ቀጥታ, ሁቲዎች በየመንን ፕሬዚዳንታዊ ቤተ-መንግሥት ላይ በፈጸሙት ጥቃት አምስት ሰዎች ተገደሉ

የሁቲ ታጣቂዎች በኤደን በሚገኘው ፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግሥት ላይ በፈጸሙት የሚሳዔል ጥቃት አምስት ሰዎች መገደላቸውን እና 16 መቁሰላቸው ተገለፀ። የአገሪቱ ማስታወቂያ ሚኒስትር ሞአማር አል ኢራይኒ ለቢቢሲ አምስት ሚሳዔል መተኮሱን ገልጸው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እና ሌሎች ሚኒስትሮች ምንም ጉዳት አልደረሰባቸውም ብለዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ፊሊፒንስ ቀይ ሽንኩርት ላይ የዋጋ ንረት እንዲፈጠር አድርገዋል ያለቻቸውን “ስግብግብ ነጋዴዎች" 28 ሚሊዮን ዶላር ቀጣች

    ቀይ ሸንኩርት

    የፊሊፒንስ ባለሥልጣናት ስድሰት ኩባንያዎች የአትክልት ዋጋ እንዲንር አድርገዋል በሚል 27.9 ሚሊዮን ዶላር መቀጣታቸውን አስታወቁ።

    በፊሊፒንስ እንደ አውሮፓውያኑ በ2022 የአንድ ኪሎ ሽንኩርት ዋጋ 800 ፔሶ (12 ዶላር ገደማ) ገብቶ የነበረ ሲሆን ይህም የአንድ ኪሎ ስጋ ዋጋን በልጦ ነበር ተብሏል።

    ይህ የገበያ ቀውስ በወቅቱ የምግብ ዋጋን ለማረጋጋት ቃል ገብተው በተመርጡት ፕሬዚዳንት ፈርዲናንድ ማርኮስ ጁኒየር ላይ ጫና ፈጥሮ ነበር።

    ረቡዕ ዕለት የፊሊፒንስ የሸማቾች ኮሚሽን የሽንኩርት አስመጪዎች፣ መጋዘኖች እና የትራንስፖርት ኩባንያዎች ላይ ቅጣት መጣሉን አስታውቋል።

    እአአ ከ2022 መጨረሻ እስከ 2023 መጀመርያ ድረስ ሽንኩርት በገበያው ላይ ጠፍቶ የነበረ ሲሆን ነጋዴዎች በኮንትሮባንድ ለማስገባት ሲሞክሩ ታይቷል።

    በዋና ከተማዋ ማኒላ የሚገኙ ምግብ ቤቶች በሽንኩርት መጥፋት ምክንያት ሽንኩርት በርከት ብሎ የሚገባባቸው ምግቦችን ማቅረብ አቁመዋል። በተጨማሪም በርገር ላይ የሚጨመረው ሽንኩረት ለስሙ ጣል የሚደረግ ሲሆን፣ በአንዳንድ ቦታዎችም በርገር ከምግብ ከዝርዝራቸው ወጥቷል።

    ይህንን የሽንኩርት መጥፋት ለማካካስ አንዳንዶች ሌሎች አማራጮችን እየተጠቀሙ ነው። ለዚህም ጣዕሙ የተለመደው አይነት ሽንኩርት ያልሆነ፣ መጠኑም በጣም ትንሽ የሆነውን በፊሊፒንስ ውስጥ የሚታወቅ የተለየ ሽንኩርት ዝርያ ለመጠቀም ተገደዋል።

    ምግብን ለማጣፈጥ የሚያገለግለው ቀይ ሽንኩርት የሃብት ማሳያ ከመሆን አልፎ በሰርግ ቡፌ ላይ የሚቀመጥ የምግብ ዓይነት እስከመሆን ደርሶ ነበር።

    የፊሊፒንስ ፕሬዚዳንት ቀይ ሽንኩርት በአስቸኴይ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ያደረጉ ሲሆን እጥረቱ እንዲፈጠር አድርገዋል ያሏቸውን አካላት “ፊሊፒናውያን በረሃብ እና ድህነት እንዲያልቁ ለማድረግ ሞክረዋል” ሲሉ ኮንነዋል።

    በ2023 መጨረሻ ላይ የተፈጠረው እጥረት የተፈታ ሲሆን ዋጋውም ተረጋግቷል።

    የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርቶች ባለሙያ የሆኑት ሲንዲ ራይስዊክ እጥረት ከመከሰቱም በፊት ፊሊፒንስ ከምታመርተው በላይ የምትጠቀም እና ሽንኩርትን ከውጭ የምታስገባ አገር ናት ብለዋል።

    የዋጋ ቀውሱ የተፈጠረበትን ምክንያት አንዲያጠና የተቋቋመው የፓርላማ ኮሚቴ የዋጋ ንረቱ “ሰው ሠራሽ” በሆነ ምክንያት መፈጠሩን አረጋግጧል።

    ኮሚቴው በኩባንያዎቹ መጋዘኖች ላይ ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ ስድስት ኩበንያዎች 50 በመቶ የአገሪቱን የሽንኩርት ገበያ እንደሚቆጣጠሩ አረጋግጫለሁ ብሏል።

    ኩባንያዎቹ “በሕገወጥ ገበያ ስርጭት፣ ማከማቸት እና ማከፋፈል” ላይ ተሰማርተዋል ብሏል።

    የሸማቾች ኮሚሽኑ አክሎም ኩባንያዎቹ በወንጀል ሊጠየቁ አንደሚችሉ ገልጿል።

  2. ትራምፕ ኢራን ላይ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንደማይጠቀሙ ተናገሩ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንማይጠቀሙ ገልጸው “የቦምቦች ሁሉ እናት” የሚባለው ኒውክሌር አለመሆኑን ተናገሩ።

    ሐሙስ ዕለት ከኒውስማክስ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ወቅት አስተዳደራቸው በኢራን ላይ ለመጠቀም እያሰበ ስላለው ‘የቦምቦች ሁሉ እናት’ የተጠየቁት ፕሬዚዳንቱ መደበኛ የጦር መሣሪያ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

    “የቦምቦች ሁሉ እናት ኒውክሌር አይደለም” ያሉት ትራምፕ “ግዙፍ ቦምብ ነው” ሲሉ መልሰዋል።

    ፕሬዚዳንቱ በቃለ ምልልሱ ወቅት አስተዳደራቸው በኅዳር ወር ከሚካሄደው የአጋማሽ ዘመን ምርጫ በኋላ በኢራን ላይ ለመጠቀም ያቀደው ቦምብ ኒውክሌር አለመሆኑን በድጋሚ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

    “የቦብሞች ሁሉ እናት ትልቅ ቦምብ ነው፤ ኒውክሌር አይደለም” ብለዋል።

    ትራምፕ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን መጠቀምን ውድቅ ያደረጉ ሲሆን፣ አሜሪካ ወደዚህ አማራጭ መሄድ አያስፈልጋትም ብለዋል።

    "አይ፣ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ አልጠቀምም። ያንን ማድረግ አያስፈልገን፣" ሲሉ ተናግረዋል።

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ይታመኑ እንደሆነ ተጠይቀው፣ ትራምፕ "እውነቱን ለመናገር፣ ማንም ሰው አላምንም. . . በፖለቲካው ዓለም ውስጥ፣ ማንንም ሰው አላምንም" ብለዋል።

