ቀጥታ, የዓለም ነዳጅ ዋጋ ሲጨምር ትራምፕ የኢራንን ኻርግ ደሴት ለመቆጣጠር እያሰቡ መሆኑን ተናገሩ

ዶናልድ ትራምፕ ለፋይናንሻል ታይምስ “ከኢራን የነዳጅ ዘይት ሊወስዱ” እና ምናልባትም የአገሪቱ ዋነኛ የነዳጅ ማከፋፈያ ኻርግ ደሴትን ሊቆጣጠሩ እንደሚችሉ ተናገሩ። ትራምፕ ይህንን ሃሳባቸውን ሲያብራሩም “ምናልባት ኻርግ ደሴትን እንቆጣጠር ይሆናል። ምናልባትም አይሆንም ይሆናል። በጣም በርካታ አማራጮች አሉን” ብለዋል። ትራምፕ ይህንን ያሉት በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በጨመረበት ወቅት ነው።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ስድስት የእስራኤል ወታደሮች ሊባኖስ ውስጥ ጉዳት ደረሰባቸው

    የእስራኤል ጦርን እና ሄዝቦላህ በደቡባዊ ሊባኖስ የሚያደረጉትን ውጊያ ተከትሎ ቴል አቪቭ በአካባቢው ከፍተኛ ድብደባ እየፈጸመች ነው

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ጦርን እና ሄዝቦላህ በደቡባዊ ሊባኖስ የሚያደረጉትን ውጊያ ተከትሎ ቴል አቪቭ በአካባቢው ከፍተኛ ድብደባ እየፈጸመች ነው

    የእስራኤል ጦር ስድስት ወታደሮቹ በተለያየ ጊዜ በሊባኖስ ውስጥ ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታወቀ።

    በደቡባዊ ሊባኖስ በትናንትናው ዕለት ሁለት የእስራኤል ወታደሮች ጸረ ታንክ ከተተኮሰባቸው በኋላ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ጦሩ በሰጠው መግለጫ ገልጿል።

    የእስራኤል መከለከያ አክሎም የተተኮሰ ድሮን በአቅራቢያቸው የወደቀ ሦስት የጦሩ አባላት በተጨማሪ ጉዳት እንደደረሰባቸው እና አንዱ ከፍተኛ ጉዳት ማስተናገዱን ገልጿል።

    በተጨማሪም አንድ ወታደር “በዘመቻ ላይ በተፈጠረ አደጋ” ጉዳት የደረሰበት መሆኑን አስታውቆ ሁሉም ወታደሮች ወደ ሕክምና ተቋም ተወስደዋል ብሏል።

    እስራኤል በሊባኖስ ወታደራዊ ዘመቻ ዳግም የጀመረችው በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ ሮኬቶችን ወደ ሰሜናዊ እስራአል ማስወንጨፉን ተከትሎ ነው።

    ሄዝቦላህ የኢራኑ ጠቅላይ መሪ መገደላቸውን ተከትሎ ለቴህራን ያለውን አጋርነት ለመግለጽ በሚል ሚሳዔሎችን ማስወንጨፍ ጀምሯል።

    እስራኤል ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሊባኖስ ባካሄደችው ዘመቻ ከ1000 በላይ ሊባኖሳውያን መገደላቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል።

    እስራኤል በተጨማሪም ደቡባዊ ሊባኖስን የመቆጣጠር ፍላገት እንዳላት በመግለጽ በሄዝቦላህ ታጣቂዎች ላይ የእግረኛ ጦሯን አሰማርታለች።

    እስራኤል በቤይሩት በፈጸመችው የአየር ድብደባ የወደመ ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, እስራኤል በቤይሩት በፈጸመችው የአየር ድብደባ የወደመ ሕንጻ
  2. የቡድን ሰባት አገራት ሚኒስተሮች የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ላይ ሊወያዩ ነው

    የፈረንሳይ መንግሥት የቡድን ሰባት አገራት ሚኒስቴሮች ዛሬ ተገናኝተው በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ የሚገኘው ጦርነት የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ላይ እንደሚመክሩ አስታወቀ።

