አራት ሺህዎቹ የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች በአጀንዳዎች ላይ የሚወያዩት እንዴት ነው?

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከአራት ዓመት በላይ ከወሰደ የተወካዮች መረጣ፣ አጀንዳ ማሰባሰብ እና ሌሎች ተግባራት በኋላ ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 8/2018 ዓ.ም. የመጨረሻውን የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ያስጀምራል።

በአዲስ አበባ ከተማ 'አዲስ ኮንቬንሽን ሴንተር' በሚካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ ከተለያዩ ክልሎች፣ ወረዳዎች፣ ከፌደራል እንዲሁም በውጭ አገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተወጣጡ ከአራት ሺህ ሰዎች ይሳተፋሉ።

ዛሬ የሚጀመረው ጉባኤ ከ30 እስከ 35 ቀናት ይወስዳል ተብሎ እንደሚጠበቅ የአገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነት ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለአንድ ወር በአንድ ስፍራ የሚቆዩት ተሳታፊዎች ምክክር የሚያደርጉት ኮሚሽኑ በሰኔ አጋማሽ ይፋ ባደረጋቸው ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ ነው። ኮሚሽኑ ይፋ ያደረጋቸው አጀንዳዎች በኢትዮጵያ ፖለቲካ የክርክር ነጥብ የሆኑ እንደ የሕገ መንግሥት መሻሻል፣ የመንግሥት ቅርፅ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ "ሕጋዊ አቋም" ያሉ ጉዳዮችን በውስጣቸው ይዘዋል።

በጉባኤው ዋዜማ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት ዋና ኮሚሽነሩ ፕሮፌሰር መስፍን፤ ኮሚሽናቸው ሊተገብረው ያቀደው የአገራዊ ምክክር ሥነ ዘዴ በሌሎች ከአገራት በተካሄዱ ተመሳሳይ ሂደቶች ተግባራዊ ያልተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ዋና ኮሚሽነሩ አገራዊ ምክክር ጉባኤው በምን ዓይነት ቅርጽ እንደሚካሄድ በዝርዝር አብራርተዋል። ዛሬ የሚካሄደው የግማሽ ቀን ሥነ ሥርዓት "የጉባኤው ማስጀመሪያው ሥነ ሥርዓት" ነው።

በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ከሀገር ውስጥ ታዳሚዎች በተጨማሪ "የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት፣ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ኤምባሲዎች፣ የውጭ አገር ሚሲዮን ተወካዮች" ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን እንደሚያስረዱት፤ የአራት ሺህዎቹ የጉባኤው ተሳታፊዎች በአንድ አዳራሽ ታድመው ለአንድ ወር ያህል እንዲመካከሩ አይደረግም።

"በዓለም ላይ ትልልቅ ምክክሮች ተሞክረዋል…ግን እሱ ምክክር አይደለም። እሱ ተሰብስበህ የሁለት፣ የሦስት፣ የአራት፣ የአምስት፣ የአሥር ሰዎችን ዲስኮርስ ሰምተህ የምትለያየው ነው" ሲሉ ኮሚሽኑ ይህንን አካሄድ የማይከተልበትን ምክንያት ገልጸዋል።

ይልቁንም አራት ሺህዎቹ ተሳታፊዎች እያንዳንዳቸው 500 አባላት ባሏቸው ስምንት ቡድኖች እንደሚከፋፈሉ ገልጸዋል። እነዚህ ስምንት ቡድኖች ኮሚሽኑ ይፋ ያደረጋቸውን ስምንት አጀንዳዎች ይከፋፈላሉ።

የትኛው አጀንዳ ለየቱ ቡድን ይሰጣል የሚለው በዕጣ ይወሰናል። 500 አባላት ያሏቸው ቡድኖች የተሰጣቸው አጀንዳ ላይ የሚወያዩት ተወካዮቹን በሌሎች አነስተኛ ቡድኖች በመከፋፈል ነው።

አነስተኛዎቹ በአንጀንዳው ውይይት ካደረጉ በኋላ የደረሱበትን "የመግባባት ወይም ያለመግባባት" ምክረ ሐሳብ ይዘው 500 አባላት ወዳሉት ትልቅ ቡድን እንደሚመለሱ ፕሮፌሰር መስፍን ገልጸዋል።

ዋና ኮሚሽነሩ እንደሚያስረዱት፤ ስምንቶቹ ቡድኖች በተሰጣቸው አጀንዳ ላይ በተናጠል የያዙትን አቋም በተመለከተ ከሌሎች ቡድኖች ጋር ምክክር የሚያደርጉበትም አሠራር ተዘርግቷል። ይህ የሚከናወነው ስምንቱ ቡድኖች እያንዳንዳቸው በሚወክሏቸው 25 ሰዎች ነው።

አራት መቶ የሚሆኑት እነዚህ ተወካዮች በቡድኖቹ በተናጠል ድምዳሜ "የተደረሰባቸውን ምክረ ሐሳቦች በሙሉ እንደገና ያብላሉ፣ በትነው ያያሉ" ሲሉ ፕሮፌሰር መስፍን አስረድተዋል። እነዚህ ተወካዮች በየቡድኑ የቀረቡት "ምክረ ሐሳቦች ተቀባይነት ይኖራቸዋል ወይ?" የሚለውን እንደሚመለከቱም አክለዋል።

