ሜሲ፣ ማራዶና ወይስ ፔሌ: የዓለም እግር ኳስ የምንጊዜም ምርጥ ተጫዋች ማን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሊዮኔል ሜሲ ለሦስተኛው የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ ደርሷል። ይህም አርጀንቲናዊው ኮከብ የምንጊዜም ታላቁ የእግር ኳስ ተጫዋች ነውን? የሚል ጥያቄን በድጋሚ ቀስቅሷል። የአገሩን ልጅ ዲያጎ ማራዶና እና የብራዚሉን ፔሌ በልጧልን?
የ39 ዓመቱ ሜሲ በ2026 የዓለም ዋንጫ ለአርጀንቲና ቁልፍ ተጫዋች ሆኖ ቀጥሏል።
ተንታኞች እንደሚሉት ሜሲ በወጣትነት ዘመኑ እንደነበረው ፈጣን ባይሆንም፣ ጨዋታዎችን በዕይታው፣ በአቋቋሙ እና በውሳኔ አሰጣጡ የመቀየር ብቃቱ ቀጥሏል፣። ብዙ ጊዜም ሜዳ ውስጥ እንደሚገኝ አሠልጣኝ ሆኖ ያገለግላል።
ነገር ግን ሜሲ ቀደምንት ተፎካካሪዎቹን በልጧል?
የሜሲ ጉዳይ
ሜሲን በእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚያስቀምጡት ሰዎች ብዙውን ጊዜ ሁለት ጉዳዮችን ያነሳሉ፤ ረጅም ጊዜ መጫወቱን እና ወጥ አቋሙን ነው።
ከብዙ ታላላቅ ተጫዋቾች በተለየ መልኩ ሜሲ ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል በአስደናቂ ብቃቱ ቀጥሏል።
ስምንት የባሎንዶር ሽልማቶችን፣ በስፔን እና በፈረንሳይ የሊግ ዋንጫዎችን፣ የቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫዎችን፣ የኮፓ አሜሪካ እና የ2022 የዓለም ዋንጫን አሸንፏል። አስደናቂ ግብ ማስቆጠር እና ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበልም ክብረ ወሰኖችን እየሰባበረ ይገኛል።
ደጋፊዎቹ በተለያዩ አገራት እና ውድድሮች ስኬታማ የመሆን ችሎታውንም ያነሳሉ። ከባርሴሎና የጀመረው በአውሮፓ የበላይነት እስከ አርጀንቲናን ለዓለም ዋንጫ ማብቃት ማድረሱን ለዚህ በምክንያትነት ያስቀምጣሉ።
ለሜሲ ደጋፊዎች የችሎታ፣ የጽናት እና ለረዥም ጊዜ መጫወቱ በታሪክ ውስጥ ከሌሎቹ ተጫዋቾች ሁሉ ይበልጣል እንዲሉ ያደርጋቸዋል።
የፈረንሳዩ አጥቂ ቴዬሪ ሄንሪ የቀድሞው የባርሴሎና የቡድን አጋሩን ልዩ የሆነ አልሸነፍ ባይነት ያለው መሆኑን ይናገራል።
ሄንሪ ከስፔኑ ማርካ ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፣ በካታላኑ ክለብ ልምምድ ወቅት የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳል።
"አውሬውን አትቀስቅሱት" ሲል ፈረንሳዊው ጠቅለል አድርጎ ይጠቅሳል። ጥፋት ተሰርቶብኝ የቅጣት ምት አልተሰጠም በሚል አርጀንቲናዊው በተከታታይ በርካታ ግቦችን ያስቆጠረባቸውን ጊዜያቶች ያወሳል።

የማራዶና ጥላ
በአርጀንቲና የተጫዋቾች ንጽጽር የሚካሄደው እንደሌሎች አገራት ከፔሌ ወይም ከሌሎች ኮከቦች ጋር አይደለም። ይልቁንም ንጽጽሩ በ1986 ብሔራዊ ቡድኑን ለዓለም ዋንጫ ክብር ካበቃው አምበሉ ዲያጎ ማራዶና ጋር ነው።
የማራዶና ተጽዕኖ ከእግር ኳስ በላይ ነው። ለብዙ አርጀንቲናውያን የብሔራዊ ማንነት ምልክትም ጭምር ነው።
"ማራዶና የአርጀንቲና ንጉሥ ነበር። ንጉሥ ሳይመረጥ አገሪቱን ይወክላል" ሲል ከሜሲ የሕይወት ታሪክ ፀሐፊዎች አንዱ የሆነው ስፔናዊው ጋዜጠኛ ጊለም ባላጉ ለቢቢሲ ኒውስ ብራዚል ተናግሯል።
ለበርካታ ዓመታት አንዳንድ አርጀንቲናውያን የሜሲን ችሎታ ቢያደንቁም ማራዶናን ግን እንደ እውነተኛ ብሔራዊ ምልክት አድርገው ይቆጥሩት ነበር።
በ2020 ህይወቱ ያለፈው ማራዶና በድህነት ማደጉ፤ መንግሥትን በግልጽ መቃወሙ እና በፖለቲካ ውስጥ መሳተፉ በብዙ ሰዎች ዘንድ የአብዮተኝነት እና የግርማ ሞገስ ምሥል እንዲኖረው አድርጓል።
ሜሲ በአንጻሩ በጣም የተለየ መንገድን ተከትሏል። ከሜዳ ውጪ ቁጥብ፣ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ፈቃደኛ ያልሆነ እና በእግር ኳስ ላይ ብቻ ያተኮረ ሲሆን፣ አብዛኛውን የጨዋታ ዘመኑን ትኩረትን በማስወገድ አሳልፏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሜሲ አመለካከቱን እንዴት ቀየረ?