    እስራኤል እና አሜሪካ የካቲት 21 2018 ዓ.ም. በኢራን ላይ የከፈቱትን ጦርነት ተከትሎ ቴህራን በባሕረ ሰላጤው የሚገኙ አገራት እና መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ፈጽማለች።

    ይህም በመላው ዓለም የኤነርጂ አቅርቦት በማስተጓጎሉ የነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ ዋጋ ጨምሯል።

    ከዚህም አገር ተያይዞ የምግብ እንዲሁም የአፈር ማዳበሪያ እና ሌሎች ቁሳቁሶች ዋጋ ላይ ጭማሪ ይታያል የሚል ፍራቻ በየአገራቱ እየተስተዋለ ነው።

    የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር በበኩላቸው ዛሬ ከተለያዩ የንግድ ማኅበረሰቦች ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ተገናኝተው በጦርነቱ ተጽዕኖ ዙሪያ እንደሚነጋገሩ ተገልጿል።

    ኪር ስታርመር የሚያገኟቸው የቢዝነስ ማኅበረሰብ አባላት ከፍተኛ የኢነርጂ፣ የመርከብ ጭነት እና የፋይናንስ አገልግሎት ኃላፊዎችን መሆኑ ተጠቅሷል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢራን ጦርነት ዙሪያ በጽህፈት ቤታቸው ከንግድ ማኅበረሰቡ ጋር የሚያደርጉት ውይይት የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት ያስከተለው ኢኮኖሚያዊ ጫናን ያነሳሉ ተብሏል።

    በለንደን የሚገኝ ገበያ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

  3. ትራምፕ በኢራን ለረዥም ጊዜ ሲፈልጓቸው የነበሩ ዒላማዎች መመታታቸውን እና መውደማቸውን ተናገሩ

    እሁድ ዕለት በቴህራን የተፈጸመ ጥቃትን ተከትሎ የተነሳ እሳት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, እሁድ ዕለት በቴህራን የተፈጸመ ጥቃትን ተከትሎ የተነሳ እሳት

    ፕሬዚዳንት ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በኢራን የሚገኙ “በርካታ ዒላማዎች” መውደማቸውን ገለጹ።

    ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ “በኢራን ትልቅ ቀን ነው። ለረዥም ጊዜ ስንፈልጋቸው የነበሩ በርካታ ዒላማዎች በታላቁ፣ በዓለም ላይ ካለው ምርጡ እና አውዳሚው ጦራችን ተመትተዋል፤ ወድመዋል።

    ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ጦሩ በኢራን የሚገኙ ከ9 ሺህ በላይ ዒላማዎችን መደብደቡን ገልጾ ነበር።

  4. ትራምፕ 'ከኢራን ዩራኒየም ለማውጣት' ዘመቻ እያሰቡ ነው - ዎል ስትሪት ጆርናል

    የአሜሪካ ጦር ጄቶች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከኢራን 1,000 ፓውንድ ዩራኒየም ለማውጣት የሚያስችል ወታደራዊ ዘመቻ ለማካሄድ እያሰቡ ነው ሲል ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል።

    ስማቸው ያልተጠቀሱ የደህንነት ባለሥልጣናትን የሚጠቅሰው የዎል ስትሪት ዘገባ፣ ይህ ዘመቻ "የአሜሪካን ወታደሮች ለቀናት ወይም ከዚያ በላይ አገሪቱ ውስጥ ሊያስቆያቸው ይችላል።"

    ትራምፕ እስካሁን ውሳኔ ላይ ባይደርሱም ግን "ባለሥልጣናቱ እንደሚሉት፣ ሃሳቡ በአጠቃላይ ክፍት ነው፣ ምክንያቱም ይህ ሃሳብ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳትሰራ ለመከላከል ያላቸውን ዋና ዓላማ ለማሳካት ይረዳል።"

    ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡት ዋይት ሐውስንና ፔንታጎንን ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።

    ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው ወደ ክልሉ የተሰማሩ ወታደሮች "በኢስፋሃን የኑክሌር ጣቢያ ላይ በኢራን ከፍተኛ የበለፀገችውን ዩራኒየምን ለማነጣጠር በሚደረገው ተልዕኮ ላይ ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ" ነገር ግን እነዚህ ወታደሮች የዃርግ ደሴትን ለመያዝ ወይም የሆርሙዝን የባህር ወሽመጥ ለመጠበቅ ሊያገለግሉ ይችላሉ።

    ኒውዮርክ ታይምስ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ እንደዘገበው ትራምፕ "በኢስፋሃን ውስጥ በሚገኝ ተራራ ስር በብዛት ተከማችተው እንደሚገኙ የሚታመኑ ቦምብ ለማምረት የቀረቡ የኒውክሌር ቁሶችን ለመቆጣጠር እና ለማጥፋት" የሚያስችል ዘመቻ ለማካሄድ "በግልጽ እያሰቡ ነው"።

    ሁለቱም የዜና አውታሮች ዘመቻው ውስብስብ እና ከፍተኛ አደጋ እንደሚኖረው ይጠቁማሉ።

  5. አሜሪካ የኢራን ኻርግ ደሴትን ለመቆጣጠር ያሰበችው ለምንድን ነው?

    የኻርግ ደሴትን የሚያሳይ የሳተላይት ምስል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ትራምፕ ለፋይናንሻል ታይምስ እንደተናገሩት አሜሪካ በኢራን የባሐር ዳርቻ ላይ የምትገኘዋን አነስተኛ ደሴት፣ ኻርግን ልትቆጣጠር ትችላለች።

    አሜሪካ በደሴቲቱ ላይ ዓኗን የጣለችው የአገሪቱ ኢኮኖሚ የደም ስር የሆነው ነዳጅ ዋነኛ መተላለፊያ በመሆኑ ነው።

    አሜሪካ ደሴቲቱን በቁጥጥሯ ስር ብታውል የኢራንን የነዳጅ ሽያጭ ማስተጓጎል ብቻ ሳይሆን ወደ አገሪቱ ሰፋፊ አካባቢዎች ጥቃት ለመፈጸምም ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላታል።

    ደሴቲቱን መቆጣጠር የእስላማዊ ሪፐብሊክ አብዮታዊ ዘብ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ማቋረጥ ያስችላል፤ ይህም ጦርነት ለማካሄድ እንደሚያስቸግረው የደህንነት ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ማይኪ ኬይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    ደሴቲቱን ለመቆጣጠር የሚደረግ ማንኛውም የአሜሪካ ዘመቻ ትንሽ እንደሚሆን ይጠበቃል ያሉት ደግሞ የስኩል ኦፍ ዋር ፖድካስት አቅራቢ አሮን ማክሌን ናቸው።

  6. ትራምፕ በኢራን “የስርአት ለውጥ አድርገናል” አሉ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ ኤርፎርስ ዋን ላይ ሆነው በሰጡት ቃለ ምልስ ወቅት በኢራን የስርዓት ለውጥ ለማምጣት የነበራቸውን ፍላጎት አሳክቻለሁ ብለው እንደሚያምኑ ተናገሩ።

    ባለፈው ሳምንት በተመሳሳይ ለፎክስ ኒውስ “የስርዓት ለውጥ አድርገናል ማለት ትችላለህ ምክንያቱም ሁሉም ተገድለዋል” ብለው ነበር።

    አውሮፕላናቸው ላይ እየተሳፈሩ ለጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ የሰጡት ትራምፕ “በሚገባ ካየኸው ግን የስርዓት ለውጥ አድርገናል፤ ያለው ስርዓት ተመትቷል፤ ወድሟል። ሁሉም ሞተዋል። ቀጣዩም ስርዓትም አብዛኛው ሞቷል። ሦስተኛው ስርዓት ከዚህ በፊት እናነጋግራቸው ከነበሩት በተለየ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ነው እየተወያየን ያለነው፤ እጅጉን የተለየ ቡድን ነው፤ ስለዚህ ያንን የስርዓት ለውጥ አድርጌ እወስደዋለሁ። እውነቱን ለመናገር በጣም ምክንያታዊ ናቸው

