ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ላይ ማሻሻያ ሊኖር እንደሚችል ፍንጭ ሰጡ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ በተጀመረው ሀገራዊ ምክክር የመጨረሻ ጉባኤ መክፈቻ ላይ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት ላይ ማሻሻያ ሊኖር እንደሚችል ፍንጭ ሰጡ።
ከአራት ዓመታት በላይ በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ አጀንዳ ሲያሰባስብ እና ተወያዮችን ሲያስመርጥ የቆየው ሀገራዊ ምክር ኮሚሽን የመጨረሻውን ምክክር የሚያደርግበትን ጉባኤ ዛሬ ረብዑ ሐምሌ 8 2018 ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ ተጀምሯል።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአሜሪካ ሕገ መንግሥት የረቀቀበትን ሁኔታ እና በአገልግሎት ላይ የቆየበትን ጊዜ በዋቢነት በመጥቀስ ኢትዮጵያም ዘላቂነት ያለው የሚያስማማ ሕገ መንግሥት ሊኖራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሜሪካ ሕገ መንግሥት በ55 ሰዎች መረቀቁን አስታውሰው እነዚህ ሰዎች "ለመቶ ዓመታት የሚቆይ ሥራ ሠርተዋል" ብለዋል።
አክለውም "የእኛ አራት ሺህ ሰዎች ከእነሱ በላይ፣ ከእነሱ በተሻለ ጊዜ ይበልጥ ልባም ሆነው፣ ሁሉን ወገን፣ መላው ኢትዮጵያን የሚሰበስብ ምክክር ቢያደርጉ፤ በቀጣይ የሚኖረን ሕገ መንግሥት ከዚህ ቀደም እንደለመድነው የመጣ ሁሉ የሚቀደው ሳይሆን፤ እኛ በአራት ሺህ ጀምረናል፣ በ10 ሺህ ምክክር ሳይደርግ፤ አንድም ሰው መቀየር አይችልም ማለት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
አራት ሺህ ተሳታፊዎች በሚገኙበት በዚህ ጉባዔ ላይ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በሥራ ላይ የቆየው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ጉዳይ በአጀንዳንት ከተካተቱት አንዱ ሲሆን፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግርም ማሻሻያዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ የጠቆመ ሆኗል።
ከዚህ ሀገራዊ ምክክር በመነሳት በሚደረሰው ውጤት መሠረትም በሕገ መንግሥቱ ላይ መሻሻያ ከተደረገ በኋላ የሚደረግ ለውጥ ቀላል እንደማይሆንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ "እኛ አራት ዓመት ተመካክረናል፤ [ወደፊት የሚመጣ ስርዓት] ስምንት ዓመት ሳይመካከር መቀየር አይችልም ማለት ነው" ብለዋል።
ታሪካዊ እና ሌሎችንም ጉዳዮችን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ ውስጥ ኮሽ ሲል ያደፈጡ የሚነቁ፣ የዘመናት ያልተቋረጠ የጠላትነት ስሜት ያላቸው አገራት መኖራቸውን ተናግረዋል።
"የኢትዮጵያን ታሪክ ከጉንደት እስከ ጉራዕ፣ ከአድዋ እስከ ማይጨው፣ ከካራማራ እስከ ባድመ እያንዳንዱን ብትፈትሹ ስንገነባ ያደፈጡ፣ ስንጨቃጨቅ ዕድል ጊዜ ጠብቀው ጣልቃ፣ ሽብልቅ እየገቡ መሻቶቻችንን እንዳንከውን የሚያደርጉ ኃይሎች አሉ" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር "የጥንቱን ታሪክ ብንተው በቅርቡ ቀይ ባሕርን ያጣንበት አጋጣሚ የዚህ እኩይ ታሪካዊ ክስተት አንዱ መገለጫ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።
