኢራን ጋር በምታደርገው ጦርነት ረዥም ርቀት የሚወነጨፉ እና ዒላማቸውን ለይተው የሚመቱ ሚሳዔሎቿን ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ መጠቀሟን ሁለት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ምንጮችን ጠቅሶ በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ዘገበ።
ምንጮቹ አክለውም አሜሪካ ዒላማቸውን ለይተው የሚመቱ እና ዘመናዊ ምድር ለምድር የሚወነጨፉ የሮኬት ሚሳዔሎቿን ተጠቅማለች ብለዋል።
አሜሪካ ያሏትን የረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳዔሎቿን በሙሉ ተጠቅማ ማጠናቀቋን ቀድሞ የዘገበው ሮይተርስ የዜና ወኪል ነው።
ሲቢኤስ ከዚህ ቀደም የረዥም ርቀት ሚሳዔሎች እና ከምድር ወደ ኤር ተምዘግዝገው ዒላማቸውን በመለየት የሚመቱ መሣሪያዎች ክምችት በመቀነሱ የትራምፕ አስተዳደር ከኢራን ጋር የምታደርገውን ጦርነት ለማቆም መገደዱን ዘግቦ ነበር።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት በመጋዘን ውስጥ የሚገኙት ዒላማቸውን ለይተው የሚመቱ እና ዘመናዊ ምድር ለምድር የሚወነጨፉ የሮኬት ሚሳዔሎች ቁጥር ውስን መሆኑን ገልፀዋል።
ባለሥልጣናቱ አክለውም ፓትሮይት እና ተርሚናል ሃይ አልቲትዩድ ኤሪያ ዲፌንስ (ቲኤችኤኤዲ) የሚባሉት መሳሪያዎች በፍጥነት አምርቶ መተካት አንደማይቻል ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ሐምሌ ወር ላይ አንድ የምርምር ቡድን ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት አሜሪካ 2330 ፓትሮይት ሚሳዔሎች የነበራት መሆን ገልጾ በሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ ግን ከ827 እስከ 759 መካከል ብቻ ቀርተዋታል ብሏል።
ይኸው ጥናት ከጦርነቱ በፊት 452 ቲኤችኤኤዲ የተባለው መሣሪያ እንደነበራት አስታውሶ በሐምሌ ወር መጨረሻ ግን ከ278 እስከ 234 ባለው ውስጥ ብቻ እንደቀራት መዝግቧል።
ሌላ በቅርቡ ይፋ የሆነ ጥናት አሜሪካ ያሏትን የመሣሪያ ክምችቶች ከጦርነቱ በፊተ ወደነበረው ለመመለስ እስከ 2029 አጋማሽ ድረስ እንደሚወስድባት ይፋ አድርጓል።
የፔንታጎን ቃል አቀባይ ሼን ፓርኔል ለሲቢኤስ ኒውስ በሰጡት ምላሽ “የአሜሪካ ጦር በዓለም ላይ ከፍተኛ አቅም ካላቸው መካከል ነወ። ፕሬዚዳንቱ ባዘዙ ሰዓት የሚሰጠውን ተልእኮ ለመፈጸም የሚያስችል አቅም አለው” ብለዋል።
አክለውም “ውጤታማ ዘመቻዎችን አድርገናል” በማለት “ሕዝባችንን እና ፍላጎታችንን ለመከላከል የሚያስችል በቂ መሣሪያ ታጥቀናል” ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር የሆኑት ፒት ሄግሴት የጦሩ የመሣሪያ ክምችት ቀንሷል የሚለውን አስተያየት ውድቅ አድርገው ነበር።