አርጀንቲና በ2021 የኮፓ አሜሪካን ካሸነፈች በኋላ ሰዎች ለሜሲ ያላቸው አመለካከት መለወጥ ጀመረ። ይህም ለ28 ዓመታት ያህል ሲጠበቅ የቆየ ትልቅ ዋንጫ ነበር።
ለውጡ በፍጥነት አድጎ ሜሲ አርጀንቲናን በ2022 ለሦስተኛ የዓለም ዋንጫ አበቃት።
በውድድሩ ወቅት ሜሲ የበለጠ ስሜታዊ እና እልኽኛ መሆኑን አሳይቷል። ይህም ብዙዎች በተለምዶ ከማራዶና ጋር ያቆራኙበት የአመራር ሚናን ተጫውቷል።
"አዲስ ባህሪውን ገለጠ። ሰዎች እንደ ቡድኑ ጄኔራል አድርገው ማየት ጀመሩ" ብሏል ጋዜጠኛው ባላጉ።
ለብዙ አርጀንቲናውያንም አጋጣሚው ሜሲን ከቀድሞው ኮከብ የተለየበትን የስሜት ክፍተት ለመዝጋት የረዳቸው ሆኗል።
ይህም ቢሆንም ክርክሩ ሙሉ በሙሉ እንዳልተፈታ ያምናል።
"ዛሬ ሜሲ እንደ እግር ኳስ ተጫዋች ማራዶናን በልጧል። ነገር ግን ማራዶናን በተሻለ ሁኔታ እንደሚወክላቸው የሚሰማቸው አርጀንቲናውያን ሁልጊዜም ይኖራሉ" ብሏል።
የፔሌ ጉዳይ
አንዳንድ ተንታኞች ሜሲ አርጀንቲናዊውን ማራዶና ብቻ ሳይሆን "የእግር ኳስ ንጉሥ" በመባል የሚታወቀውን እና በ2022 ሕይወቱ ያለፈውን ፔሌን በልጧል ብለው ይከራከራሉ።
ፔሌ በ1958፣ በ1962 እና በ1970 አገሩ የዓለም ዋንጫን ሦስት ጊዜ እንድታነሳ ያስቻለ ብቸኛው ተጫዋች ሆኖ ቀጥሏል።
ፔሌ በአውሮፓውያኑ 2018 ከብራዚሉ ፎልሃ ዴ ኤስ ፓውሎ ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ማራዶና ከሜሲ "በጣም የተሻለ ተጫዋች" እንደሆነ ተከራክሯል።
ሜሲ በግራ እግሩ ላይ በጣም ጥገኛ መሆኑን እና የሌሎች የእግር ኳስ ታላላቅ ተጫዋቾችን አጠቃላይ የጨዋታ ብቃት እንደሌለው ተናግሯል።
በ1970ዎቹ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ስለነበሩት የጀርመን እና የሆላንድ እግር ኳስ ተጫዋቾች በማንሳት "[ፍራንዝ] ቤከንባወር እና [ጆሃን] ክሩፍም የተሻሉ ናቸው" ብሏል ፔሌ።
የቀድሞው የብራዚል ተጫዋች ቶስታኦ ግን የተለየ አመለካከት ነበረው። በ2021 ሜሲ ማራዶናን መብለጡን ነገር ግን አሁንም ከብራዚሉ ኮከብ ቀጥሎ እንደሚቀመጥ ተከራክሯል።
"ከፔሌ በኋላ ሜሲ በታሪክ ውስጥ ምርጡ ተጫዋች ነው" ሲል ቶስታኦ ተናግሯል። "እሱ ከማራዶና የበለጠ የተሟላ እና ረጅም የጨዋታ ዘመን ነበረው። በፔሌ እና በሜሲ መካከል ያለው ልዩነት አካላዊ ነው። ፔሌ ጠንካራ እና ትልቅ ተጫዋች ነበር።"
ፔሌ ጭምር የራሱ ክህሎት ከሜሲ ጋር ሊወዳደር የማይችል እንደሆነ ገልጿል።
"ኳሱን በጭንቅላት ከሚገጭ፣ በግራ እና በቀኝ እግሩ የሚመታን በአንድ እግሩ ብቻ ከሚጫወት፣ አንድ ክህሎት ብቻ ካለው እና ኳሱን በጭንቅላት ከማይገጭ ሰው እንዴት ጋር ማወዳደር ይቻላል?" ሲል ለፎልሃ ደ ኤስ ፖውሎ ተናግሯል።
