ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአፍሪካ ዋንጫ ዙሪያ እየታመሰ ያለው ካፍ ዋና ጸሐፊ ከሥራ ለቀቁ
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ዋና ጸሐፊ የአህጉሪቱ እግር ኳስ ትርምስ ውስጥ በገባበት በዚህ ወቅት ከሥልጣናቸው ለቀቁ።
ቬሮን ሞሴንጎ-ኦምባ ጡረታ እንደሚወጡ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል። ዋና ጸሐፊው ከሥልጣናቸው መልቀቃቸውን የገለጹት የ2025 የአፍሪካ ዋንጫ (አፍኮን) ከሴኔጋል በተነጠቀበት እና የሴቶች ውድድር ባለቀ ሰዓት ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ያደረጉ ውሳኔዎች በተላለፉበት ወቅት ነው።
እነዚህ ክስተቶች የአፍሪካ እግር ኳስ የአስተዳደሪ አካል የሆነውን ካፍ ቀውስ ውስጥ እንዲገባ አድርገውታል።
ሞሴንጎ-ኦምባ እሑድ ዕለት ባወጡት መግለጫ በሥልጣን ዘመናቸው ወቅት የተከሰቱትን ውዝግቦች ጠቅሰዋል።
"አንዳንድ ሰዎች በእኔ ላይ ያቀረቡትን ጥርጣሬ ማስወገድ ስለቻልኩ፤ በሰላም ጡረታ መውጣት እችላለሁ። ካፍም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በፋይናንስ ጥንካሬ ላይ ይገኛል" ሲሉ የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪክ ሞትሴፔ ምክትል ሞሴንጎ-ኦምባ ጽፈዋል።
ሞሴንጎ-ኦምባ የድርጅቱ የጡረታ ዕድሜ 63 ዓመት ሆኖም እስከ 66 ዓመታቸው በዋና ፀሐፊነት በመቆየታቸው ሲተቹ ቆይተዋል።
በተጨማሪም በአንዳንድ ሠራተኞች የሥራ ቦታን በማበላሸት ቢከሷቸውም፤ ቅሬታውን ተከትሎ በተደረገ ምርመራ ነጸ ተደርገዋል።
የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዜጋ ሆኑት ሞሴንጎ-ኦምባ፤ የስዊዘርላንድ ዜግነት ያላቸውም ሲሆኑ በ2021 ነው ዋና ፀሐፊ ሆነው የተሾሙት።
እንደ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገባ ከሆነ የካፍ የውድድር ዳይሬክተር ሳምሶን አዳሙ ተጠባባቂ ዋና ፀሐፊ ሆነው ይሾማሉ።
ካፍ ሴኔጋል የአፍሪካ ዋንጫን መነጠቋን ተከትሎ ለስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት (ካስ) ያቀረበችው ይግባኝ የሚያስተላልፈውን ውሳኔ እየጠበቀ ነው።
ሴኔጋል በጥር ወር የአፍሪካ ፍጻሜ ጨዋታ ላይ አስተናጋጇ ሞሮኮን አንድ ለምንም ያሸነፈችበት ውጤት መሰረዙን ተክተሎ ነው ወደ ካስ ያመራችው።
በጨዋታው ምንም ጎል ባልተቆጠረ ሰዓት ሞሮኮ የፍጹም ቅጣት ምት ማግኘቷን በመቃወም የሴኔጋል ተጫዋቾች ሜዳውን ለቀው ወጥተዋል።
ከ17 ደቂቃ ያህል መዘግየት በኋላ ወደ ሜዳ ሲመለሱ ሞሮኮ የፍጹም ቅጣት ምት ማስቆጠር ሳትችል ቀርታ ሴኔጋል በተጨማሪ ሰዓት ባስቆጠረችው ጎል አሸንፋለች።
የሞሮኮ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይግባኝ ማቅርቡን ተከትሎ ካፍ ሴኔጋል ጨዋታውን በማቋረጧ ሞሮኮ 3 ለምንም በሆነ ውጤት አሸንፋለች ሲል ወስኗል።