ኢትዮጵያ "ለሺህ ዘመናት" በባለቤትነት ይዛ ያስተዳደረችውን የነበረውን ቀይ ባሕር ያጣችው "ያልተመረጠ እና ያልተወያየ" ሲሉ የጠሩት መንግሥት "በሸፍጥ" አገሪቱን "የጂኦግራፊ እስረኛ አድርጓታል" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚህ ንግግር በኢትዮጵያ ላይ ለዘመናት ያልተቋረጠ የጠላትነት ስሜት አላቸው ያሏቸውን አገራት በስም አልጠሩም።
ነገር ግን ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ፍላጎቷን በተደጋጋሚ መግለጿን ስትቀጥል፤ ከኤርትራ ጋር ያላት ግንኙነትም ውጥረት አጥልቶበታል።
በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ጋር አለመግባባት ውስጥ ያለችው ግብፅም ከኤርትራ ጋር ወዳጅነቷን አጠናክራ ቀጥላለች።
"ኢትዮጵያ ለሺህ ዘመናት ያስተዳደረችውን በባለቤትነት የያዘችውን ለራሷም ለከባቢውም መጠቀሚያ ያኖረችውን ቀይ ባሕር ያልተመረጠ መንግሥት ያልተወያየ መንግሥት በሸፍጥ ኢትዮጵያን የጂኦግራፊ እስረኛ እንዲያደርግ ያደረገበት ዋና ምክንያት በውስጥ ያለን ስንፍና እንጂ የኢትዮጵያን መሻት እና ጥቅም ማስቆም የሚችል ኃይል ስለነበረ ስላለ ስለሚኖር አይደለም።"
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ንግግራቸው "ሁልጊዜም ጥቅማችንን አሳልፈን የምንሰጠው፣ ስንገነባ ያልነበሩ ስንጣላ ስንሻኮት የሚያንዣብቡ አሞሮች" ስላሉ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ለሚያንዣብቡ አሞሮች በማለት ባስተላለፉት መልዕክትም "ከብቱን መርጠን የምንገዛ እኛ ነን። የቅርጫውን ባለቤት የምንወስን እኛ ነን። የተረፈንን፣ የምንፈልገውን ካልሆነ በስተቀር የትኛውም አሞራ ከየትኛውም የቅርጫ መደብ ላይ አንዲት ኪሎ ሥጋ መውሰድ እንደማይችል ላረጋግጥላቸው እፈልጋለሁ።"
ኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካ "በኃይለ ቃል ተጀምሮ በኃይለ ቃል ይጠናቀቃል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ይህንን ስብራት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ማቆም ያስፈልጋል" ሲሉ ለተገኙ እንግዶች አሳስበዋል።
ኢትዮጰያ ለዘመናት በችግሮች ውስጥ ፀንታ ለመቆየቷ ምሥጢሩ ሽምግልና ንግግር፣ ይቅርታ እና ካሳ መሆናቸውን ጠቅሰው ይህም የንግግር እና የይቅርታ ባሕል ኢትዮጵያን አጽንቷል ሲሉ ለተሰብሳቢዎች ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ 'አዲስ ኮንቬንሽን ሴንተር' ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 8/2018 ዓ.ም. በተጀመረው የመጨረሻውን የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ ከተለያዩ ክልሎች፣ ወረዳዎች፣ ከፌደራል እንዲሁም በውጭ አገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተወጣጡ ከአራት ሺህ ሰዎች ተሳታፊ ናቸው።
ለአንድ ወር ያህል በሚቆየው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የሚሳተፉት ከመላ አገሪቱ ተመርጠው የተሰባሰቡት አራት ሺህ ተሳታፊዎችም በቡድኖች ተከፋፈለው የተወያዩባቸውን አጀንዳዎች፤ በጉባኤው ማጠቃለያ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እንደሚያስረክቡ ፕሮፌሰር መስፍን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በተካሄደው የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ የአፍሪካ ኅብረት እና የኢጋድ ተወካዮች እንዲሁም የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ተገኝተዋል።