በሰሜናዊ ቆጵሮስ ጀልባ ተገልብጦ ስምንት ሰዎች ሲሞቱ፣ 18 ተሳፋሪዎች የደረሱበት አልታወቀም

የተገለበጠው ጀልባ ላይ የነፍስ አድን ጃኬት ለብሰው የቆሙ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በሰሜናዊ ቆጵሮስ መንገደኞችን ያሳፈረ ጀልባ ተገልብጦ ቢያንስ የስምንት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፣ 18 ሰዎች እስካሁን የደረሱበት እንዳልታወቀ በአካባቢው የሚገኘው የቱርክ አስተዳደር አስታወቀ።

እሁድ ዕለት 'ኪሬኒያ' ከተባለው የባሕር ዳርቻ ከተማ የተነሳው ጀልባ 259 መንገደኞችን እና ስምንት ሠራተኞችን ይዞ እንደነበር 'ተርኪሽ ሪፐብሊክ' በሚል በቆጵሮስ አገርነቱን ያወጀው አስተዳደር ጠቅላይ ሚኒስት የሆኑት ኡናል ኡስቴል ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ ጀልባው ከተነሳ በኋላ ውሃ ማስገባት ጀምሯል።

አደጋውን ተከትሎ የጀልባው ካፒቴን እና ሰባት ሠራተኞች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ኡስቴል በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው አስታውቀዋል። "ይህ አሳዛኝ ክስተት እንዴት ተፈጠረ" የሚለውን ለማወቅ ምርመራ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

ጀልባው ላይ ከነበሩ ተጓዦች ውስጥ አብዛኞቹን ማትረፍ መቻሉን ባለሥልጣናት ገልጸዋል። የቱርክ ባለሥልጣናት አሁንም ቢሆን የፍለጋ እና የነፍስ አደን ሥራን ማከናወን ቀጥለዋል።

በአሁኑ ሰዓት ጀልባው የሰመጠ ሲሆን፣ ባለሥልጣናቱ ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ እንዲችሉ የጀልባውን ጥቁር ሳጥን (ብላክ ቦክስ) ለማግኘት እየሞከሩ ነው።

የግል ንብረት የሆነው ይህ ጀልባ ኪሬኒያ ከሚገኝ ታዋቂ ሪዞርት የተነሳው እሁድ እኩለ ቀን ገደማ ላይ ነበር።

ጀልባው ቅዳሜ ዕለት ወደ ቱርክ ሊጓዝ የነበረ ቢሆንም በነበረው መጥፎ አየር ሁኔታ ምክንያት ጉዞውን አዘግይቶ ነበር።

እሁድ ዕለት ጀልባው ከመገልበጡ በፊት በሁለት ወጀቦች መመታቱንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ 'ቲአርቲ' ለተባለ የቱርክ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

የጀልባው ካፒቴን ከመጀመሪያው ወጀብ ለማምለጥ ሲሞክር ሁለተኛ ወጀብ እንዲመታው እና ውሃ ወደ ጀልባዋ መግባት እንደጀመረም አስረድተዋል።

ከአደጋው በኋላ ሄሊኮፕተር እና የባሕር ጥበቃ ጀልባዎች በስፍራው ተሰማርተዋል። በሕይወት የተረፉ መንገደኞች የሚቀበሉ አምቡላንሶችም በባሕር ዳርቻው ቆመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኡስቴል በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ "አሁን ላይ ቅድሚያ የሚሰጠው የሰው ሕይወት ነው" ያሉ ሲሆን፣ የነፍስ አድን ቡድኖች እና የጤና ባለሥልጣናት በሙሉ በስፍራው እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

ክስተቱን በተመለከተ ጥልቅ ምርመራ እንደሚካሄድ እና "ትንሽ ቸልተኝነትም ቢሆን እንደሚደረስበት" አክለዋል። "ማንም ቢሆን ጥፋተኛ ወይም ተጠያቂ ሆኖ የተገኘ የትኛውም ሰው አይማርም" ሲሉም ጽፈዋል።

በቱርክ ብቻ የአገርነት ዕውቅና የተሰጣት የሰሜን ቆጵሮስ የቱርክ ሪፐብሊክ የትራንስፖርት ሚኒስትር ኤርሃን አሪክሊ፣ 100 ተሳፋሪዎች በሕይወት ተርፈው ወደ ባሕር ዳርቻው መወሰዳቸውን ለአካባቢው መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲብ ታይፕ ኤርዶዋን በአደጋው የተሰማቸውን ሐዘን ለቱርክ ቆጵሮሳውያን ገልጸዋል። የደረሱበት ያልታወቀ ሰዎችን ለማግኘት የሚደረገው ጥረት "ያለመስተጓጎል ይቀጥላል" ብለዋል።