የትራምፕ 'ጎልደን ዶም' የሚሳዔል መከላከያ ሁሉንም ጥቃቶች መመከት እንደማይችል ተገለጸ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ "ጎልደን ዶም" የተሰኘው የሚሳዔል መከላከያ ሥርዓትን ለመገንባት፣ ለማሰማራት እና ለሁለት አስርት ዓመታት ጥቅም ላይ ለማዋል ከ1.2 ትሪሊየን ዶላር በላይ እንደሚያስወጣ ተገለጸ።

የፕሬዝዳንታዊ ዘመናቸው ከማብቃቱ በፊት "ሙሉ በሙሉ" ተግባራዊ" እንደሚሆን የተነገረው ይህ የሚሳዔል መከላከያ ሥርዓት መጀመርያ ላይ 175 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስወጣ ተገልጾ ነበር።

በመሬት፣ በባሕር እና በሕዋ ላይ ያሉ የ"ቀጣዩ ትውልድ" የቴክኖሎጂ መረብን፣ እንዲሁም አጥቂ ሚሳዔሎችን ለመከላከል ያለመ ሕዋ ላይ የተመሠረቱ አክሻፊ እና ጠቋሚዎች (ሴንሰር) ያካትታል የተባለው ይህ መሣሪያ የተባለውን ያህል ውጤታማ ላይሆን ይችላል ተብሏል።

አዲስ በወጣው ሪፖርት መሠረት አሜሪካን ከባሌስቲክ እና ክሩዝ ሚሳዔሎች ይከላከላል የተባለው ይህ መሣሪያ ለሩሲያ ወይም ቻይና ጥቃት የተጋለጠ ነው ተብሏል።

በአዲሱ ሪፖርት መሠረት ይህንን የመከላከያ ሥርዓት ለመታጠቅ ብቻ ከ1 ትሪሊየን ዶላር በላይ የሚያስወጣ ሲሆን ወጪው የማክሸፊያ መሣሪያዎቹን፣ ሕዋ ላይ የሚቀመጡ መከታተያ፣ አክሻፊ እና ጠቋሚዎችን እንደሚያካትት ተገልጿል።

ትራምፕ ሁለተኛው የሥልጣን ዘመናቸውን እንደጀመሩ ይፋ ያደረጉት ይህ መሣሪያ "የቀጣይ ትውልድን" የአየር ላይ ስጋቶችን ያስወግዳል ተብሎ ነበር።

በቅድሚያ 25 ቢሊዮን ዶላር ፈሰስ ለማድረግ ቃል የገቡት ፕሬዝዳንቱ አጠቃላይ ወጪው ወደ 175 ቢሊዮን ዶላር ገደማ እንደሚሆን ተገምቶ ነበር።

ዲሞክራቱ ሴናተር ጄፍ መርክሌይ ማክሰኞ ዕለት "የፕሬዚዳንቱ 'ጎልደን ዶም' የተባለው ይህ መሣሪያ ለመከላከያ ኮንትራክተሮች ከተራ የአሜሪካ ዜጎች የተገኘን ገንዘብ በግዙፍ ስጦታነት ከማስጠት በስተቀር ምንም ማለት አይደለም" ብለዋል።

ቢቢሲ ከፔንታጎን ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

አሜሪካ እንደዚህ ዓይነት ግዙፍ አካባቢን የሚሸፍን ሁሉን አቀፍ የመከላከያ ስርዓት መገንባት ትችል እንደሆነ ጥርጣሬዎች ነበሩ።

ባለሥልጣናት አሜሪካ አሁን ያሏት የመከላከያ ስርዓቶች ሊገዳደሯት የሚችሉ ጠላቶቿ ካሏቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተራቀቁ ከመጡ የጦር መሣሪያዎች ጋር እኩል እንዳልሆኑ አስጠንቅቀዋል።

ጎልደን ዶም የሚያስወጣው ወጪ ቢገመትም "ስርዓቱ ግን በአቻ ወይም ተቀራራቢ አቅም ያለው ጠላት በሚሰነዘረው ሙሉ ጥቃት ሊሸነፍ ይችላል" ሲል ሪፖርቱ አስታውቋል።

ሥርዓቱ እስራኤል ከ2011 ጀምሮ አገሪቱ ሮኬቶችን እና ሚሳዔሎችን ለማምከን እየተጠቀመችበት ያለውን አይረን ዶም በከፊል መነሻ ያደረገ ነው።

ጎልደን ዶም፣ ከአይረን ዶም በብዙ እጥፍ ይለያል የተባለ ሲሆን፣ ከድምጽ ፍጥነት በላይ የሚምዘገዘጉ ሃይፐርሶኒክ ጦር መሳሪያዎችን እና ፎብስ (FOBS ) በመባል የሚታወቀውን እና ወደ ዒላማው ለመወንጨፍ ዝቅተኛ የምድር ምህዋርን የሚጠቀመውን የጦር መሣርያ ሥርዓት ጨምሮ የተለያዩ ስጋቶችን ለመመከት የተነደፈ መሆኑ ተገልጿል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣናቸውን በተረከቡ በሰባተኛው ቀን የመከላከያ ሚኒስትራቸው የአየር ጥቃቶችን ለመከላከል እና ለመመከት የሚያስችል ሥርዓት ላይ ዕቅዳቸውን እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር።

በወቅቱ ዋይት ሐውስ አሜሪካ ፊት ለፊቷ የተጋፈጠችው "በጣም አስከፊ ስጋት" ሲል ገልጾት ነበር።

ትራምፕ የሚሳዔል የመከላከያ ሥርዓቱ ከመሬት፣ ከባሕር እና ከሕዋ ላይ የሚነሱ ጥቃቶችን መመከት የሚያስችል "የቀጣይ ትውልድ" ቴክኖሎጂዎችን ያቀፈ ነው ብለዋል።

አክለውም በሕዋ ላይ የሚቀመጡ ጠቋሚዎችን (ሴንሰሮችን) እና ማምከን የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን እንደሚያካትት ተናግረዋል።

ስፔስኤክስ እና ሎክሂድ ማርቲን ባለፈው ወር ሕዋ ላይ የሚቀመጥ ሚሳዔል ማምከኛ ስርዓት ለመስራት 3.2 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ኮንትራት አሸንፈዋል።