ኢራን ጦርነቱን ለማስቆም የሚደረገው ስምምነት ሆርሙዝን ዳግም ለመክፈት ያስችላል አለች
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከአሜሪካ ጋር ጦርነቱን ለማስቆም የሚደረገው ድርድር ላይ ከስምምነት ለመድረስ መቃረባቸውን እና ሆርሙዝምን ዳግም ለማስከፈት የሚያስችል መሆኑን ተናገሩ።
ሰይድ አባስ አራጋቺ ለአገር ውስጥ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ስምምነቱ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ እንቅስቃሴ ላይ የተጣለው እገዳም እንዲነሳ ያደርጋል።
ነገር ግን በኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ላይ የሚደረገው ድርድር ከዚህ በኋላ እንደሚጀመር አስታውቀዋል።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት የስምምነቱ የተወሰኑ ዝርዝሮችን እውነተኛ መሆናቸውን አረጋግጠው የኢራን ምጣኔ ኃብታዊ ተጠቃሚነት ቴህራን ግዴታዎቿን በማክበሯ ላይ የተመሠረቱ ናቸው ብለዋል።
የኢራን ጦርነት የተጀመረው የካቲት 21 2018 ዓ.ም. እስራኤል እና አሜሪካ ድብደባ ከፈጸሙ በኋላ ነው።
ከዚያ በኋላ የዓለም አንድ አምስተኛ የነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ መተላለፊያ የሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ ሙሉ በሙሉ ተዘግቷል።
በሚያዚያ ወር በሁለቱ አገራት መካከል የተኩስ አቁም ቢደረስም ኢራን እና አሜሪካ ይህንን ሳምንት ጨምሮ አንዳቸው ሌላኛቸው ላይ ድብደባ ፈጽመዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሐሙስ ዕለት ኢራን ላይ ለመፈጸም “ታቅዶ የነበረውን ጥቃት” መሰረዛቸውን ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ ለምን እነደሰረዙት ሲያስረዱም ተደራዳሪዎች ሊፈረም የሚችል “ስምምነት ላይ ደርሰዋል” ብለዋል።
አርብ ዕለት የኢራን ብዙኃን መገናኛዎች ሁለቱ አገራት የሚደራደሩባቸውን ባለ 14 ነጥብ ሰነድ ውስጥ የተወሰነውን አጋርተዋል።
ትራምፕ ግን “ከተስማማንባቸው ነጥቦች ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም” እንዲሁም “ከእውነታው ጋር ምንም ትስስር የለውም” ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።
ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ደግሞ የአደራዳሪዋ ፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስት ሼህባዝ ሻሪፍ ሁለቱ አገራት እየተነጋገሩበት ያለው የመግባቢያ ሰነድ ላይ ከስምምነት ተደርሷል የመጨረሻ ጉዳዮች ብቻ እየተጠበቁ ናቸው ብለዋል።
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አራጋቺ በጠቅላይ ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ውስጥ የአዲሱ ስምምነት “ደጋፊዎች እና ነቃፊዎች” መኖራቸውን እንደገለጹ የአገሪቱ ብዙኃን መገናኛዎች ዘግበዋል።
ይሁን እንጂ የጋራ ውሳኔ ላይ አልደረሰንም ካሉ በኋላ “ለአሁኑ መጠበቅ ይኖርብናል። ስምምነቱ ከጸደቀ ከርቀት ይፈረማል” ሲሉ አክለዋል።
እስራኤል በአሜሪካ እና ኢራን ስምምነት ውስጥ ተሳታፊ አይደለችም። ለዓመታት ኢራን በምዕራባዊያን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ልትገነባ ነው የሚል ውንጀላ ሲቀርብባት ቆይቷል።
ኢራን በበኩሏ ፕሮግራሙ ለኤሌትሪክ ኃይል እና ለምርምር አገልግሎት ብቻ የሚውል ነው በማለት ስታስተባብል ነበር።