የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ በሁለት የሞዛምቢክ ዜጎች ግድያ ላይ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Gallo Images via Getty Images
ሁለት የሞዛምቢክ ዜጎች በደቡብ አፍሪካ ዋ ሞሰል ቤይ ከተማ መገደላቸውን የአገሪቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ።
ቀደም ሲል የሞዛምቢክ መንግሥት አምስት ዜጎቹ "በቀጥታ መጤ ጠል ከሆነ ጥቃት ጋር በተያያዘ" መገደላቸውን ገልጾ ነበር።
ነገር ግን የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ የግድያውን ምክንያት ይፋ ሳያደርግ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ብቻ አስታውቋል።
ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በሕገወጥ ስደተኞች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እንዲወስድ የሚጠይቁ ሠልፎች ከተካሄዱ በኋላ ውጥረቶች እየተባባሱ መጥተዋል።
የተወሰኑ የአፍሪካ መንግሥታት በዜጎቻቸው ላይ ጥቃት መፈጸሙን ቢናገሩም፤ የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት ግን ይህንን አላረጋገጡም።
ቅዳሜ ዕለት በምዕራባዊ ኬፕ ግዛት እንደተገደሉ የተገለጹት ሞዛምቢካውያን የ27 እና 43 ዓመት ወንዶች ናቸው።
የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ማክሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ "ጉዳዩን ለማጣራት እንፈልጋለን" ብሏል።
በሌላ ዜና ፖሊስ እሁድ ማለዳ የ18 ዓመት ደቡብ አፍሪካዊ ለዘረፋ ነው በተባለ ጥቃት በስለት ተወግቶ መገደሉን አስታውቋል። ነገር ግን እስካሁን ድረስ በወንጀሉ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለ የለም።
አርብ ዕለት በክዋኖንቃባ የመኖሪያ አካባቢ ተቃውሞ ተቀስቅሶ 50 የስደተኛ መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል። ጥቃቱን ተከትሎ አምስት ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አስታውቋል።
አንዲት ሞዛምቢካዊት ለደቡብ አፍሪካ መገናኛ ብዙኃን ሠልፈኞቹ የእርሷ እና የቤተሰቦቿ "ቤቶችን በእሳት ማቃጠላቸውን" ተናግራለች።
ዶሊንዳ ማቡንዳ "አገሪቱን ለቅቀን እንድንሄድ አለበለዚያ ግን ጥቃት እንደሚደርስብን ተናግረዋል" ካለች በኋላ የሚችሉትን ሁሉ ወስደው "አመለጡ" ብላለች።
የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ሁለት ሞዛምቢካውያን መገደላቸውን ቢገልጽም ሞዛምቢክ ግን አምስት መሆናቸውን አስታውቃለች።
የሞዛምቢክ መንግሥት አርብ ዕለት በነበረው ጥቃት 800 የሚሆኑ ዜጎቹ "የመጤ ጠል ጥቃት ዒላማ" መሆናቸውን አስታውቋል።
አክሎም ቅዳሜ ዕለት 300 ዜጎቹ ደቡብ አፍሪካን ለቅቀው መውጣታቸወን እና 500 የሚሆኑት ደግሞ እንደሚቀጥሉ ተናግሯል። ሁለት ሰዎች በመኪና አደጋ መሞታቸውንም ጨምሮ ገልጿል።
የሞዛምቢክ መንግሥት "የሁኔታው ተለዋዋጭነትን ከግምት በማስገባት አሁን ያለው ሁኔታ ሊባባስ ይችላል" ሲል ዜጎቹን አስጠንቅቋል።
የደቡብ አፍሪካ ተቃዋሚ ሠልፈኞች ሰነድ አልባ ስደተኞችን በመቃወም መንግሥታቸው እርምጃ እንዲወስድ ጫና እያደረጉ ነው።
ስደተኞቹ በወንጀል ላይ ተሳትፈዋል በሚል መንግሥት ላይ ተጽዕኖ እየፈጠሩ ያሉት ሠልፈኞቹ በአገሪቱ ፀረ ስደተኛ የሆነ አመለካከት እንዲስፋፋ እያደረጉ ነው።
በቅርቡ ጋና የደኅንነት ስጋቶችን በመጥቀስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿን ያስወጣች ሲሆን ኬንያ፣ ማላዊ፣ ሌሶቶ እና ዚምባብዌ ደግሞ ለዜጎቻቸው የጥንቃቄ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ፖሊስ በውጭ ዜጎች ላይ የደረሱ ጥቃቶችን ባያረጋግጥም መንግሥት ግን በሌላ አገር ዜጎች ላይ የሚደርሱ "የወንጀል ተግባራትን" ኮንኗል።
የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ ሦስት ሚሊዮን የውጭ ዜጎች እንደሚገኙ የሚገልጽ ሲሆን፣ ይህም ከአጠቃላይ ሕዝቡ 5 በመቶ ያህል ይሆናል።
ነገር ግን በርካቶች ከሕጋዊ ወረቀት ውጭ በደቡብ አፍሪካ ትልልቅ ከተሞች ተሠራጭተው እንደሚኖሩ ይታመናል።
'ማርች ኤንድ ማርች' የተሰኘው የተቃውሞ ቡድን የሚያካሄዳቸውን የፀረ ስደተኞች ሠልፎችን የቀጠለ ሲሆን፣ ሰነድ አልባ ስደተኞች እስከ ፈረንጆቹ ሰኔ 30 ድረስ አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ቀነ ገደብ ማስቀመጡ ተነግሯል።
መጤ ጠል ተቃውሞዎች በደቡብ አፍሪካ በተለያየ ጊዜ የተከሰቱ ሲሆን፣ የስደተኞችን ሕይወትም ቀጥፈው ያውቃሉ።