  3. ሁቲዎች በየመንን ፕሬዚዳንታዊ ቤተ-መንግሥት ላይ በፈጸሙት ጥቃት አምስት ሰዎች ተገደሉ

    የሁቲ ታጣቂ

    ሁቲዎች ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የየመን መንግሥት መቀመጫ በሆነው እና በኤደን በሚገኘው ቤተ መንግሥት ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተናገሩ።

    የሁቲ ታጣቂዎች በኤደን በሚገኘው ፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግሥት ላይ በፈጸሙት የሚሳዔል ጥቃት አምስት ሰዎች መገደላቸውን እና 16 መቁሰላቸው ተገልጿል።

    የአገሪቱ ማስታወቂያ ሚኒስትር ሞአማር አል ኢራይኒ ለቢቢሲ አምስት ሚሳዔል መተኮሱን ገልጸው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እና ሌሎች ሚኒስትሮች ምንም ጉዳት አልደረሰባቸውም ብለዋል።

    በየመን ወደብ ከተማ ኤደን የሚገኘው እና የመንግሥት መቀመጫ የሆነው ቤተ መንግሥት አቅራቢያ ሐሙስ ዕለት ቢያንስ ስድስት ፍንዳታዎች መከሰታቸውን የዐይን እማኞች ተናግረዋል።

    በኢራን በሚደገፉት የሁቲ አማፂያን እና በሳዑዲ አረቢያ በሚመራው ጥምረት መካከል የሚካሄደው ግጭት እየተባባሰ ከመጣ ወዲህ በቤተ መንግሥቱ አካባቢ የተፈጸመው ይህ ጥቃት ያልተለመደ ክስተት ነበር።

    ፍንዳታዎቹ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤ የፈጠሩ ሲሆን አካባቢውን ለቅቀው እንዲሸሹም አድርጓል።

    የየመን ጤና ሚኒስትር ቃሲም ቡሃይቤህ በበኩላቸው ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል የቤተመንግሥቱ ጥበቃዎች እና ሌሎች ሠራተኞች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ሻያ ዚንዳኑ “ጭካኔ የተሞላበት” ያሉትን ጥቃት አውግዘው ሁቲዎች “የወንጀል ባህሪያቸውን ቀጥለውበታል’ ብለዋል።

    በኤደን ከተማ የሚገኘው የሳባ የዜና ወኪል በበኩሉ መንግሥት ሁቲዎች በሚሳዔሎች እና በድሮኖች ጥቃት መፈጸማቸውን መናገሩን ዘግቧል።

    አንድ የጸጥታ ባለሥልጣን እንደገለጹት፣ ቢያንስ ሁለት ፍንዳታዎች በማሺቅ ቤተ መንግሥት አቅራቢያ በሚገኘው ኮረብታ ላይ የተከሰቱ ሲሆን፣ ሌሎች ሁለት ፍንዳታዎች ደግሞ የጸጥታ አካላት መግቢያ በር አካባቢ ተፈጽመዋል።

    አብዛኛዎቹ የየመን መንግሥት ኃላፊዎች በስደት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ በኤደን ከተማ ያሉት ደግሞ ደህንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን ተናግረዋል።

    በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተሰራጨ የሚገኝ እና አሶሼትድ ፕሬስ ትክክለኛነቱን ያረጋገጠው አንድ ቪዲዮ ቤተ መንግሥቱ በሚገኝበት አካባቢ ጭስ ሲወጣ ያሳያል።

    ሁቲዎች የሳዑዲ ጦር ዘመቻ ዋና መምሪያ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን አስታውቀዋል።

    ይህ የአማፂያኑ እርምጃ በሳዑዲ አረቢያ ግዛት ውስጥ በሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎችና የነዳጅ መሠረተ ልማቶች ላይ የፈጸሙት ተከታታይ ጥቃቶች አካል መሆኑን አስታውቀዋል።

    ከዓለማችን ዋና ዋና የነዳጅ ላኪ አገራት አንዷ የሆነችው ሳዑዲ አረቢያ ተደጋጋሚ ጥቃቶች እየደረሱባት በመሆኑ የኢራንን ጦርነት ለማስቆም የሚደረጉ ጥረቶችን አወሳስቦታል።

    አማፂያኑ አየር መንገዶች የሳዑዲ አረቢያን የአየር ክልል እንዳይጠቀሙ ማስጠንቀቂያ በመስጠታቸው፣ በክልሉ የሚደረጉ የአየር ጉዞዎችም ተስተጓጉለዋል።

    ፍላይት ራዳር 24 ወደ ጂዳ አውሮፕላን ማረፊያ የሚደረጉ በርካታ በረራዎች መሰረዛቸውን አስታውቋል።

  4. ትራምፕ ባልደረቦቹን የገደለው የቀድሞ የአሜሪካ ወታደር የሞት ቅጣት በቀጥታ እንዳይተላለፍ ወሰኑ

    የኒዳል ሐሰን ፎቶግራፍ
    የምስሉ መግለጫ, እአአ በ2012 ባለሥልጣናት ያሰራጩት እና ቀኑ ያልተገለጸ የኒዳል ሐሰን ምስል

    የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀድሞው የአሜሪካ ወታደር ኒዳል ሃሳን 13 ባልደረቦቹን በመግደሉ የተፈረደበት የሞት ቅጣት ሲፈጸም በቀጥታ እንዳይተላለፍ ወሰኑ።

    ከዚህ ቀደም ትራምፕ የሞት ቅጣቱ ሲፈጸም በቀጥታ እንዲታላለፍ ፈቅደው እንደነበር ገልጸዋል።

    አንድ የመከላከያ ሚኒስቴር ባለሥልጣንም ባልደረቦቹን በገደለው ኒዳል ሐሰን ላይ በተኩስ የሚፈፀመውን የሞት ቅጣት ሕዝብ በቀጥታ እንዲከታተል ይደረጋል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

    ነገር ግን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጄዲ ቫንስ የቀጥታ ስርጭቱ ስለመካሄዱ ጥርጣሬ እንዳላቸው ገልጸው እርሳቸው ግን እንደማይመለከቱ ተናግረዋል።

    ከዚያ በኋላ የሞት ቅጣቱ ሲፈጸም በቀጣታ ይተላለፋል መባሉ በርካታ ትችቶችን አስከትሏል።

    ሐሙስ ዕለት ትራምፕ “በርካታ በጣም ጥሩ እና በጎ ዓላማ ያላቸው ሰዎች ሲገደል ላይመለከቱ ይችላሉ” ብለዋል።

    ትራምፕ አክለውም “የሞት ቅጣቱ አፈጻጸም በቀጥታ እንዲተላለፍ ማድረግ፤ አሜሪካ ከአሸባሪዎች እንዲሁም እንደ ሀሰን ካሉ “ቆሻሻ” ሰዎችን እንዴት እንደምትቀጣ ለዓለም ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል” ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

    “በተያዘለት ጊዜ በተኩስ እሩምታ ይገደላል፤ ነገር ግን ቅጣቱ ሲፈጸም በቀጥታ አይተላለፍም” ብለዋል።

    ሃሳን በቴክሳስ በሚገኝ ጦር ሰፈር እአአ በ2009 መሣሪያ ያልታጠቁ 13 የአሜሪካ ወታደሮችን ተኩሶ ሲገድል 32 ደግሞ አቁስሏል።