"ከፔሌ ጋር ለማነጻጸር በግራ እግሩ እና በቀኝ በጥሩ ሁኔታ ከሚመታ እንዲሁም በግንባር ጎሎችን የሚያስቆጥር ሰው መሆን አለበት።"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከቁጥርም በላይ
አለመግባባቱ ሰፋ ያለ ችግርን ያሳያል። ስታቲስቲክስን ለብቻው ከተመለከትን ክርክሩ መቋጫያ ሊያገኝ ይችላል።
የሜሲ የግለሰብ እና የቡድን ሽልማቶች ስብስብ ተወዳዳሪ የለውም።
ቁጥሮች ብቻቸውን ግን በእግር ኳስ ታላላቅ ተጫዋቾች መካከል ያለው ንፅፅር ሙሉ በሙሉ ሊያስረዱ አይችሉም።
ፔሌ፣ ማራዶና እና ሜሲ በተለያዩ ዘመናት ነው የተጫወቱት።
ፔሌ በአውሮፓውያኑ 1958 የመጀመሪያውን የዓለም ዋንጫ ሲያነሳ እግር ኳስ ዘመናዊ የስፖርት ሳይንስ፣ ዓለም አቀፍ የቴሌቪዥን ሽፋን እና የላቀ ቴክኖሎጂ አልነበረውም።
ማራዶና በ1980ዎቹ የዓለምን ትኩረት ሲስብ ከዛሬው ባለብዙ ቢሊዮን ዶላር ኢንዱስትሪ በጣም የራቀ ስፖርት ነበር።
ሜሲ የእግር ኳስ ዘመኑን በሙሉ በብቃት ትንታኔ፣ በተራቀቀ የሕክምና ድጋፍ እና በተከታታይ የሚዲያ ሽፋን በተቀረጸ አካባቢ ውስጥ አሳልፏል። እያንዳንዱ ግጥሚያ በአሠልጣኞች፣ በባለሙያዎች እና በዓለም ዙሪያ ባሉ አድናቂዎች ይተነተናል።
በዚህ ምክንያትም በተለያዩ ትውልዶች ውስጥ ሚገኙ ተጫዋቾችን ማወዳደር እየከበደ ይሄዳል።
ሜሲን "ብልህ" ብሎ የገለጸው የቀድሞው የብራዚል አጥቂ ሮናልዶ፤ የዓለማችንን የምንጊዜም ኮከብ ተጫዋች ለማወቅ ጥቅም ላይ የሚውለው መስፈርት ይወስነዋል ሲል ተከራክሯል።
"ያለ መስፈርት እንዴት መምረጥ ይቻላል?" ሲል ይጠይቃል።
የፔሌ፣ የማራዶና እና የሜሲ የእግር ኳስ ዘመን በተለያዩ ጊዜያት መከናወኑ እርግጥ ነው።
ፔሌ እግር ኳስን ወደ ዓለም አቀፍ ስፖርት ለመቀየር ረድቷል። በአርጀንቲና ታሪክ ሁከት በነገሠበት ወቅት ማራዶና የስፖርት፣ የፖለቲካ እና የባህል ምልክት ሆኗል።
ሜሲ ስሙን የገነባው ግሎባላይዜሽን፣ የስፖርት ሳይንስ እና የሚዲያ ሽፋን በተስፋፋበት ዘመን ነው።
ሦስቱ ተጫዋቾች ከፍተኛ ለውጥ ባሳየው ስፖርት ውስጥ ተሳትፈዋል። ሁሉም ሙሉ በሙሉ የተለያዩ ሁኔታዎች፣ የጊዜ ሰሌዳዎች፣ ተግዳሮቶች እና ዕድሎች ገጥመዋቸዋል። ማንኛውም ውሳኔ የሚመሠረተው በተሰጥኦ፣ በስኬት፣ ረጅም ዕድሜ በመጫወት ወይም በባህል ተጽዕኖ ነው።
ለዚህም ነው ክርክሩ የማብቃት ዕድል ሳያገኝ እና የእግር ኳስ የምንጊዜምን ኮከብ ተጫዋች ክርክር ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ የሚኖረው።















