ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሳዑዲ ከአሜሪካ ጋር የደረሰችው የኒውክሌር ስምምነት ጦር መሣሪያ መገንባት ያስችላታል?
አሜሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ፣ የባሕረ ሰላጤዋ አገር ዩራኒየም እንድታበለጽግ ይፈቅዳል የተባለ ታሪካዊ ስምምነት ተፈራርመዋል።
የአሜሪካ ኤነርጂ መሥሪያ ቤት እንዳለው ስምምነቱ "ሰላማዊ የኒውክሌር የትብብር ስምምነት" ተብሎ የተገለጸ ሲሆን የአሜሪካ ኩባንያዎች በሳዑዲ የኤነርጂ ፕሮግራም ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው።
የስምምነቱ ዝርዝር ነጥቦች ግን ይፋ አልተደረጉም።
የበለጸገ ዩራኒየም ለኃይል ማመንጫዎች እንደ ነዳጅ የሚጠቅም ሲሆን ኒውክሌር ቦምብ ለመሥራትም ያስችላል።
ባለሙያዎች እንደሚሉት ይህ ባልተረጋጋው ቀጣና ውስጥ የኒውክሌር መስፋፋት አደጋ ሊያስከትል የሚችል ነው።
የኒውክሌር ጉዳይ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ለከፈቱት ጥቃት ማዕከል ሆኖ ቆይቷል።
ሁለቱ አገራት በኢራን ላይ ጥቃት እንዲከፍቱ ካደረጓቸው ምክንያቶች አንዱ ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ ማበልጸጓን እንድታቆም ለማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል።
ቴህራን ግን የኒውክሌር መሣሪያ የማበልጸግ ዕቅድ እንደሌላት በተደጋጋሚ ገልጻለች።
ሳዑዲዎች ዩራኒየም እንዲያበለጽጉ ይፈቀድላቸዋል?
የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች የተረጋገጡ ከሆነ የሳዑዲን የኒውክሌር ስምምነት ልዩ ያደርገዋል።
አሜሪካ "ሰላማዊ የኒውክሌር ትብብር " ያለችውን ስምምነት ወደ 50 ከሚጠጉ አገራት ጋር እንደተደረሰ የኤነርጅ መሥሪያ ቤቷ አስታውቋል።
እንዲህ ዓይነት ስምምነቶች ነዳጅ፣ ኃይል አመንጪዎች (ሪአክተርስ) እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን ጨምሮ የኒውክሌር ቁሳቁሶች እንዲዘዋወሩ እና የጋራ ጥናቶች እንዲካሄዱ ይፈቅዳሉ።
ሆኖም እስካሁን በአገራቸው ውስጥ የኒውክሌር ነዳጅ ለማምረት እንዲሁም የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ለመሥራት ወሳኝ ግብዓት የሆነውን ዩራኒየም እንዲያበለጽጉ የተፈቀደላቸው ሕንድ እና ጃፓን ነበሩ።
ሌሎች አገራት የኒውክሌር ነዳጅ የሚያስገቡት ከውጪ ሲሆን ኃይል ለማመንጨት የሚጠቅመውንና አገልግሎት ላይ የዋለን የኒውክሌር ነዳጅ እንደገና እንዳያብላሉ ታግደዋል።
ይህ ዘዴ እንደ ፕሉቲኒየም እና ዩራኒየም ያሉ ጥቅም ላይ የሚውሉ የኒውክሌር ቁሶችን እንደገና ለማውጣት የሚረዳ ነው።
ይህንን እንዳያደርጉ ከታገዱ በርካታ አገራት መካከል የሳዑዲ አረቢያ ጎረቤት የሆነችው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ (ዩኤኢ) ትገኝበታለች።
ተቀማጭነቱ በአሜሪካ የሆነው 'ዲፌንስ ፕራዮሪቲስ' የጥናት ተቋም የመካከለኛው ምሥራቅ ዳይሬክተር የሆኑት ሮዝመሪ ኬላኒክ ፣ ስምምነቱ አሜሪካ፣ ሳዑዲ አረቢያ ዩራኒየም እንድታበለጽግ መፍቀድን የሚያካትት ከሆነ "በጣም አስደንጋጭ" ነው ብለዋል።
"አሜሪካ ከዚህ ቀደም እንዲህ አድርጋ አታውቅም፤ ሌላ አገር በራሳቸው ምድር እንዲያበልጽጉ ረድታም አታውቅም" ያሉት ዳይሬክተሯ፤ የዚህ ምክንያቱም " አገራት የየራሳቸውን የኒውክሌር ነዳጅ ማምረት ከቻሉ የኒውክሌር መሣሪያ ለመገንባት ትልቅ አደጋ ስለሚሆን ነው" ሲሉ አስረድተዋል።
የበለጸገ ዩራኒየም ምንድን ነው?