    ይህም በአሜሪካ ጦር ታሪክ ከ60 ዓመታት በኋላ የሚፈፀም የመጀመሪያው ወታደራዊ የሞት ቅጣት ይሆናል።

    ትራምፕ ግድያው ሲፈጸም የሟች ቤተሰቦች ተገኝተው ይመለከታሉ ብለዋል።

    “ፍትህ ሲፈጸም ሊመለከቱ ይገባል” ሲሉ አክለዋል።

    በሐሰን ላይ የሚፈፀመው የሞት ቅጣት በቴክሳስ ፎርት ሁድ እአአ ታኅሣሥ 3 ተግባራዊ እንደሚሆን የአሜሪካ ጦር አስታውቋል። ይህም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ በተኩስ የሚፈፀም የመጀመሪያው ወታደራዊ የሞት ቅጣት ይሆናል።

    ባለፈው ዓመት በ17 አገሮች ከ2,700 በላይ የሞት ቅጣቶች የተፈፀሙ ሲሆን፣ በይፋ ሕዝብ እየተመለከተ ቅጣቱን የፈፀሙት ሁለት አገሮች ብቻ ናቸው።

    የአምነስቲ ኢንተርናሽናል መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በ2025 በኢራን 11 በአፍጋኒስታን ደግሞ 6 የሞት ቅጣቶች በይፋ ተፈፅመዋል።

  5. ሄዝቦላህ በሊባኖስ መንግሥት የጦር መሣሪያዎች እንደተወረሱበት ገለፀ

    የሄዝቦላህ ወታደሮች

    አንድ የሄዝቦላህ አባል ባለፈው ሳምንት በሊባኖስ የጸጥታ ኃይል በቁጥጥር ስር የዋለው በመቶዎች ኪሎ ግራም የሚቆጠር ተቀጣጣይ ፈንጂ የቡድኑ መሆኑን ተናገሩ።

    በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ ትጥቁን እንዲፈታ የሊባኖስ መንግሥት ጫና እያደረገ ነው።

    ባለፈው ሳምንት የሊባኖስ ባለሥልጣናት ፈንጂ የጫነ ተሽከርካሪ በፍተሻ ኬላ ላይ ካስቆሙ በኋላ ሁለት ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውለዋል።

    በወቅቱ ባለሥልጣናቱ ተሽከርካሪው የማን እንደሆነ አልገለፁም። ነገር ግን ተቀጣጣይ ፈንጂው ለአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት ወይም በአገሪቱ ውስጥ አለመረጋጋትን ለመፍጠር ታቅዶ ነበር በሚል ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል።

    ሐሙስ ዕለት ለመገናኛ ብዙኃን አስተያየታቸውን የሰጡ የሊባኖስ ፓርላማ አባል፣ ሀሰን ፋድላላህ ሂዝቦላህ ፈንጂዎቹን እስራኤል ላይ ለመጠቀም አቅዶ ነበር ብለዋል።

    የእስራኤል ወታደሮች የተወሰነ የሊባኖስ ግዛትን እንደተቆጣጠሩ ናቸው።

    የሄዝቦላህ ባለሥልጣናት እና የሊባኖስ ደህንነት ምንጭ ለሮይተርስ እንደተናገሩት ባለፈው ሳምንት በመኪና ተጭኖ የተያዘው ፈንጂ የእስራኤል ወታደሮችን በድሮን ዒላማ ለማድረግ የተዘጋጀ ነበር።

    ፋድላላህ እንዳሉት ሄዝቦላህ መኪናው እና የተወረሰው ፈንጂ የእርሱ መሆኑን ለሊባኖስ የፀጥታ ሰዎች ወዲያውኑ አስታውቋል።

    አክሎም የተወረሰበት ጭነት እንዲመለስለት እና የታሰሩት ሰዎች እንዲቀቁ ጠይቋል።

    ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ ሄዝቦላህ ከየትኛውም ወታደራዊ አንቅስቃሴ እንዲታቀብ የሊባኖስ መንግሥት ውሳኔ አሳልፏል።

  6. በሆርሙዝ አቅራቢያ ሁለት መርከቦች ጥቃት ከተፈጸመባቸው በኋላ መስመጣቸው ተነገረ

    የነዳጅ ጫኝ መርከብ

    ባለፉት 24 ሰዓታት ሁለት መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ አቅራቢያ ጥቃት ከተፈጸመባቸው በኋላ መስመጣቸው ተነገረ።

    የባሕር ትራንስፖርት ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት ባለፉት አስር ቀናት በወሽመጡ ላይ የሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶቸ ቁጥር ጨምሯል።

    ኢረን በወደቦቿ ላይ አሜሪካ የጣለችው እገዳ መቀጠሉን ተከትሎ የምትፈጽመውን ጥቃት አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታውቃለች።

    የሲንጋፖርን ባንዲራ የምታውለበልበው እና ጂኤፍኤስ ፕራይድ የተባለችው እቃ ጫኝ መርከብ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ እየቀዘፈች ባለችበት ወቅት ጥቃት ደርሶባት መስመጧን የባሕር ትራንስፖርት ደህንነት ምንጮች ተናግረዋል።

    መርከቧ ጥቃት ከደረሰባት በኋላ 21 ሠራተኞቿን ማትረፍ መቻሉን ጨምሮ ገልጸዋል።

    በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ ምንም ዓይነት ጉዳት አለመመዝገቡን ምንጮቹ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

    በሌላ ጥቃት የአንቲጓ እና ባርባዶስ ባንዲራን የምታውለበልብ መርከብ ጥቃት ከደረሰባት ከሳምንት በኋላ መስመጧን የመንግሥታቱ ድርጅት የመርከብ ትራንስፖርት ኤጀንሲ አስታውቋል።

    አንድ የመርከቧ ሠራተኛ ሲገደል ቀሪዎቹ ባህረተኞች መትረፋቸውን ምንጮች ጨምረው ተናግረዋል።

    የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በደረሰባቸው ጥቃት የሰመጡ መርከቦች ቁጥር ሦሰት ደርሷል።

  7. ዩክሬን በሩሲያ የነዳጅ ማጣሪያዎች ላይ ጥቃት መፈጸም እንደምትቀጥል አስታወቀች

    ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ

    ዩክሬን በሩሲያ የነዳጅ ማጣሪያዎች ላይ ጥቃቷን እንደምትቀጥል ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ተናገሩ። ዜሌንስኪ ዩናይትድ ስቴትስ ለአገራቸው ትሰጥ የነበረውን ወሳኝ መረጃ አቋርጣለች ሲሉም ከስሰዋል።

    የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት በሞስኮ ላይ የሚፈጽሟቸውን ጥቃቶች ለሦስት ቀናት በዋሽንግተን ትዕዛዝ የተነሳ ማስቆማቸውን አስታውሰው፣ ሩሲያ ግን የኢነርጂ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃቶችን መፈጸሟን ቀጥላለች ብለዋል። "አሁን በቅቶናል" ሲሉ ለፋይናንሺያል ታይምስ ተናግረዋል ።

    ዜሌንስኪ በተጨማሪም አሜሪካ ከሩሲያ የናፍጣ ዘይት ለማስገባት ስምምነት ላይ ከደረሰች በኋላ ስለሞስኮ ጥቃቶች ለኪየቭ የምትሰጠውን የደህንነት መረጃ ማቋረጧን በመግለጽ ከስሰዋል።

