ትራምፕን ያስፈነጠዘው የኢራን ስምምነት እና ያልተመለሱ ጥያቄዎች

የፎቶው ባለመብት, REUTERS/Stringer TPX IMAGES OF THE DAY
በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የነበረውን ጦርነት የሚቋጭ ስምምነት መበሰሩ ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የልደት ስጦታ ቢሆንም የተጠቀለለው ግን በአጠራጣሪ ወረቀት ነው።
በማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው ስምምነቱን ሲያሳውቁ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የሆርሙዝ ወሽመጥ ለንግድ መርከቦች እንደሚከፈት እና ዋሽንግተን የባሕር እግዷን እንደምታነሳ ገልፀዋል።
ትራምፕ እሑድ ዕለት "ነዳጁ ይፍሰስ" ሲሉ እፎይ ብለዋል።
የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች እንዳልተሳካላቸው በማነጻጸርም ያቀረቡት ትራምፕ፤ በአጠቃላይ ቀጣናው ሰላም እና ደኅንነት የሚያመጣ "ትልቅ ስምምነት" መድረሳቸውን ተናግረዋል።
እንደዚህ ዓይነት ግነት በእርግጥም ለትራምፕ አዲስ አይደለም። ባለፈው ጥቅምት የጋዛን ጦርነት ለማስቆም "ለሁሉም [ለቀጣናው] ዘላለማዊ ሰላም" እና "የእምነት፣ ተስፋ እና ፈጣሪ ዘመን ጅማሮ" ያሉት ስምምነትም እንዲሁ የተሞካሸ ነበር። መሬት ላይ ግን እውነታው ስምምነቱ ጠብ አለማለቱ ነው።
በእንደዚህ ዓይነት ከፍተኛ የዲፕሎማሲያዊ ስምምነት ስኬት እና ውድቀት በአመዛኙ በዝርዝሩ የሚገለፅ ነው። እናም በዚህ ስምምነት ላይ ዝርዝሩ ጥቂት ነው።
እሑድ ዕለት ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ኢራን መቼም የኒውክሌር የጦር መሣሪያ እንዳይኖራት ማድረግ "በዚህ ስምምነት የተካተተ ነው" እና አሜሪካ ስምምነቱ ስለመከበሩ ማረጋገጥ ትችላለች ብለዋል።
ይሁን እንጂ በኒውክሌር ማበልፀግ ላይ የሚጣለው ገደብ እና የቴህራን የበለፀገ እና የተከማቸ ዩራኒየም እጣ ፈንታን ጨምሮ በወሳኝ ጉዳዮች ላይ ጥያቄዎች ገና አልተመለሱም።
አብዛኞቹ እነዚህ ጉዳዮች ለ60 ቀናት በተራዘመው የተኩስ አቁም ስምምነት ውስጥ ቀጣይነት ባላቸው ድርድሮች እና "የቴክኒክ" ንግግሮች እንደሚሰራባቸው እሙን ነው።
ይሁን እንጂ ኢራን የኒውክሌር ፍላጎቷን እርግፍ አድርጋ እንድትተው ለአስርት ዓመታት የተደረጉ የውትወታ እና የጫና ጥረቶች የሚነግሩን በዚህ "የመግባቢያ ስምምነት" አሜሪካ አገኘሁ ብላ የምታምነው ውጤት ምንም ዋስትና እንደሌለው ነው።
እሑድ ዕለት የኢራን ጠቅላይ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ያወጣው መግለጫ "ሌላኛው ተደራዳሪ በመግባቢያ ስምምነቱ የገባቸውን ቃሎች እስኪተገብር ድረስ የመጨረሻው ድርድር ይራዘማል" ማለቱ ይህን አጉልቶ የሚያሳይ ነው።
እነዚህ ቃል ኪዳኖች ምን እንደሆኑ እና ኢራን እንዴት እንደምትተረጉማቸው ስምምነቱ እውን ስለመሆኑ የሚወስን ይሆናል።
