የትራምፕ አስተዳደር የውጭ አገራት ተማሪዎች የቪዛ ደንቦችን አጠበቀ

የአሜሪካ ዩኒቨርስቲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ለውጭ አገራት ተማሪዎች ጥብቅ የቪዛ ደንቦችን ለመተግበር የመጨረሻ ውሳኔ ላይ መድረሱ ተገለጸ።

ውሳኔው ተማሪዎች ያለ ፌደራል መንግሥት ፈቃድ ከአራት ዓመት በላይ በአሜሪካ እንዳይቆዩ ማገድ እና ሌሎችም ጥብቅ እርምጃዎችን ያካተተ ነው።

ዩኒቨርሲቲ መለወጥ ወይም የትምህርት ክፍል መቀየር ላይም ገደብ ይጣላል ተብሏል። እስካሁን ድረስ ባለው አሠራር ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ቪዛ እንዲራዘም የማድረግ ሥልጣን ነበራቸው።

ፖሊሲው የሚተገበረው ከቀጣዩ መስከረም አንስቶ ሲሆን፤ የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ "የቪዛ ብዝበዛን የሚገዳደር እና የጀርባ ታሪክ ምርመራ በማድረግ ብሔራዊ ደኅንነትን የሚያጠናክር አሠራር ነው" ብሏል።

የዓለም አቀፍ መምህራን ማኅበር ግን ውሳኔውን "የተዛባ እና አላስፈላጊ" ሲል ኮንኖታል።

እስካሁን ድረስ ይተገበር በነበረው አሠራር ኤፍ-1 እና ጄ-1 የውጭ አገራት ተማሪዎች ቪዛ ያላቸው ትምህርት እስከሚያጠናቅቁ ድረስ በአሜሪካ መቆየት ይፈቀድላቸዋል።

ከዚህ በኋላ ግን የተማሪዎች የቆይታ ጊዜ ላይ ገደብ የሚጣል ይሆናል።

የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ ማርክዌይን ሙሊን "ለአሥርታት የውጭ አገራት ተማሪዎች ያለ ጊዜ ገደብ ወደ አሜሪካ ሲመጡ ነበር። በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ትምህርቶች እየጀመሩ አሜሪካ በመቆየት የስደተኞች ሥርዓቱን በዝብዘዋል" ብለዋል።

በአሜሪካ በአብዛኞቹ የትምህርት ክፍሎች የመጀመሪያ ዲግሪ ለማጠናቀቅ አራት ዓመት ይወስዳል። ሦስተኛ ዲግሪ ግን ዘለግ ያለ ጊዜ ያስፈልገዋል።

የውጭ አገራት ተማሪዎች የመጀመሪያ ዲግሪ በብዛት የሚሠሩት በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ነው።

ትምህርቶቹን እንዲሁም የመመረቂያ ጽሑፍ ለመጨረስም ጊዜ ያስፈልጋል።

ጥናት እና ምርምር ለማከናወን የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት የሚደረገው ጥረትም ተጨማሪ ጊዜ ይወስዳል።

የትራምፕ አስተዳደር ባወጣው አዲስ ፖሊሲ መሠረት ተማሪዎች ከተመረቁ በኋላ በ30 ቀናት ውስጥ ከአሜሪካ መውጣት አለባቸው። ሌላው አማራጭ የቪዛ ዓይነት መቀየር ሲሆን፤ ይህም 60 ተጨማሪ ቀናት ለማግኘት ይረዳል።

የዓለም አቀፍ መምህራን ማኅበር ዋና ኃላፊ ፋንታ አው አዲሱ ፖሊሲ "ጥርጣሬ የሚያጭር፣ በቢሮክራሲ የተሞላ፣ በአግባቡ የሚሠራ ሥርዓት ላይ ፍርሃት የሚያሳድር፣ ችግር በሌለበት መፍትሔ የሚፈልግ ነው" ሲሉ ተችተዋል።

የትራምፕ አስተዳደር የውጭ አገራት ተማሪዎች እና የስደተኞን ቁጥር ለመቀነስ የተለያዩ እርምጃዎች መውሰዱን ቀጥሏል።

አንዳንድ ዕውቅ ዩኒቨርስቲዎች የሚቀበሏቸውን የውጭ አገራት ተማሪዎች ቁጥር እንዲቀንሱ ለማድረግ ተሞክሯል። የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የተቃወሙ ተማሪዎች ቪዛ እንዲሰረዝም ተወስኗል።