    የዩክሬን ጦር ኃይል በሚጠቀምባቸው የስታርሊንክ የሳተላይት አገልግሎቶች ላይ የተጣሉት ገደቦች ሆን ተብሎ የተፈጸሙ መሆናቸውን በመጥቀስ ተናግረዋል።

    ክሬምሊን ዩክሬን ሐሙስ ዕለት ከሞስኮ በስተደቡብ በሚገኝ የነዳጅ ማጣሪያ ላይ "ከፍተኛ ጥቃት ለመፈጸም ሞክራለች" ብሏል።

    የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው አራት ሚሳኤሎች እና በርካታ ድሮኖች ከሽፈዋል፤ የወደቁት ስብርባሪዎችም በራያዛን አካባቢ የእሳት ቃጠሎ አስከትለዋል።

    በሌላ በኩል ዜሌንስኪ ባለፉት ቀናት በርካታ የዩክሬን ከተሞች በሩሲያ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ገልጸዋል።

    ቀደም ሲል ሞስኮም ይህንኑ ተግባራዊ ካደረገች የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እሁድ ዕለት ባወጡት "የኃይል ተኩስ አቁም" ላይ እንደሚስማሙ ተናግረዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሩሲያ እና ዩክሬን "የኤነርጂ ተኩስ አቁም" ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀው ነበር።

    የዩክሬኑ ፕሬዚደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ሩሲያ የምትደግፈው ከሆነ በተኩስ አቁሙ እንደሚስማሙ ቢገልጹም ሩሲያ ግን ወዲያውኑ ጥቃቶችን ፈጽማ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዩክሬናውያንን ያለ ኤሌትሪክ አቅርቦት አስቀርታለች።

    ክሬምሊን በትራምፕ የኤነርጂ ተኩስ አቁም ስለመስማማቱ ያለው ነገር የለም።

  8. ኬንያ በነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ አደረገች

    ነዳጅ የሚሞላ ሞተረኛ

    ኬንያ የቤንዚን እና ነጭ ናፍጣ የመሸጫ ዋጋ ላይ ጭማሪ ማድረጓን የአገሪቷ የኢነርጅ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን አስታወቀ።

    ተቆጣጣሪ አካሉ የዋጋ ጭማሪ የተደረገው በመካከለኛው ምሥራቅ ባለው ጦርነት ምክንያት ነዳጅ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የሚወጣው ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ እንደሆነ ጠቅሷል።

    በዚህም የቤንዚን ዋጋ ቀድሞ ከነበረው በ6 በመቶ ሲጨምር የነጭ ናፍጣ መሸጫ ዋጋ ደግሞ የ4 በመቶ ጭማሪ ተደርጎበታል።

    በአዲሱ የዋጋ ማሻሻያ መሠረት አንድ ሊትር ቤንዚን ይሸጥበት ከነበረው 217.86 የኬንያ ሽልንግ (1.68 ዶላር) ወደ 227.76 ከፍ ብሏል።

    በሊትር በ191.38 ሽልንግ ይሸጥ የነበረው ነጭ ናፍጣ ደግሞ 219.87 ደርሷል።

    የኢነርጂ እና የነዳጅ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣኑ መንግሥት ከ16 ወደ 8 በመቶ ያወረደውን የነዳጅ ተጨማሪ እሴት ታክስ እስከ አውሮፓውያኑ ጥር 14 ድረስ እንደሚያራዝም አስታውቋል።

    የነዳጅ ዋጋ መናር ትራንስፖርት፣ ግብርና እና ኮንስትራክሽንን ጨምሮ በበርካታ ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል።

    ኬንያ ነዳጅ የምታስገባው ከባሕረ ሰላጤው አገራት በመሆኑ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ በኋላ አቅርቦት እና ዋጋ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አስከትሏል።

  9. በፓኪስታን የትምህርት ቤት ጣሪያ ተደርምሶ ቢያንስ 28 ተማሪዎችና አንድ መምህር ሞቱ

    የአደጋው ሥፍራ አካባቢ የቆመ አምቡላንስ እና የተሰባሰቡ ሰዎች

    በፓኪስታን ፔሽዋር ከተማ የሚገኝ ትምህርት ቤት ጣሪያ ተደርምሶ ቢያንስ 28 ተማሪዎች እና አንድ መምህር ሲሞቱ፣ 20 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የሆስፒታል ባለሥልጣናት ተናገሩ።

    የአደጋው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት አደጋው ሲደርስ ተማሪዎች ክፍል ውስጥ ነበሩ።

    በሥፍራው ያሉ የነፍስ አድን ሰራተኞችም ፍርስራሽ የተጫናቸው ሌሎች ሰዎች ካሉ እየፈለጉ ነው።

    አደጋውን ተከትሎ የትምህርት ቤቱ ባለቤት መታሰራቸውን ፖሊስ የገለጸ ሲሆን ምርምራ እየተካሄደ ነው።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ሸህባዝ ሻሪፍ በሰጡት መግለጫ በደረሰው ጉዳት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማቸው ገልጸው፤ ለተጎጂ ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝተዋል።

    በፓኪስታን የጣሪያ እና የሕንጻ መደርመስ አደጋ የተለመደ ነው።

    እንዲህ ዓይነት አደጋዎች የሚያጋጥሙት ሕንጻዎች የደኅንነት ደረጃቸውን ባለመጠበቃቸው እና ጥራት የሌለው የግንባታ ቁሳቁሶችን ስለሚጠቀሙ ነው።

    ያለፈው ሰኔ ወር ላይ በላሆር ከተማ የአንድ የትምህርት ማዕከል ጣሪያ ፈርሶ ከ12 በላይ ሕፃናት ሞተዋል።

    እአአ በ2025 እንዲሁ በካራቺ አካባቢ ባለአምስት ወለል ሕንጻ ተደርምሶ 27 ሰዎች ሲሞቱ 10 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።

  10. የትራምፕ አስተዳደር በሩሲያ የነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ለማላላት እያሰበ መሆኑ ተዘገበ

    የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ‘ሻዶው ፍሊት’ በመባል በሚታወቁት የነዳጅ ዘይት እና ናፍጣ ምርቶችን በሚያጓጉዙ መርከቦች ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ለማላላት እያጤነ መሆኑን ሮይተርስ ዘገበ።

    እነዚህ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች እንደ ሩሲያ እና ኢራን ካሉ ማዕቀብ ከተጣለባቸው አገራት በምስጢር ነዳጅ የሚያጓጉዙ ናቸው።

    አብዛኞቹ እነዚህ መርከቦች ንብረትነታቸው የማን እንደሆነ እና የመድን ዋስትና የቱ ኩባንያ እንደሰጣቸው አይታወቅም።

    ሮይተርስ አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ የአሜሪካ ባለሥልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው አስተዳደሩ አሁን ላይ ማዕቀቡን ለማላላት እያሰበ ያለው በዓለም ላይ ያጋጠመውን ያልተጠበቀ የነዳጅ ዋጋ ንረትን ለመቀነስ እና አቅርቦቱን ለማሻሻል ነው።