    “ስለዚህ የስርዓት ለውጥ ያለ ይመስለኛል። ከዚያ የበለጠ ማድረግ አትችልም" ሲሉ ሃሳባቸውን አጠናክረዋል።

    ትራምፕ ለአንድ ወር በዘለቀው ጦርነት ውስጥ በርካታ የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት መገደላቸውን በመጥቀስም “የነበረው ስርዓት በጣም መጥፎ ነበር፤ ፍጹም ጨካኝ. . . ሁለተኛውም ተሾመ፤ እናም ሁሉም ተወገዱ፤ ሁሉም ሞተዋል፤ በውስጡ ትንሽ ትንፋሽ ከቀረችው በስተቀር” ብለዋል።

    ትራምፕ አክለውም ኢራን ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ላይ ትደርሳለች ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል።

    “ከስምምነት ላይ የምንደርስ ይመስለኛል፤ እርግጠኛ ነኝ፤ ግን ላንደርስ የምንችልበትም ዕድል አለ" ብለዋል።

    “ከኢራን ጋር ምን እንደሚሆን አታውቅም፤ ምክንያቱም እንደራደራለን እና ከዚያ እንደበድባቸዋለን” ሲሉ አክለዋል።

  7. ትራምፕ አሜሪካ “የኢራንን ነዳጅ ዘይት ልትወስድ’ እና ኻርግ ደሴትን ልትቆጣጠር ትችላለች አሉ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ዶናልድ ትራምፕ ለፋይናንሻል ታይምስ “ከኢራን የነዳጅ ዘይት ሊወስዱ” እና ምናልባትም የአገሪቱ ዋነኛ የነዳጅ ማከፋፈያ ኻርግ ደሴትን ሊቆጣጠሩ እንደሚችሉ ተናገሩ።

    “እውነቱን ለመናገር የምፈልገው ከኢራን የነዳጅ ዘይት መውሰድ ነው፤ ነገር ግን በዩኤስ ያሉ አንዳንድ የማይረቡ ሰዎች ‘ያንን ለምን ታደርጋለህ?’ ይላሉ። የማይረቡ ሰዎች ናቸው” ብለዋል።

    ትራምፕ ይህ እርምጃቸው ኻርግ ደሴትን መቆጠጣር ማለት ሊሆን እንደሚችልም ተናግረዋል።

    “ምናልባት ኻርግ ደሴተን እንወስድ ይሆናል። ምናልባትም አይሆንም ይሆናል። በጣም በርካታ አማራጮች አሉን” ሲሉ ለፋይናንሻል ታይምስ ተናግረዋል።

    “ምናልባትም እዚያ [ኻርግ ደሴት] ለተወሰነ ጊዜ እንቆያለን ማለትም ሊሆን ይችላል።”

    በደሴቲቱ ላይ ስላለው የኢራን መከላከያ ጦር ሲጠየቁም “ምንም ዓይነት መከላከያ ያላቸው አይመስለኝም። በቀላሉ ልንወስደው እንችላለን” ሲሉ ተናግረዋል።

    ፕሬዚዳንት ትራምፕ ይህንን ያሉት ተጨማሪ 3ሺህ 500 እግረኛ ጦር በመካከለኛው ምሥራቅ መድረሳቸው ከተነገረ እና በአካባቢው እያደገ የመጣው ውጥረት የአሜሪካ ጦርን ለኢራን ጥቃት የበለጠ እያጋለጠው ይሄዳል የሚል ስጋት ባደገበት ወቅት ነው።

    ትራምፕ በፓኪስታን አማካኝነት ከኢራን ጋር የሚካሄደው ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር በጥሩ ሀኔታ እየሄደ መሆኑን ተናግረዋል። ነገር ግን የተኩስ አቁም ስምምነት በቅርቡ ይደረስ እንደሆን ከመናገር ተቆጥበዋል።

    “ከስምምነት ላይ በፍጥነት ሊደረስ ይችል ይሆናል” ብለዋል።