በወሲባዊ ብዝበዛ እና በስም ማጠልሸት ጥፋተኛ የተባሉት ትራምፕ ለአሜሪካዊቷ ደራሲ 5 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ከፈሉ

ኢ ጄን ካሮል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ጸሐፊዋ ኢ ጄን ካሮል ላይ ወሲባዊ ብዝበዛ በማድረስ እና ስም በማጠልሸት ጥፋተኛ የተባሉት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከአምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ካሳ መክፈላቸው ተገለጸ።

የደራሲዋ ጠበቃ ሮበርታ ካፕሊን "በፍርድ ውሳኔው መሠረት የካሳ ክፍያውን መቀበሏን ስናሳውቅ በደስታ ነው" ብለዋል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔውን ዳግመኛ እንዲያጤን ለመጠየቅ ያሰቡት ትራምፕ ክፍያውን ማዘግየታቸው ተገልጿል።

ሆኖም ግን ብይኑን የሰጡት ዳኛ ባለፈው ሳምንት ባስተላለፉት ትዕዛዝ ትራምፕ ካሳውን እንዲከፍሉ አድርገዋል።

የትራምፕ የሕግ አማካሪዎች ቡድን ተወካይ ክፍያውን በተመለከተ አስተያየት ለመስጠት አልፈቀዱም።

የደራሲዋ የሕግ አማካሪዎች ቡድን እንዳለው 5 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እና ተከሳሹ ይግባኝ ባሉት ወቅት የካሳው ወለድ ተደምሮ ከ5.62 ሚሊዮን ዶላር በላይ ክፍያ ተፈጽሟል።

የቀድሞዋ የመጽሔት አምደኛ ኢ ጄን ካሮል አሁን 82 ዓመት ሞልቷታል።

በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ አጋማሽ ትራምፕ ጥቃት እንዳደረሱባት በመግለጽ ከስሳለች።

በማንሀተን በሚገኘው ቤርግዶፍ ጉድማን ጥቃት ከፈጸሙባት በኋላ በአውሮፓውያኑ 2022 በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያቸው ስሟን እንዳጠፉት ተናግራለች።

በ2023 ኒው ዮርክ በሚገኝ ፍርድ ቤት ትራምፕ ካሳ እንዲከፍሉ ተወስኗል። ፕሬዝዳንቱ ጥፋተኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።

የካሳ ክፍያው በፍርድ ቤት ቁጥጥር በሚደረግበት አካውንት ውስጥ ተቀምጦ ሳለ ትራምፕ ይግባኝ ብለዋል።

ትራምፕ ካሳውን መክፈል አለባቸው የሚለው ውሳኔ ሲጸና፤ የፕሬዝዳንቱ የሕግ ቡድን "ማጭበርበር" እና "ውሸትን የተመረኮዘ አደን" ሲል አጣጥሏል።

ዳኛ ልዊስ ካፕሊን የተጭበረበረ ማስረጃ አቅርበዋል ሲሉም ትራምፕ ወንጅለዋል።

የፌደራል ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ግን ዳኛው ምንም ስህተት እንዳልሠሩ በመግለጽ ውሳኔ አሳልፏል።

ባለፈው ወር የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባሳለፈው ውሳኔ ትራምፕ ካሳውን መክፈል አለባቸው ተብሏል።

ደራሲዋ "አሸንፈናል! ድሉ በመላው ዓለም ያሉ ሴቶች ነው" በማለት ደስታዋን ገልጻለች።

በ2024 ትራምፕ በስም ማጠልሸት ጥፋተኛ ሲባሉም ትራምፕ ይግባኝ ብለው ነበር። በዚህ ክስ ለደራሲዋ ወደ 84 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ካሳ እንዲከፈል ተወስኗል።