    በመሆኑም አስተዳደሩ ማዕቀብ የተጣለባቸው መርከቦች ነዳጅ እንዲያጓጉዙ ለመፍቀድ እያሰበ መሆኑን ባለሥልጣኑ ተናግረዋል።

    የአሜሪካ የኢነርጂ ኃላፊ ክሪስ ራይትም በሳዑዲ አረቢያ ለተካሄደው የዓለም የፔትሮሊየም ጉባኤ በላኩት እና በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተጋራ የቪዲዮ መልዕክት የአሜሪካ መንግሥት 'በሻዶው ፍሊት' ላይ የጣለውን ማዕቀብ ለማላላት እየተወያየ መሆኑን ገልጸዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዚደንት ትራምፕ ከቀናት በፊት በሩሲያ ላይ ናፍጣ ላይ የጣሉትን ማዕቀብ በጊዜያዊነት አንስተዋል።

    ውሳኔያቸው ከዩክሬን ፕሬዚደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ፣ ከአውሮፓ አገራት እና ከአንዳንድ የትራምፕ ሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት ትችት ገጥሞታል።

  11. ለ12 ዓመታት የተጓተተው ከቻይና ወደ ሰሜን ኮሪያ የሚወስደው ድልድይ ተከፈተ

    3 ኪሎሜትር የሚረዝመው ድልድይ ዋነኛ የንግድ መስመር እንደሚሆን ይጠበቃል
    የምስሉ መግለጫ, 3 ኪሎሜትር የሚረዝመው ድልድይ ዋነኛ የንግድ መስመር እንደሚሆን ይጠበቃል

    በቻይና እና ሰሜን ኮሪያ መካከል ያለው የንግድ ግንኙነት መሻሻሉን ተከትሎ ሁለቱን አገራት የሚያገናኘው ድልድይ መከፈቱ ተገለጸ።

    በኒውክሌር መሣሪያ ምክንያት ዓለም አቀፍ ማዕቀቦች የተጣሉባት ሰሜን ኮሪያ ዋነኛ የንግድ አጋሯ ቻይና ሆናለች።

    3 ኪሎሜትር የሚረዝመው ድልድይ ዋነኛ የንግድ መስመር እንደሚሆንም ይጠበቃል።

    በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ሲቀዛቀዝ በአውሮፓውያኑ 2014 ሰሜን ኮሪያ የመንገዱን ግንባታ አቋርጣለች።

    የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማኦ ኒንግ “ትስስር ለመፍጠር ጠቃሚ ነው። ንግድን እንዲሁም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ያሻሽላል” ሲሉ የድልድዩ መከፈት የሚኖረውን ጠቀሜታ ገልጸዋል።

    ባለፈው ዓመት በሁለቱ አገራት መካከል የነበረው የንግድ ልውውጥ 2.7 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።

    በሀንኩክ ዩኒቨርስቲ የቻይና የውጭ ጉዳዮች አጥኚ ካን ዩን-ዮንግ እንደሚሉት ግን የተባበሩት መንግሥታት በሰሜን ኮሪያ ላይ በጣለው ማዕቀብ መሠረት ድንበር አካባቢ ንግድ ሊከናወን የሚችልበት ዕድል ጠባብ ነው።

  12. አሜሪካ እና ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ማዳበሪያ እንዲያልፍ እንዲስማሙ ተመድ አሳሰበ

    ጭነት የያዘ መርከብ

    አሜሪካ እና ኢራን በቀጣይ ሳምንታት በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ማዳበሪያ እንዲያልፍ ካልተስማሙ የአፍሪካ እና እስያ የምግብ ደኅንነት አደጋ ውስጥ እንደሚገባ የተባበሩት መንግሥታት አስጠነቀቀ።

    ተመድ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ማዳበሪያ እንዲያለፍ የሚያመቻች ቡድን አዋቅሯል።

    የተባበሩት መንግሥታት ምክትል ዋና ጸሐፊ ሞሪራ ደ ሲልቫ እንደተናገሩት፤ ቡድኑ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ማዳበሪያ ማለፍ የሚችልበትን መንገድ ቀይሷል። አሜሪካ እና ኢራን ስምምነት ላይ ከደረሱ ከ7 እስከ 10 ባለው ቀን ውስጥ እንደሚተገበርም ገልጸዋል።

    ነገ የዓለም የምግብ ቀን ሲሆን፤ ምክትል ዋና ጸሐፊው በባንኮክ የሚካሄደውን የዓለም አቀፉ ገንዘብ ተቋም እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ውይይት እየታደሙ ይገኛሉ።

    በሰጡት ቃል ምልልስም “በቀጣይ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ የግድ ስምምነት ላይ መደረስ አለበት። ካልሆነ ግን ሰብል የሚዘራበት ወቅት ያልፋል” ብለዋል።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል ያነጋገራቸው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እንደገለጹት፤ የአሜሪካ ጦር በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል በሺህዎች የሚቆጠሩ መርከቦች እንዲያልፉ አግዟል።

    “ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ያለውን የመንቀሳቀስ ነጻነት ለማሰናክለ የምታደርገውን ጥረት ለማክሸፍ እርምጃ መውሰዳችንን እንቀጥላለን” ሲሉም ተናግረዋል።

    ባንኮክ ከሚገኘው የኢራን ኤምባሲ ምላሽ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም።

  13. ኬንያ በኢቦላ ቫይረስ የተያዘ ሁለተኛው ግለሰብ መገኘቱን አረጋገጠች

    የሕክምና ባለሙያ

    ኬንያ መነሻው ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ የሆነ አንድ ነጋዴ በኢቦላ ቫይረስ መሞቱ ከተረጋገጠ ከ10 ቀናት በኋላ ሁለተኛውን በቫይረሱ የተያዘ ሰው አገኘች።

    አሁን በቫይረሱ መያዙ የተረጋገጠው የ39 ዓመቱ ግለሰብ በቫይረሱ ከሞተው ግለሰብ ጋር የቅርብ ዘመድ ሲሆን በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንደነበር የኬንያ ጤና ሚኒስቴር ገልጿል።

    ሁለቱም በበሽታው የተያዙ ሰዎች ንክኪ ያላቸው እንደሆነ የገለጸው ሚኒስቴሩ፣ እስካሁን ድረስ ቫይረሱ ወደ ማኅበረሰቡ መሰራጨቱን የሚያሳይ መረጃ እንደሌለ ገልጿል።

    ሆኖም ማኅበረሰቡ እንዲረጋጋ፤ ነገር ግን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ሚኒስቴሩ አሳስቧል።

    መጀመሪያ በቫይረሱ የተያዘው የ40 ዓመቱ ኬንያዊ ህመም አጋጥሞት ናይሮቢ የሚገኝ ሆስፒታል ከገባ በኋላ ነበር ሕይወቱ ያለፈው።

    ከአውሮፕላን ማረፊያ ተቀብሎ ወደ ሆስፒታል የወሰደውም አሁን በቫይረሱ መያዙ የተረጋገጠው ግለሰብ ነበር።

    ግለሰቡ ወደ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተጉዞ የነበረ ሲሆን ምንም ምልክት ሳያሳይ ነበር በኡጋንዳ አድርጎ ወደ ኬንያ የገባው።

    የኢቦላ ቫይረስ ህመም ለማስከተል ከሁለት እስከ 21 ቀናት ድረስ ይወስዳል። ይህ ማለት አንድ በቫይረሱ የተያዘ ሰው ለበርካታ ሳምንታት ምልክት ሳያሳይ ሊቆይ ይችላል ማለት ነው።