በዚህ ደረጃ ላይ ተወካዮቹ "በጋራ የሚደርሱበት የመጨረሻ የጋራ ምክረ ሐሳብ" አራት ሺህ ተሳታፊዎች በሙሉ ለሚሳተፉበት ጉባኤ ይቀርባል። እንደ ዋና ኮሚሽነሩ ገለጻ፤ በዚህ ጊዜ ሁሉም ተሳታፊዎች የሚሰበሰቡት ምክረ ሐሳቦቹን "በጋራ ለመቀበል፣ ለማፅደቅ ወይም ለመጣል" ይሆናል።

በእነዚህ ሂደቶች በሙሉ ለታሳታፊዎቹ እገዛ የሚያደርጉ "ከአመካካሪዎች"፣ "የምሁራን ቡድን" እንዲሁም ቃለ ጉባኤ መዝጋቢዎች ይኖራሉ።

በዚህ ዓይነቱ ሂደት የሚለዩ "ሙሉ በሙሉ ያግባቡ" ወይም "ወደ አለመግባባት የወሰዱ ጉዳዮች በምክረ ሐሳብ ደረጃ ተሰንደው" ለመንግሥት ወይም ለሌሎች ለሚመለከታቸው "ተግባሪ" አካላት ይላካሉ።

ዋና ኮሚሽነሩ እንደሚያስረዱት በምክክር ጉባኤው መግባባት ያልደረሰባቸው ጉዳዮች "ለሕዝብ ውሳኔ" ሊቀርቡ ይችላሉ። ይህም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካኝነት ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲላክ እንደሚደረግ ጠቅሰዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን፤ ኮሚሽኑ የሚመለከታቸው አካላት ምክረ ሐሳቦቹን "በትክክል መቀበላቸውን እና ቀስ እያለ ደግሞ ወደ ትግባራ መሄዳቸውን አረጋግጦ፤ ለሕዝቡ በሚገባ ያስረዳል" ሲሉ የተቋሙን የመጨረሻው ተግባር ገልጸዋል።

"ሪፖርቶቻችንን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ በቀጥታ እናደርሳለን። [የሚመለከታቸው አካላት] 'እንሠራለን' ብለዋል፣ 'የተሠሩ ናቸው'፣ 'አንሠራም ብለዋል'፤ ምክንያቱን እንዲያስረዱ ሕዝቦቻችን ይጠይቁ ወደሚለው እንሄዳለን" ብለዋል።

ኮሚሽኑ፤ የምክረ ሐሳቦችን አፈጻጸም የመከታተል ኃላፊነት በ2014 ዓ.ም. የጸደቀው ማቋቋሚያ አዋጅ ተሰጥቶታል።

ኮሚሽኑ ምክረ ሃሳቦችን ለመተግባር እንዲቻል "ግልፅ እና ተጨባጭ የሆነ ዕቅድ እንዲያዘጋጅ አስፈላጊውን እገዛ" እንደሚያደርግ ተደንግጓል። "የምክረ ሃሳቦቹን አፈጻጸም ለመከታተል የሚያስችል ሥርዓት" እንደሚዘረጋም በአዋጁ ሰፍሯል።

ይሁን እንጂ ባለፈው የካቲት ላይ ለሁለተኛ ጊዜ የተራዘመው የኮሚሽነሮቹ የሥራ ዘመን በቀጣዩ ዓመት ጥቅምት 2019 ዓ.ም. ይጠናቀቃል።

የቀረው ጊዜ የክትትል ሥራውን ለማከናወን በቂ ለስመሆኑ ከቢቢሲ ጥያቄ የቀረበላቸው ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን፤ "ስምንት ወር ነው ፈቃድ የተሰጠን፣ ስምንት ወሩን ስንጨርስ [ውሳኔው] ፈቃድ የሰጠው አካል ነው። እንግዲህ የእሱ ጉዳይ ነው" ብለዋል።

"ሥራዎቹን እኛ ኢንቬንተሪውን ሠርተን የቀሩ ሥራዎች የሚቀሩትን ከምክረ ሐሳብ ጋር ሰጥተን እኛ ሥራችንን እናገባድዳለን። ከዚያ ወዲያ ያለው ውሳኔ የሚሆነው የሕዝብ፣ የመንግሥት፣ በተለይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምናልባትም የአዲሱ የሕዝብ ተወካዮች ወይም የአዲሱ ፓርላማ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከአራት ዓመታት በፊት የተቋቋመው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኢትዮጵያ ውስጥ አወዛጋቢ ናቸው የተባሉ ጉዳዮችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እና በውጭ አገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን አጀንዳዎችን አሰባስቧል።

ኮሚሽኑ ለመጨረሻው ምክክር በማለት ስምምነት ዋና ዋና የምክክር አጀንዳዎችን ከጥቂት ሳምንታት በፊት አጣርቶ ያቀረበ ሲሆን፣ ዛሬ የሚጀመረው የመጨረሻው የምክክር መድረክ በእነዚህ አጀንዳዎች ላይ በመነጋገር የመቋጫ ውሳኔ ላይ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።