ፊሊፒንስ ቀይ ሽንኩርት ላይ የዋጋ ንረት እንዲፈጠር አድርገዋል ያለቻቸውን “ስግብግብ ነጋዴዎች" 28 ሚሊዮን ዶላር ቀጣች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የፊሊፒንስ ባለሥልጣናት ስድሰት ኩባንያዎች የአትክልት ዋጋ እንዲንር አድርገዋል በሚል 27.9 ሚሊዮን ዶላር መቀጣታቸውን አስታወቁ።
በፊሊፒንስ እንደ አውሮፓውያኑ በ2022 የአንድ ኪሎ ሽንኩርት ዋጋ 800 ፔሶ (12 ዶላር ገደማ) ገብቶ የነበረ ሲሆን ይህም የአንድ ኪሎ ስጋ ዋጋን በልጦ ነበር ተብሏል።
ይህ የገበያ ቀውስ በወቅቱ የምግብ ዋጋን ለማረጋጋት ቃል ገብተው በተመርጡት ፕሬዚዳንት ፈርዲናንድ ማርኮስ ጁኒየር ላይ ጫና ፈጥሮ ነበር።
ረቡዕ ዕለት የፊሊፒንስ የሸማቾች ኮሚሽን የሽንኩርት አስመጪዎች፣ መጋዘኖች እና የትራንስፖርት ኩባንያዎች ላይ ቅጣት መጣሉን አስታውቋል።
እአአ ከ2022 መጨረሻ እስከ 2023 መጀመርያ ድረስ ሽንኩርት በገበያው ላይ ጠፍቶ የነበረ ሲሆን ነጋዴዎች በኮንትሮባንድ ለማስገባት ሲሞክሩ ታይቷል።
በዋና ከተማዋ ማኒላ የሚገኙ ምግብ ቤቶች በሽንኩርት መጥፋት ምክንያት ሽንኩርት በርከት ብሎ የሚገባባቸው ምግቦችን ማቅረብ አቁመዋል። በተጨማሪም በርገር ላይ የሚጨመረው ሽንኩረት ለስሙ ጣል የሚደረግ ሲሆን፣ በአንዳንድ ቦታዎችም በርገር ከምግብ ከዝርዝራቸው ወጥቷል።
ይህንን የሽንኩርት መጥፋት ለማካካስ አንዳንዶች ሌሎች አማራጮችን እየተጠቀሙ ነው። ለዚህም ጣዕሙ የተለመደው አይነት ሽንኩርት ያልሆነ፣ መጠኑም በጣም ትንሽ የሆነውን በፊሊፒንስ ውስጥ የሚታወቅ የተለየ ሽንኩርት ዝርያ ለመጠቀም ተገደዋል።
ምግብን ለማጣፈጥ የሚያገለግለው ቀይ ሽንኩርት የሃብት ማሳያ ከመሆን አልፎ በሰርግ ቡፌ ላይ የሚቀመጥ የምግብ ዓይነት እስከመሆን ደርሶ ነበር።
የፊሊፒንስ ፕሬዚዳንት ቀይ ሽንኩርት በአስቸኴይ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ያደረጉ ሲሆን እጥረቱ እንዲፈጠር አድርገዋል ያሏቸውን አካላት “ፊሊፒናውያን በረሃብ እና ድህነት እንዲያልቁ ለማድረግ ሞክረዋል” ሲሉ ኮንነዋል።
በ2023 መጨረሻ ላይ የተፈጠረው እጥረት የተፈታ ሲሆን ዋጋውም ተረጋግቷል።
የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርቶች ባለሙያ የሆኑት ሲንዲ ራይስዊክ እጥረት ከመከሰቱም በፊት ፊሊፒንስ ከምታመርተው በላይ የምትጠቀም እና ሽንኩርትን ከውጭ የምታስገባ አገር ናት ብለዋል።
የዋጋ ቀውሱ የተፈጠረበትን ምክንያት አንዲያጠና የተቋቋመው የፓርላማ ኮሚቴ የዋጋ ንረቱ “ሰው ሠራሽ” በሆነ ምክንያት መፈጠሩን አረጋግጧል።
ኮሚቴው በኩባንያዎቹ መጋዘኖች ላይ ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ ስድስት ኩበንያዎች 50 በመቶ የአገሪቱን የሽንኩርት ገበያ እንደሚቆጣጠሩ አረጋግጫለሁ ብሏል።
ኩባንያዎቹ “በሕገወጥ ገበያ ስርጭት፣ ማከማቸት እና ማከፋፈል” ላይ ተሰማርተዋል ብሏል።
የሸማቾች ኮሚሽኑ አክሎም ኩባንያዎቹ በወንጀል ሊጠየቁ አንደሚችሉ ገልጿል።



