ዩራኒየም በመሬት የላይኛው ክፍል (ክረስት) የሚገኝ ንረጥ ነገር ነው።
በአብዛኛው ዩ-238 እና ዩ- 235 በተባሉ ሁለት አይሶቶፖች የሚሠራ ነው።
99 በመቶ የሚሆነው ተፈጥሯዊ ዩራኒየም ዩ-238 አይሶቶፕ የያዘ ሲሆን፣ ኃይል መፍጠር አይችልም።
0.7 በመቶ ብቻ የሆነው ዩ-235 አይሶቶፕ ነው በቀላሉ በመከፋፈል ኒውክሌር ፊውዥን በሚባለው ሒደት ኤነርጂ ማመንጨት የሚችለው።
በመሆኑም ዩራኒየምን ጠቃሚ ለማድረግ በማበልጸግ ሒደቱ የዩ-235 መጠንን መጨመር ያስፈልጋል።
መጀመሪያ ላይ ዩራኒየሙ ወደ ጋዝ መቀየር ይኖርበታል።
ከዚያም ጋዙ በከፍተኛ ፍጥነት ወደሚሽከረከር ማሽን እንዲገባ ይደረጋል።
በዚህ ሒደት እየተጨመቀ ሲሄድ ከባድ የሆነው ዩ-238 ወደ ዳር ይወጣል፤ ቀላል የሆነው ዩ-235 ደግሞ ለመካከሉ ቅርብ ሆኖ ይቀመጣል።
ይህም ቀስ በቀስ ብርቅዬ የሆነውና ጠቃሚ የሆነው ዩ-235 ዩራኒየም ከተለመደው ዩ-238 ዩራኒየም እንዲለይ ያስችለዋል።
ተለይቶ የተከማቸው ይህ ዩራኒየም ከአንደኛው የማብለያው ጫፍ በኩል ይወጣል።
ለኒውክሌር ኃይል ማመንጫ እና ለጦር መሣሪያ የሚውለው ዩራኒየም ልዩነት ምንድን ነው?
ዩራኒየም የሚበለጽግበት ደረጃ ለተለያዩ አገልግሎቶች እንዲውል ደያርገዋል።
በዝቅተኛ ደረጃ የበለጸገ ዩራኒየም የሚይዘው ከሦስት እስከ አምስት በመቶ የሚሆን ዩ-235 ነው። ይህም ለኒውክሌር ኃይል ማበልጸጊያዎች ነዳጅ በመሆን ያገለግላል።
የአፀግብሮት ሰንሰለት (ሪአክሽን ቼይን) ለመፍጠር ግን በቂ አይደለም። ለጦር መሣሪያ ከሚያስፈልግ መጠንም እጅግ በጣም አነስተኛ ነው።
በከፍተኛ ደረጃ ወይም 20 በመቶና ከዚያ በላይ የበለጸገ ዩራኒየም ለምርምር ኃይል የሚውል ሲሆን ለጦር መሣሪያ የሚውል ዩራኒየም ወደ 90 በመቶ መበልጸግ ይኖርበታል።
ይህ ክምችት ለኒውክሌር ኃይል በቂ ሲሆን ወዲያውኑ ከቁጥጥር ውጪ ሊሆን ይችላል።
ቁሱ አንድ ላይ በሚሆንበት ጊዜ አቶሞች በጣም በፍጥነት መከፋፈል የሚጀምሩ ሲሆን በሰከንድ ሽርፍራፊ እጅግ ብዙ የሆነ ኃይል ይለቃል።
ይህ ነው ለሲቪል እና ለጦር መሣሪያ የሚውል ዩራንኒየምን የሚለየው።
ለነዳጅ የሚውለው በዝቅተኛ ደረጃ የሚበለጽግ ሲሆን ሒደቱ ሆነ ተብሎ ዘገምተኛ እንዲሆን የሚደረግ እና በጥንቃቄ የሚያዝ ነው። ይህም ኤነርጅን ቀስ በቀስ በወራት ወይም በዓመታት ለመልቀቅ ያስችላል።
የኒውክሌር ቦምብ ዩራኒየም ግን የዚህ ተቃራኒ ነው። ሪአክሽኑ በአንድ ጊዜ በፍጥነት እንዲፈጠር ይደረጋል።
ሳዑዲ ኒውክሌር ቦምብ ትሠራለች?
የአሜሪካ የኤነርጂ መሥሪያ ቤት ስምምነቱን ባስታወቀበት እና ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ ከትብብር ስምምነቱ በተጨማሪ "የሁለትዮሽ ጥበቃ ስምምነት" መፈራረማቸውን ገልጿል።
"እነዚህ ሁለት ስምምነቶች የኒውክሌር መስፋፋትን ጨምሮ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን በርካታ ኢኮኖሚያዊ እና ስትራቴጂካዊ ዓላማዎችን የሚያራምድ ለአስርተ ዓመታት የሚቆይና በርካታ ቢሊዮን ዶላር የሚፈጅ አጋርነት ሕጋዊ መሠረት ይጥላሉ" ብሏል መግለጫው።
የሳዑዲ መንግሥት በበኩሉ ባወጣው መግለጫ ስምምነቱ ሁለቱ አገራት በኤነርጂው ዘርፍ ያላቸው ትብብር መቀጠሉን የሚያመለክት ነው ብሏል።
ሁለቱ አገራት ከስምምነት ላይ የደረሱት የሳዑዲው መሪ ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሃመድ ቢን ሳልማን ባለፈው ኅዳር ወር በዋሽንግተን ጉብኝት ካደረጉ በኋላ ነው።
ልዑል አልጋ ወራሽ ቢን ሳልማን እአአ በ2018 ለአሜሪካው የቢቢሲ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ፣ አገራቸው ኒውክሌር መሣሪያ የመታጠቅ እቅድ እንደሌላት፤ ነገር ግን "ኢራን የኒውክሌር ቦምብ ካመረተች ያለምንም ጥርጥር በተቻለ ፍጥነት እርምጃ እንወስዳለን" ብለዋል።
የመካከለኛ ምሥራቅ አገር ከ2010 ጀምሮ የሲቪል ኒውክሌር ፕሮግራም ለማበልጸግ እየሞከረች ነው።
ሆኖም እስካሁን ምንም ዓይነት የኒውክሌር ማበልጸጊያ የላትም።
የዓለምን የኒውክሌር ኃይል ኢንደስትሪ የሚወክለው ዓለም አቀፉ - የዓለም የኒውክሌር ማኅበር አገሪቷ የኒውክሌር ኢነርጅ ለማምረትም አቅሙ የላትም።