ኢቦላ የተከሰተባት ዲሞክራቲክ ኮንጎ በአሰቃቂ በሽታ እና ግጭት እየተፈተነች እንደሆነ የዓለም የጤና ድርጅት አሳሰበ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የቀጠለው ግጭት የኢቦላ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የሚደረገውን እንቅስቃሴ እያስተጓጎለ ነ ውሲሉ የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አስጠነቀቁ።
ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በምሥራቃዊ የአገሪቱ ክፍል የሚገኘው ኢቱሪ ግዛት "የአሰቃቂ በሽታ እና የግጭት ድምር" ማዕከል ሆኗል ብለዋል።
ዶ/ር ቴድሮስ በኤክስ ገፃቸው፤ የዓለም የጤና ድርጅት "የማኅበረሰብ እምነትነትን መገንባት ወይም ቦንቦች እየዘነቡ የታመሙትን ለይቶ ማከም" አልቻለም ብለዋል።
ኃላፊው በዚህ ሳምንት ወደ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተጉዘው ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚደረጉ ጥረቶችን እንደሚመሩ ይጠበቃል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኡጋንዳ ከኮንጎ ጋር የሚያገናኛትን ድንበር በጊዜያዊነት መዝጋቷን አስታውቃለች።
ቫይረሱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ 220 ሰዎች ሞተዋል ተብሏል።
የረድኤት ሰራተኞች መንገዶች ለጉዞ አስቸጋሪ በመሆናቸው ከባድ ፈተና የገጠማቸው ሲሆን፤ ግጭቶች እና የተፈናቀሉ ሰዎች ብዛት የጤና ስርዓቱን አዳክሞታል። እንዲሁም ዓለም አቀፍ እርዳታ መቀነስም ተፅዕኖ አሳድሯል።
የኢቱሪ ግዛት አብዛኛው የቫይረሱ ኬዞች የተመዘገቡበት አካባቢ ነው። እ.አ.አ ከ2021 የሲቪል አስተዳደሩ በወታደራዊ ጄነራል መሪነት ከተተካ ወዲህ ግዛቱ በወታደራዊ አገዛዝ ሥር ነው።
ዶ/ር ቴድሮስ በአካባቢው የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚከናወነው ሥራ "በሰብዓዊ አቅርቦት ላይ የተመሰረተ ነው" ብለዋል።
"ሆኖም የቀጠሉት ግጭቶች ብዙ ሰዎችን እያፈናቀሉ ነው፤ ይህም የተጋለጡ ሰዎች በተጨናነቁ ካምፖች ውስጥ እንዲቆዩ እያደረገ እና የቁጥጥር ኮሪደሮችን እየቆረጠ ነው" ብለዋል።
"የመጀመሪያ እርዳታ ሰጪ ሠራተኞች ሁሉንም ነገር አደጋ ላይ ጥለዋል። በጤና ተቋማት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ኬዞች እና ንክኪ ያላቸውን ሰዎች መከታተልን አስቸጋሪ አድርገውታል" ሲሉ ችግሩን ገልፀዋል።
ኃላፊው ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት አድርገው የሕክምና ቡድኖች በደኅንነት እንዲንቀሳቀሱ መፍቀድ አለባቸውም ብለዋል።
የኢቦላ ወረርሽኝ ሊስፋፋ ይችላል የሚለው ስጋት በርካታ አገራትን ጠንካራ የጉዞ ገደቦች እንዲያወጡ አድርጓል።
ረቡዕ ዕለት ኡጋንዳ ድንበሯን ወዲያው እንደምትዘጋ አስታውቃለች። ነገር ግን የአስቸኳይ ሰራተኞች ማለትም የሕክምና እና የረድኤት ሰራተኞች፣ የምግብ አጓጓዦች እና የደኅንነት አካላት በጥብቅ መመሪያ መሰረት መሻገር ይችላሉ ተብሏል።
ካናዳ ከኮንጎ፣ ኡጋንዳ እና ደቡብ ሱዳን የሚመጡ ሰዎች ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ ለ90 ቀናት የሚቆይ እግድ ጥላለች።
ባህማስም ጥብቅ መመሪያዎችን ያወጣች ሲሆን፤ ከአገራቱ የሚመጡ የውጭ ዜጎች በለይቶ ማቆያ እንዲቆዩ አደርጋለሁ ብላለች።
ባለፈው ሳምንት አሜሪካ ዜጎቿ ያልሆኑ እና ከሦስቱ አገራት የሚጓዙ መንገደኞች እንዳይገቡ ከለከለች።
የዲሞክራቲክ ኮንጎ የጤና ባለሥልጣናት ከ1,000 በላይ ሰዎች ከኢቦላ ጋር የሚመሳሰሉ ምልክቶች እንዳሳዩ ይናገራሉ።