የኃይል ዘርፍ ተንታኞች በሆርሙዝ ወሽመጥ ነዳጅ ማንቀሳቀስ ወዲያው ከጦርነቱ በፊት ወደነበረበት የመመለስ ሁኔታ እንደማይኖረው አስጠንቅቀዋል። የተከማቹ ግዙፍ ታንከሮችን ማንቀሳቀስ፣ የባሕር ፈንጂዎችን ማንሳት እና መደበኛውን የነዳጅ ዝውውር እና ምርት መመለስ ሳምንታትን ይወስዳል።
በይፋ ስምምነቱን ለመፈረም ጥቂት ቀናት ብቻ የቀሩ ሲሆን፤ ኢራን እና አሜሪካ የስምምነቱን ውጤት ለማረጋገጥ ቁልፍ ጉዳዮችን እልባት ለመስጠት ጊዜ አላቸው። ነገር ግን ሁሉም ነገር ለማክተምም ጊዜ አለ።
ሌላኛዋ አፍራሽ እስራኤል ናት።
ይህ ጦርነት ሁሌም ቢሆን የሦስት ወገን ነው። ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለዌል ስትሪት ጆርናል ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ሊባኖስ ላይ የጥቃት ትዕዛዝ በመስጠታቸው ለመጠናቀቅ ጫፍ ላይ የነበረውን የኢራን ስምምነት ሊያከሽፍ ይችላል በሚል እንዳስቆጣቸው ተናግረዋል።
ስምምነቱ ለሕዝብ ይፋ እስኪደረግ ድረስም የፀና ይመስላል። ነገር ግን እስራኤል ሊባኖስ ላይ አዲስ ወታደራዊ ዘመቻ የምትጀምር ከሆነ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግም ልትዘጋ እና የዓለምን ምጣኔ ሀብት በድጋሜ አደጋ ላይ ልትጥል ትችላለች።
ቫንስ በሰጡት አስተያየት ይህ ጦርነት በበርካታ አሜሪካዊያን ላይ በከፍተኛ የኃይል ዋጋ እና በምጣኔ ሀብቱ ላይ ያደረሰውን ጉዳት እውቅና ሰጥተዋል።
"ለአሜሪካዊያን ማስተላለፍ የምፈልገው የመጀመሪያ መልዕክቴ እናመሰግናለሁ የሚል ነው" ያሉት ቫንስ የኃይል ዋጋ መቀነስ እንደሚጀምር ቃል ገብተዋል።
ይህ በምን ያህል ፍጥነት እውን እንደሚሆን እና እጅ ባጠራቸው የአሜሪካ ሸማቾች ላይ በምን ፍጥነት እንደሚደርስ የኅዳሩ የሕግ አውጭዎች ምርጫ ላይ ተፅዕኖው ይታያል።
በቅርብ በተደረጉ የሕዝብ አስተያየት ድምፆች ትራምፕ እና ፓርቲያቸው የሕዝባቸውን ትዕግሥት እያጡ ነው፥ 'ዩገቭ' የተሰኘው የአስተያየት መስጫ መድረክ ባደረገው ቅኝት 63 በመቶ አሜሪካዊያን ዮፕሬዝዳንቱን የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ አይደግፉም፤ 57 በመቶዎቹ ደግሞ ምጣኔ ሀብቱ እየባሰበት ነው ብለው ያምናሉ።
የዕሁዱ ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ባይሆን እንኳ ቢያንስ በጦርነቱ ጫና ምክንያት የደረሰውን የምጣኔ ሀብት ችግር ለመቅረፍ ይረዳል። የነዳጅ ዋጋ እውነተኛ ቅናሽ ካሳየ ሁኔታዎች እየተቀየሩ ስለመሆኑ ለአሜሪካ ሕዝብ ተጨባጭ ምልክት ይሆናል።
ሁኔታዎች ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበሩበት መመለሳቸው ተጨባጭ እርምጃ ቢሆንም የትራምፕ ግዙፍ ግብ ለአሁኑ ከትልም ያልደረሰ እና በአገራቸው አሁንም ፖለቲካዊ አደጋ ሊገጥማቸው ይችላል።















