ወደ ዌስት ባንክ የተጓዙት የአሜሪካ ኮንግረስ አባል በእስራኤል ሰፋሪዎች ተይዘው እንደነበር ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ ኮንግረስ አባል የሆኑት ዴሞክራቱ ሮ ካና በወረራ ሥር ወደሚገኘው ዌስት ባንክ ጉብኝት በሚያደርጉበት ወቅት በታጠቁ እስራኤላውያን ሰፋሪዎች ለአንድ ሰዓት ተኩል ተይዘው መቆየታቸውን ተናገሩ።
የ49 ዓመቱ ካና ረቡዕ ዕለት ከቡድን አባላቶቻቸው ጋር መኪና ውስጥ ሳሉ የኤም4 ጠመንጃ በያዙ ሰፋሪዎች መከበባቸውን ለዜና ወኪሉ ሮይተርስ ገልጸዋል።
ካና በኤክስ ገጻቸው ላይ ባጋሩት ጽሑፍ፤ ወደ ሥፍራው የደረሱት የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት አባላት "ለሰፋሪዎቹ በመወገናቸው እስራችን ቀጥሏል" ብለዋል።
የእስራኤል ጦር ባወጣው መግለጫ፤ ሰፋሪዎች የተሽከርካሪዎችን ጉዞ ስለማገዳቸው ጥቆማ ከደረሰ በኋላ ወታደሮች እና የፖሊስ አባላት እርምጃ መውሰዳቸውን ጠቅሷል።
ወደ ሥፍራው "ወታደሮች እንደደረሱ፤ የእስራኤል ሲቪሎችን በትነዋል፤ ተሽከርካሪዎቹም መንገዳቸውን እንዲቀጥሉ አድርገዋል" ብሏል።
የኮንግረስ አባሉ ካና ወደ ሥፍራው የተጓዙት እስራኤል በዌስት ባንክ ያደረገችው ወረራ ያደረሰውን ተጽዕኖ በተመለከተ ያለውን እውነት የሚያጣራ ተግባር ለማከናወን ነበር።
የሁለት ልጆች አባት የሆኑት ፖለቲከኛው፤ በ2028 በሚካሄደው የአሜሪካ ምርጫ ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር እያጤኑ ነው።
"እስራኤላዊ ሰፋሪዎች ባወደሙት መንደር ነበርን፤ ትምህርት ቤቱን አውድመዋል፤ ያንን መንደር አውድመውታል፤ እናም እየተመለከትነው ብቻ ነበር" ብለዋል።
ካን "እነዚህ ወንበዴዎች በአሜሪካ የተሰራ ኤም 4 የማሽን ጥይት (ማሽንገን) ይዘው መጡ እና አሰሩን። መንገዱንም ዘጉት። ከዚያም ለእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ደወሉ። ሠራዊቱ ከእነርሱ ጎን ነበር፤ ከአሜሪካውያን ጎን አልነበረም" ሲሉ ተናግረዋል።
ታስረው በነበረበት ሰዓት ረዳታቸው ለእርዳታ እየሩሳሌም ወደሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ደውለው እንደነበር የተናገሩት የምክር ቤት አባሉ፤ የፖሊስ አባላት ጣልቃ ከገቡ በኋላ መለቀቃቸውን ገልጸዋል።
እስራኤል በ1967 የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ዌስት ባንክ እና ምሥራቅ እየሩሳሌምን ከወረረችበት ጊዜ አንስቶ 700 ሺህ አይሁዳውያን የሚኖሩባቸውን 160 ገደማ ሰፈራዎች ገንብታለች።
ሰፈራ የተገነባባቸው ሥፍራዎች ፍልስጤማውያን ወደ ፊት ለመመስረት ተስፋ የሚያደርጓት አገር አካል እንዲሆኑ የሚፈልጓቸው ናቸው። በእነዚህ ሥፍራዎች 3.3 ሚሊዮን ፍልስጤማውያን ይኖራሉ።
በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት እነዚህ ሰፈራዎች ሕገ ወጥ ናቸው።