    በመሆኑም ቀድሞ በሽታውን መለየት የመዳን እድል እንዲኖር እና ቫይረሱ ወደ ሌሎች ሰዎች እንዳይዛመት ያደርጋል።

    ግለሰቡ ሕይወቱ ካለፈ በኋላ ከእርሱ ጋር ንክኪ ያላቸው 128 ሰዎች ተለይተዋል።

    ከማክሰኞ ዕለት ወዲህ 113 የሚሆኑት መገኘታቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። ከእነዚህ መካከል 108 የሚሆኑት በኬንያ በለይቶ ማቆያ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ቀሪዎቹ እየተፈለጉ ነው።

    በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በዚህ ዓመት ብቻ ከ4000 በላይ ሰዎች በኢቦላ ቫይረስ ሞተዋል። ይህም እስካሁን ከተቀሰቀሱ ከባድ ወረርሽኞች ውስጥ ሁለተኛው ገዳይ አድርጎታል።

  14. በአንድ ጊዜ በአምስት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በመሥራት 350 ሺህ ፓውንድ ያገኘው ግለሰብ በማጭበርበር ተከሰሰ

    ተከሳሹ ክሶቹን አስተባብሏል

    በዩናይትድ ኪንግደም በአምስት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በመሥራት 350 ሺህ ፓውንድ ያገኘው ግለሰብ ፍርድ ቤት ቀረበ።

    ካሺም ቾውድሀሪ የተባለው ግለሰብ “ታምሜያለሁ” ብሎ ከአንዱ መሥሪያ ቤት ቀርቶ ወደ ሌላኛው በመሄድ እና “ከቤት ሆኜ ልሥራ” በሚል በማጭበርበር ተከስሶ ፍርድ ቤት ቀርቧል።

    ከአውሮፓውያኑ ጥር 2020 እስከ መስከረም 2023 ባሉት ዓመታት ለአምስት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሠርቷል።

    በሳውዝሀውክ ክራውን ፍርድ ቤት የቀረበው ካሺም፤ ከአለቃው ጋር በቪድዮ ሲነጋገር የታመመ ለመምሰል ነጭ መዋዋቢያ (ሜክ አፕ) ተቀብቶ ነበር ተብሏል። ሆኖም መዋዋቢያው ከፊቱ ላይ ለቅቋል።

    በምሥራቅ ለንደን የሚኖረው የ55 ዓመቱ ግለሰብ ዘጠኝ የማጭበርበር ክሶች ቢቀርቡበትም ጥፋተኛ አለመሆኑን ገልጿል።

    በውሸት ገንዘብ ለማግኘት ሞክሯል መባሉንም አስተባብሏል።

    ሆኖም ግን ሥራ ሲያመለክት ራሱን “በሐሰተኛ መንገድ ማቅረቡ” በፍርድ ቤት ተገልጿል።

    በዩኬ የአገር ውስጥ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፣ የአካባቢ ጥበቃ መሥሪያ ቤት፣ የምግብ እና የገጠር ጉዳዮች መሥሪያ ቤት፣ የጤና ደኅንነት መሥሪያ ቤት እና የጤና እና ማኅበራዊ ጥበቃ መሥሪያ ቤቶች በተመሳሳይ ወቅት ሠርቷል። በመሥሪያ ቤቶቹ እንደ ሙሉ ጊዜ ተቀጣሪ ሲከፈለው እንደነበር በፍርድ ቤቱ ተገልጿል።

  15. በቱርክ 4,700 ዓመት ያስቆጠረ የመርከብ ስብርባሪ ተገኘ

    በሸክላ የተሠሩ እቃ ማስቀመጫ ማሰሮዎች ባሕር ወለል ላይ ተገኝተዋል
    የምስሉ መግለጫ, በሸክላ የተሠሩ እቃ ማስቀመጫ ማሰሮዎች ባሕር ወለል ላይ ተገኝተዋል

    በዓለም ታሪክ ረዥም ዕድሜ ያለው የመርከብ ስብርባሪ በቱርክ ባሕር ዳርቻ መገኘቱን የቅሪተ አካል ተመራማሪዎች አስታወቁ።

    የመርከብ ስብርባሪው ከ4,400 እስከ 4,700 ዓመታት ያስቆጠረ እንደሆነ ተገልጿል።

    በነሐስ ዘመን (ብሮንዝ ኤጅ) መርከቡ እንደተሰባበረ ይታመናል። ይህ ዘመን ፒራሚዶች የተገነቡበት ነው።

    የመርከቡ እንጨታማ ክፍል ዘመን ተሻግሮ ባይተርፍም በሸክላ የተሠሩ እቃ ማስቀመጫ ማሰሮዎች ባሕር ወለል ላይ ተገኝተዋል።

    መርከቡ 10 ሜትር ርዝመት እንደነበረው የቅሪተ አካል ተመራማሪዎች ተናግረዋል።

    መርከቡ በሜድትራኒያን ባሕር ላይ የሚንቀሳቀስ የንግድ መርከብ ነበር።

    በቱርክ የአክዴንዝ ዩኒቨርስቲ ባለሙያ ፕ/ር ሀካን ኦኒዝ “የመርከቡ ስብርባሪ ከባሕር በታች የተገኘ ጊዜ ጠቋሚ ነው” ሲሉ ገልጸውታል።

    በዚያን ዘመን በባሕር መጓዝ አደገኛ ነበር። በተለይም ኬኮቫ ደሴት አካባቢ ባለው ጠንካራ ንፋስ ምክንያት መርከቦች ጉዳት ይደርስባቸው ነበር።

    አሰሳ በተካሄደበት አካባቢ በመቶዎች የሚቆጠሩ መርከቦች ስብርባሪዎች ተገኝተዋል።

  16. ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ የምታልፍ መርከብ በፈንጂ ተመትታ መስመጧን አስታወቀች

    የሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚገኙ መርከቦች

    በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ስትንቀሳቀስ የነበረች የጭነት መርከብ በፈንጂ ተመትታ መስመጧን የኢራን አብዮታዊ ዘብ ባሕር ኃይል አስታወቀ።

    ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ቴህራን መርከብ መስመጡን ስትናገር ይህ የመጀመርያዋ ነው።

    የመርከቧ ሠራተኞች ስላሉበት ሁኔታ የታወቀ ነገር የለም። የኢራን ብሔራዊ ቴሌቪዥን አብዮታዊ ዘቡን ጠቅሶ መርከቧ ረቡዕ ማለዳ እየቀዘፈች የነበረው ሕገ ወጥ እና አደገኛ በሚባል መስመር ላይ እንደነበር ዘግቧል።

    መርከቧ መጀመርያ በእሳት መያያዟ የተገለጸ ሲሆን 2 ሺህ 500 ኮንቴነሮችን መጫኗ ተገልጿል። ኢራን በተደጋጋሚ ያለ እርሷ ፈቃድ መርከቦች በወሽመጡ እንዳያቋርጡ አስጠንቅቃለች።

    የአሜሪካ ጦር በኦማን የባሕር ክልል በሚገኘው የወሽመጡ አካል መርከቦች እንዲያልፉ ከለላ ይሰጣል። ስለ መርከቧ መስመጥ በገለልተኛ ወገን የተረጋገጠ መረጃ የለም።

