የተመድ የአቶሚክ ኤነርጂ ኃላፊ በስምምነቱ መሠረት ተቆጣጣሪዎች የኢራንን የኒውክሌር ጣቢያዎች ይጎበኛሉ አሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የዓለም አቀፉ የኒውክሌር ተቋም ኃላፊ፤ አሜሪካ እና ኢራን በደረሱት የመጀመሪያ ደረጃ የሰላም ስምምነት መሠረት ተቆጣጣሪዎች በቴህራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ተገኝተው ምርመራ እንደሚያደርጉ ተናገሩ።
የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኤነርጂ ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ ጃፓን ውስጥ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ “በእርግጥም ምርመራ ይካሄዳል” ብለዋል። የሚካሄድበትን “መንገድ፣ ቀን፣ ሂደት፣ ቦታ [በተመለከተ] እንሰራለን፤ በጣም በቅርቡ” ሲሉም አክለዋል።
የኢራንን እጅግ የበለጸገ ዩራኒየም የመበረዝ ተግባር በዓለም አቀፉ የኒውክሌር ተቋም ቁጥጥር እንደሚካሄድ ባለፈው ሳምንት የተፈረመው ስምምነት ላይ “በግልጽ” እንደሰፈረም ገልጸዋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ግን ጉዳት የደረሰባቸው የአገሪቱ የኒውክሌር ተቋማት እና የኒውክሌር ቁሶችን የተመለከተ ሥራ ሊከናወን የሚችለው ከአሜሪካ ጋር በሚደረስ የመጨረሻ ስምምነት ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ እንደሚሆን ተናግረዋል።
የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኤነርጂ ዋና ዳይሬክተር ይህንን አስተያየት የሰጡት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ስለ ስምምነቱ ለመወያየት የባሕረ ሰላጤው አገራትን እየጎበኙ ባለበት ወቅት ነው።
አሜሪካ እና ኢራን የተፈራረሙት የመጀመሪያ ስምምነት፤ ቴህራን በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚደረግ የመርከቦች ጉዞን እንደምትፈቅድ፤ ዋሽንግተን ደግሞ በኢራን ወደቦች ላይ የጣለችውን የጉዞ እገዳ እንደምታነሳ ያትታል።
ባለፉት ቀናት የተመድ የኒውክሌር ተቆጣጣሪዎች ወደ ቴህራን የመግባታቸው ጉዳይ ላይ አሜሪካ እና ኢራን የተቃረነ አስተያየት ሰጥተዋል።
የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ በስዊትዘርላንድ ከኢራን ዋና ተደራዳሪ ጋር ካደረጉት ንግግር በኋላ ቴህራን “የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኤነርጂ ተቆጣጣሪዎች ወደ አገሪቱ እንዲመለሱ ለመጋበዝ ተስማምታለች” ሲሉ ተደምጠዋል።
በቀጣዩ ቀን አስተያየት የሰጡት የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ግን በጉዳዩ ላይ የተደረገ “ምንም ዝርዝር ውይይት” እንደሌለ ተናግረዋል።
ኢራን፤ የተቋሙ ተቆጣጣሪዎች ባለፈው ዓመት ከእስራኤል ጋር በተደረገው የ12 ቀናት ጦርነት ድብደባ ወደተፈጸመባቸው የኒውክሌር ተቋማት እንዲሄዱ የማድረግ እቅድ እንደሌላትም ገልጸዋል።




















