ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ ለሳዑዲ አረቢያ 24.3 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የጦር ጄቶችን ለመሸጥ ወሰነች
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ለሳዑዲ አረቢያ ወደ 50 የሚጠጉ የኤፍ-35 ተዋጊ አውሮፕላኖችን ለመሸጥ መወሰኑን ይፋ አድርጓል።
ይህ የአስተዳደሩ ውሳኔ በአሜሪካ ዘንድ የፖሊሲ ለውጥ መኖሩን ያሳያል የተባለ ሲሆን አንዳንድ የኮንግረስ አባላት ግን እርምጃው ስጋት ላይ ጥሏቸዋል።
ሳዑዲ አረቢያ ለዓመታት በዓለም ላይ እጅግ ዘመናዊ የሆነውን የጦር አውሮፕላን ለመግዛት ስትፈልግ ቆይታለች። የጦር አውሮፕላኑ ከጠላት ዕይታ መሰወር የሚያስችል ቴክኖሎጂ የተገጠመለት ነው።
ዋሽንግተን ሽያጩን ለመፈጸም ስታመነታ የቆየችው ለአጋሯ እስራኤል የኤፍ-35 አውሮፕላኖችን ስለምታቀርብ ነበር።
የአሜሪካ ሕግ እስራኤል ከቀጣናዊ ጎረቤቶቿ በተለየ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ የአሜሪካ የጦር መሳሪያዎች እንድታገኝ ዋስትና ይሰጣታል።
ኮንግረሱ ለሪያድ የሚሸጠውን 24 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የአሜሪካ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ለማገድ ወይም ለመመርመር 30 ቀናት ተሰጥቶታል።
የኢሊኖይ ተወካይ የሆኑት ዴሞክራቱ ራጃ ክሪሽናሞርቲ ሐሙስ ዕለት ሽያጩን ተቃውመዋል።
"ይህ የአሜሪካን ወታደራዊ ቴክኖሎጂ ፈርጥ ለቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ቅርብ ርቀት ላይ ሊያስቀምጥ ይችላል" በማለት አስጠንቅቀዋል።
ሌሎች የዴሞክራቲክ ሕግ አውጪዎች እና አንዳንድ የአሜሪካ የመከላከያ ባለሥልጣናት ለሳዑዲ አረቢያ የኤፍ-35 አውሮፕላኖችን መሸጥ ላይ ያላቸውን ተመሳሳይ ስጋት ተናግረዋል።
ሪያድ በሁለቱ አገራት መካከል በተፈረመው የጸጥታ አጋርነት ስር ምስጢራዊውን ቴክኖሎጂ ከቻይና ጋር ልትጋራ እንደምትችል ተናግረዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሐሙስ ዕለት ባወጣው መግለጫ ስምምነቱ የአሜሪካን "የውጭ ፖሊሲ እና የብሔራዊ ደህንነት ዓላማዎች" እንደሚደግፍ አስታውቋል።
ስምምነቱ "በባህረ ሰላጤው ቀጣና የፖለቲካ መረጋጋት እና የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያበረታታ እና የኔቶ አባል አገር ያልሆነን ዋነኛ አጋር ደህንነትን ያሻሽላል" ብሏል።
"የዚህ መሣሪያ ሽያጭ እና የሚደረገው ድጋፍ በቀጣናው ያለውን ወታደራዊ ሚዛን አይለውጥም" ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
ትራምፕ ባለፈው ኅዳር ወር ዋይት ሐውስን ከጎበኙት የሳዑዲው አልጋ ወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላቸው።
ሁለቱ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር በሪያድ ተገናኝተው የነበረ ሲሆን፣ ዋይት ሐውስ "በታሪክ ውስጥ ትልቁ የመከላከያ ሽያጭ ስምምነት" ሲል የገለጸውን የ142 ቢሊዮን ዶላር የጦር መሳሪያ ሽያጭ ተፈራርሟል።
ለሳዑዲ አረቢያ በቅርቡ የቀረበው ሽያጭ 48 የኤፍ-35 አውሮፕላኖችን ያካትታል።
ይህም አገሪቱን በአሁኑ ጊዜ 50 ጄቶች ካሏት እስራኤል ጋር እኩል ያደርጋታል።
ይሁን እንጂ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በግንቦት ወር ሌላ የኤፍ-35 አውሮፕላኖችን እንደሚገዛ አስታውቋል።
ይህ ስምምነት የእስራኤልን የኤፍ-35 አውሮፕላኖች ቁጥር በእጥፍ አሳድጎ 100 እንደሚያደርስ የኢየሩሳሌም ፖስት ዘገባ ያመለክታል ።
የአንድ ሎክሂድ ማርቲን ኤፍ-35ኤ አውሮፕላን ዋጋ 82.5 ሚሊዮን ዶላር ይገመታል።
ኮንግረስ ቀደም ሲል እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2018 የሳዑዲ ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ ግድያ ተከትሎ ከሪያድ ጋር በተደረጉ የጦር መሳሪያ ስምምነቶች ላይ ጥያቄዎችን አቅርቧል።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ሪያድ ከእስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ቀድሞ ሁኔታዋ ለመመለስ ከፈለገች ለሳዑዲ አረቢያ የኤፍ-35 አውሮፕላኖችን ለማቅረብ ሃሳብ የነበረው ቢሆንም ነገር ግን የተደረገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አልተሳካም።
ኮንግረስ ቀደም ሲል በ2018 የሳውዲ ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ ግድያ በኋላ ከሪያድ ጋር የተደረገውን የጦር መሳሪያ ስምምነቶች ጥያቄ አቅርቧል።
አሜሪካ ዘመናዊ ጦር አውሮፕላኖችን የምትሸጠው አብዛኛውን የምዕራብ የመን አካል የሚቆጣጠረውን እና በኢራን የሚደገፈውን ሁቲ በመዋጋት ላይ እያለች ነው።
የሁቲ ታጣቂዎች በቅርቡ የየመንን ቀይ ባሕር ዳርቻ በሳዑዲ ከሚደገፉ የመንግሥት ደጋፊ ኃይሎች እጅ ነጥቀው ተቆጣጥረውታል።
የሳዑዲው ልዑል፣ ትራምፕ በሁቲ አማፅያን ላይ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወስዱ በግላቸው ግፊት ማድረጋቸውን ጉዳዩን የሚያውቁ ሁለት ምንጮች ለሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።