የሁቲ አማፂያን እስራኤል ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ከ115 ዶላር በላይ ከፍ አለ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካ እና የእስራኤል ከኢራን ጋር የሚያደርጉት ጦርነት እየተባባሰ መሄድን ተከትሎ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ሲጨመር ሰኞ ጠዋት የእስያ አክሲዮኖች ገበያ በከፍተኛ ተቀዘቅዟል።

የብሬንት ድፍድፍ ዋጋ ከ3 በመቶ በላይ በመጨመር የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ከ115 ዶላር በላይ ከፍ ብሏል። በአሜሪካ ደግሞ ወደ 3.5 በመቶ ጨምሮ ወደ 103 ዶላር ከፍ ብሏል። ይህም የብሬንት የወሩ ከፍተኛው ዋጋ ሆኖ ወደ መመዝገብ እያንደረደረው ይገኛል።

የእስያ የአክሲዮን ገበያዎች የተቀዛቀዙ ሲሆን የጃፓኑ ኒኬይ በ4.5 በመቶ ሲወርድ የደቡብ ኮሪያው ኮስፒ ደግሞ በ4 በመቶ ዝቅ ብሏል።

ገበያው ላይ ለውጥ የታየው በየመን በኢራን የሚደገፉት የሁቲ አማጺያን ቅዳሜና እሑድ እስራኤልን በመምታት ግጭቱን ከተቀላቀሉ በኋላ ነው።

ኢራን በበኩሏ በዩኒቨርሲቲዎች እና በአሜሪካ እና በእስራኤል ባለስልጣናት ቤቶች ላይ የበቀል ጥቃት እንደምትሰነዝር አስፈራርታለች።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እሑድ ዕለት ከፋይናንሺያል ታይምስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "ከኢራን ነዳጅን መውሰድ" እና ምናልባትም ዋና የነዳጅ ማዕከሏን የኻርግ ደሴትን መቆጣጠር እንደሚሆን ተናግረዋል።

በደሴቲቱ ላይ ስላለው የኢራን መከላከያ ሲጠየቁ "ምንም ዓይነት መከላከያ አላቸው ብዬ አላስብም። በቀላሉ ልንቋቋመው እንችላለን" ብለዋል።

ትራምፕ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ በጥር ወር ከተያዙ በኋላ አሜሪካ የነዳጅ ኢንዱስትሪውን "ያለገደብ" ለመቆጣጠር ከሄደችበት መንገድ ጋር የወሰዱትን እርምጃ አነጻጽረዋል።

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የኢራን የፓርላማ አፈ ጉባኤ የአገራቸው ጦር ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የሚደርሱ ተጨማሪ 3 ሺህ 500 "የአሜሪካ ወታደሮችን እየጠበቁ" መሆኑን በመግለጽ አስጠንቅቀዋል።

ቴህራን የአሜሪካ እና የእስራኤልን ጥቃቶች ተከትሎ የሆርሙዝን የባህር ወሽመጥ ለማቋረጥ የሚሞክሩ መርከቦችን ለማጥቃት በማስፈራራቷ እና ጥቃት በመጀመሯ የዓለም የነዳጅ ገበያ ተለዋዋጭ ሆኗል።

በዓለም ላይ 20 በመቶ የሚሆነው የነዳጅና የጋዝ አቅርቦት በወሽመጡ የሚያልፍ ነበረ ቢሆንም አሁን ግን በአብዛኛው ቆሟል። ይህም ዋጋውን እያባባሰ ይገኛል።

የማኳሪ ዩኒቨርሲቲ የኢነርጂ ገበያ ባለሙያ የሆኑት ሲን ፎሊ ግጭቱ ካልበረደ በስተቀር የነዳጅ ዋጋ የበለጠ ይጨምራል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

የሁቲ ጥቃቶች በየመን አቅራቢያ በሚገኘው ባብ አል-ማንዴብ የባህር ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ የነዳጅ መርከቦችን ሊያቆም ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል ሲሉ ፎሊ ተናግረዋል።

ባብ አል-ማንዴብ ከተዘጋ ተጨማሪ 10 በመቶ የዓለምን የነዳጅ አቅርቦት ሊስተጓጎል ይችላል። ይህም "በዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለቶች ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል" ሲሉ ፎሊ ገልጸዋል።

የሊፖው ኦይል አሶሴትስ አማካሪ ድርጅት ባልደረባው አንድሪው ሊፖው በበኩላቸው በዓለም አቀፍ የኃይል አቅርቦት ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች ከቀጠሉ የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በሚቀጥሉት ሳምንታት በበርሜል 130 ዶላር ይደርሳል ብለው ይጠብቃሉ።

"ትልቁ ፍርሃቴ በዓለም ዙሪያ የኢኮኖሚ መቃቀዛቀዝ ያጋጥማል. . . ምክንያቱም ሸማቾች ለነዳጅ እና ለምግብ ከፍተኛ ገንዘብ ያወጣሉ" ብለዋል።

አሜሪካ እና እስራኤል ኢራንን ከመምታታቸው አንድ ቀን በፊት የብሬንት ድድፍ ነዳጅ ዋጋ 72 ዶላር አካባቢ ነበር።