  17. በጀርመን አንዲት ታዳጊን አላግባብ ጎንትሏል የተባለ ሮቦት በፖሊስ ተያዘ

    ጥቁር ጺም፣ ወርቃማ ሰንሰለት እና ነጭ ልብስ ያደረገ ቀይና ወርቃማ ቀለም ያለው ሮቦት መሬት ላይ ተኝቶ ይታያል

    የጀርመን ፖሊስ ሮቦት ተጠቅመው በ16 ዓመቷ ታዳጊ ላይ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ፈጽመዋል በተባሉ ሁለት ታዳጊ ወጣቶች ላይ ምርመራ ጀመረ።

    የኮሎኝ ፖሊስ፣ የታዳጊዋን መቀመጫ አላግባብ ነክቷል የተባለውን ቀይ እና ወርቃማ ቀለም ያለው ሮቦት ወርሷል። ታዳጊዋ በድርጊቱ ተረብሻ በመጮህ ከቦታው መሸሿ ተገልጿል።

    የኖርዝራይን ዌስትፋሊያ ፖሊስ፣ የ16 ዓመቱ የሮቦቱ ባለቤት እና የ19 ዓመት ጓደኛው ክስተቱን በማኅበራዊ ሚዲያ በቀጥታ እያስተላለፉ አስተያየት ሲሰጡበት እንደነበር ይታመናል ብሏል።

    ፖሊስ በፌስቡክ ባወጣው መግለጫ፣ 120 ሴንቲ ሜትር ቁመት ያለው ሮቦቱ ቅዳሜ ዕለት እኩለ ሌሊት አካባቢ ታዳጊዋ ከጓደኞቿ ጋር ሳለች ከኋላዋ እንደቀረባት ገልጿል።

    ክስተቱ የተፈፀመው ልጃገረዷ በከተማው መሀል አካባቢ በሚገኝ ፈጣን ምግብ ቤት ፊት ቆማ ሳለች እንደሆነ የፖሊስ መረጃ ያመለክታል።

    የድንገተኛ ጊዜ አገልግሎት ስለጉዳዩ መረጃ ከደረሰው በኋላ፣ በምርመራ ላይ ያሉት ሁለቱ ወጣቶች ብዙም ሳይቆይ በአቅራቢያው ተገኝተዋል። ሮቦቱም በባለቤቱ መኪና የኋላ ክፍል መገኘቱን ፖሊስ ተናግሯል።

    ፖሊስ ያወጣው ፎቶ ሮቦቱ ጥቁር ጺም፣ ወርቃማ ቀለም ያለው ሰንሰለት እና ነጭ ልብስ ለብሶ ያሳያል።

    ፖሊስ ከሮቦቱ ጋር የተጠርጣሪዎቹን ሁለት ሞባይል ስልኮችም የያዘ ሲሆን በክስተቱ ወቅት ሆን ብለው የሮቦቱን እንቅስቃሴ እየተቆጣጠሩ እንደነበር ለማጣራት ምርመራ እያደረገ ነው።

    ፖሊስ አስከትሎ በፌስቡክ ገጹ ባስተላለፈው መልዕክት፣ ጉዳዩን በተመለከተ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰጡ አንዳንድ አስተያየቶች “ወሰን የሚያልፉ እና በከፋ ሁኔታም የወንጀል ድርጊት ሊሆኑ የሚችሉ” መሆናቸውን አስጠንቅቋል።

  18. የሩሲያ ጥቃት 600 ሺህ ዩክሬናውያንን ከኤሌክትሪክ ኃይል ውጭ ማድረጉን ዜሌንስኪ ተናገሩ

    የዩክሬን የሕይወት አድን ሠራተኞች ሩሲያ ምሽቱን ጥቃት በፈፀመችበት በኪየቭ የሚገኝ አንድ የመኖሪያ ሕንፃ ላይ እሳት ሲያጠፉ
    የምስሉ መግለጫ, የዩክሬን የሕይወት አድን ሠራተኞች ሩሲያ ምሽቱን ጥቃት በፈፀመችበት በኪየቭ የሚገኝ አንድ የመኖሪያ ሕንፃ ላይ እሳት ሲያጠፉ

    ሩሲያ ምሽቱን በፈፀመችው የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃት ምክንያት፣ በመላው ዩክሬን ቢያንስ 600 ሺህ ሰዎች ከኤሌክትሪክ ውጭ መሆናቸውን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ገለፁ።

    ዜሌንስኪ፣ በኪየቭ እና በዋና ከተማዋ ዙሪያ እንዲሁም በሰሜን ምሥራቃዊቷ ካርኪቭ ከተማ “ወሳኝ” የኃይል መሠረተ ልማቶች በጥቃቱ መመታታቸውን ገልፀዋል።

    ይህ ጥቃት የተፈፀመው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እሁድ ዕለት፣ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል “የኃይል መሠረተ ልማቶችን የሚመለከት የተኩስ አቁም” ተግባራዊ ሆኗል ካሉ በኋላ ነው።

    በኪየቭ ቢያንስ ሦስት ሰዎች ሲገደሉ 21 ሰዎች መጎዳታቸውን የዩክሬን መንግሥት የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ገልጿል።

    የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ፣ ሌሊቱን የተፈፀመው “መጠነ ሰፊ” ጥቃት በኪየቭ እና በካርኪቭ ክልሎች የሚገኙ የዩክሬን ጦር የሚጠቀማቸው የመገናኛ እና የኃይል ተቋማት ላይ ያነጣጠረ እንደነበር አስታውቋል።

    ሚኒስቴሩ አያይዞም፣ ዋና ከተማዋን ሞስኮ እና ሩሲያ በአውሮፓውያኑ 2014 በኃይል የያዘችውን ደቡባዊው የዩክሬን ባሕረ ሰላጤ ክሬሚያን ጨምሮ፣ በተለያዩ የሩሲያ ክልሎች ሌሊቱን 902 የዩክሬን ድሮኖች ተመትተው መጣላቸውን ገልጿል።

    የዩክሬን አየር ኃይል ደግሞ ሩሲያ ሌሊቱን ለፈፀመችው ጥቃት 39 ባለስቲክ እና ክሩዝ ሚሳዔሎችን እንዲሁም 128 ድሮኖችን ተጠቅማለች ብሏል። ከእነዚህም አራት ሚሳዔሎች እና 115 ድሮኖች መትቶ መጣሉን ገልጸዋል።

    ትራምፕ እሁድ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ “በሩሲያ እና በዩክሬን ጦርነት ውስጥ የኃይል መሠረተ ልማቶችን የሚመለከት የተኩስ አቁም ከአሁን ጀምሮ ተግባራዊ ሆኗል። ሁለቱም ወገኖች ተስማምተዋል። ስምምነቱን አትጣሱ!” ብለው ነበር።

    ይህን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ፣ ሞስኮ ተመሳሳይ እርምጃ የምትወስድ ከሆነ፣ ዩክሬን በሩሲያ የነዳጅ ማጣሪያዎች እና ሌሎች የኃይል ተቋማት ላይ የምትፈፅመውን ጥቃት ለማቆም ዝግጁ መሆኗን በተደጋጋሚ ተናግረዋል።

    ነገር ግን የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ፣ ዩክሬን የተኩስ አቁም የሚያስገኘው “የእፎይታ ጊዜ” እንደማይገባት ተናግረዋል።

    ማንኛውም የተኩስ አቁም ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ፣ አውሮፓ ዩክሬን ጦርነቱን እንድትቀጥል “ተጨማሪ መሣሪያዎችን በብዛት ማቅረብ” እንደሚችል አክለዋል።

    የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ የጀመሩት እአአ በ2022 ሲሆን በአሁኑ ወቅት ሞስኮ 20 በመቶ የሚሆነውን የዩክሬንን ግዛት ተቆጣጥራለች።

  19. ሳዑዲ አረቢያ ስደተኛው በፌስቡክ ገጹ ላይ በሰጠው አስተያየት የተነሳ የተጣለበትን የሞት ፍርድ ሰረዘች

    የ27 ዓመቱ አኖጃን ሲቫራሳ
    የምስሉ መግለጫ, የሞት ፍርድ ተፈርዶበት የነበረው የ27 ዓመቱ አኖጃን ሲቫራሳ

    የሳዑዲ አረቢያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፌስቡክ ላይ በሰጠው አስተያየት ምክንያት ሞት የተፈረደበትን ሲሪ ላንካዊ ስደተኛ ቅጣት መሰረዙን የሲሪ ላንካ ውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር አሩን ሄማቻንድራ አስታወቁ።

    የሳዑዲ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የ27 ዓመቱ አኖጃን ሲቫራሳ በመስከረም ወር በፌስቡክ ገጹ ላይ በሰጠው አስተያየት ላይ እስልምናን እና ነቢዩ መሐመድን ተሳድቧል በሚል የሞት ፍርድ ፈርዶበታል።

    የፍርድ ውሳኔው በሲሪ ላንካ ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሮ የነበረ ሲሆን ምህረት እንዲደረግለት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች እንዲጀመሩም ምክንያት ሆኗል።

    የሳዑዲ አረቢያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ረቡዕ ዕለት ፍርዱን ማንሳቱን ሄማቻንድራ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል። ምክትል ሚኒስትሩ በልጥፋቸው ላይ የሁለቱ አገራት ባለሥልጣናት እና የሕግ ቡድኖች ላደረጉት ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

    በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ አንድ ወጣት የሂንዱ ምዕመናንን የሚከተል ውሻን ሲማታ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ተጋርቶ የሃይማኖት ክርክር አስነስቷል።

    በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በነበረው ውይይት ወቅት አንድ ግለሰብ የሂንዱ አምላክን የሚያንቋሽሽ አስተያየት በመለጠፉ፣ ሲቫራሳ ነቢዩ ሙሐመድን በታሚል ቋንቋ እንዲሰድብ ምክንያት ሆኗል።

    ሲቫራሳ አስተያየቱን ወዲያውኑ ሰርዞ የይቅርታ ቪዲዮ ቢለጥፍም፣ ልጥፉን ስክሪን ሾት ያነሱ ሰዎች ቀጣሪዎቹ ጉዳዩን እንዲመለከቱ እና የሳዑዲ ባለሥልጣናት በሐምሌ ወር በቁጥጥር ሥር እንዲያውሉት አድርገዋል።

    ሲቫርሳ ላይ የቀረበው ክስ ከዚህ በኋላ በሌላ የሕግ ሂደት ስለመታየቱ ወይንም በእስር ላይ ስለመቆየቱ የተገለጸ ነገር የለም። ግለሰቡ መጀመሪያ ላይ በአል-አህሳ የወንጀል ፍርድ ቤት የአምስት ዓመት እስራት እንዲሁም ሦስት ሚሊዮን የሳዑዲ ሪያል ቅጣት ተፈርዶበታል።

    የሲቫራሳ ጉዳይን በተመለከተ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር በነበረው ድርድር ላይ የተሳተፉት የሲሪ ላንካ የሕግ አውጪ ፋይዘር ሙስጠፋ፣ ሳዑዲ አረቢያ የሞት ፍርዱን መሻሯን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

    የሲቫራሳ ቤተሰቦች እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከመስከረም 28 ጀምሮ ከእርሱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳልነበራቸው ተናግረዋል። ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ቡድኖችም ሳዑዲ የሞት ፍርዷን እንድታነሳ ጥሪ አቅርበዋል።

    ማክሰኞ ዕለት የሂዩማን ራይትስ ዎች ከፍተኛ ተመራማሪ ጆይ ሺአ "የሳዑዲ ባለሥልጣናት በተለይም ተጋላጭ በሆኑ ስደተኞች ላይ፣ ከንግግር ጋር በተያያዙ ጥፋቶች ላይ ያልተለመዱ የቅጣት ፍርዶችን ለመስጠት የሚጠቀሙባቸውን አላግባብ የሚተላለፉ ሕጎች ማቆም አለባቸው" ሲሉ ተናግረዋል።

  20. ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ በኢራን ላይ ግዙፍ ጥቃት ለመክፈት ተነጋገሩ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በሁለቱም አገራት ከሚጠብቁ ምርጫዎች በፊት በኢራን ላይ ግዙፍ እና አዲስ ዘመቻ ለመክፈት መነጋገራቸውን አክሲዮስ ዘገበ።

    ሁለት የአሜሪካ ባለሥልጣናት እና አንድ ስለ ውይይቱ የሚያውቁ ምንጮችን የጠቀሰው አክሲዮስ የመሪዎቹ ንግግር የተደረገው ትራምፕ የአጋማሽ ዘመን የአሜሪካ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ኢራን ላይ ጥቃት እንደማይፅሙ ከመናገራቸው በፊት ነው።

    ኔታኒያሁ የእስራኤል የደኅንነት መረጃ ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯን ዳግም ለመገንባት እየሰራች እንደሆነ መጠቆሙን እንዳነሱ አንድ ምንጭ ገልፀዋል።

    የዋይት ሐውስ ባለሥልጣን ሁለቱ መሪዎች ጦርነቱን ዳግም ለመጀመር ተነጋግረዋል መባሉን “ውሸት” ብለውታል።

    ለዚህም የጠቀሱት ትራምፕ በኅዳር ከሚደረገው ምርጫ በፊት ጥቃት መፈፀሙን ውድቅ ማድረጋቸውን ነው።

    የሁለቱም አገራት ወታደሮች በተጠንቀቅ ሲሆኑ ትራምፕ አቋማቸውን ከቀየሩ በሚል ዝግጅታቸውን እያጠናቀቁ እንደሆነም ምንጩ ተናግረዋል።

    አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን የትራምፕን አቋም ወላዋይ አድርገው የገለፁ ሲሆን፤ ምንም ቃል ሳይገቡ ኔታኒያሁ እንዲዘጋጁ እንደነገሯቸው ጠቁመዋል።

    እንደ ዘገባው ከሆነ ምንም እንኳ አብዛኞቹ አማካሪዎች ማዕቀብ እና ምጣኔ ሀብታዊ ጫናው እንዲቀጥል ፍላጎት ቢኖራቸውም የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት እና የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ መሪዎች ዳግም ጥቃት ለመጀመር ከፍተኛ ድጋፍ አሳይተዋል።

    የእስራኤል ጦር አዛዥ ሌተናንት ጀነራል እያል ዛሚር ለአሜሪካ ኃይሎች አዛዥ ጀነራል ዳን ኬን በሦስት ሣምንታት ውስጥ ግጭቱ ቢቀሰቀስ የእስራኤልን ምርጫ ሊያራዝም እንደሚችል መናገራቸው ተዘግቧል።

    የኳታር አሸማጋዮች አሜሪካ በቅርቡ ባቀረበችውን ግብረ መልስ ሰነድ ዙሪያ የኢራንን ምላሽ እየጠቁ መሆኑንም የአክሲዮስ ዘገባ አክሏል።