ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሩቢዮ ምን ተነጋገሩ?

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ጋር በስልክ መወያየታቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው አስታውቀዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትም ውይይት መካሄዱን በድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ አትቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "በሁለትዮሽ፣ በቀጣናዊ እና በባለብዙ ወገን የጋራ ትኩረትን በሚሹ ጉዳዮች ላይ እጅግ ፍሬያማ የሆነ የስልክ ውይይት አድርጌያለሁ" ሲሉ የውይይቱን ይዘት ገልጸዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ፤ ንግግራቸው "ከኤርትራ ጋር እየተባባሰ የመጣውን ውጥረት" የተመለከተ መሆኑ ተገልጿል።

"የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሁሉም ወገኖች በኩል ውጥረት ማርገብን ይደግፋሉ" ይላል መግለጫው።

ለውስጣዊ እንዲሁም ውጭያዊ ውጥረቶች ብቸኛው ዘላቂ መፍትሔ ውይይት መሆኑም ተመልክቷል።

ለዚህም በአውሮፓውያኑ 2018 በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ማዕቀፍ ተጠቅሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበኩላቸው ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ስላደረጉት ውይይት በጥቅል ከመግለጽ ባሻገር የተነጋገሩባቸውን ጉዳዮች በተመለከተ ዝርዝር ነገር አልገለጹም።

ከሩቢዮ ጋር ያደረጉት ውይይት፤ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን "ዕድሜ ጠገብ ወዳጅነት ወደላቀ ስትራቴጂካዊ እና ተግባራዊ አጋርነት ለማሳደግ በሁለቱም አገራት በኩል ያለውን ቁርጠኝነት ማረጋገጫ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን "ቀጣይነት ያለው ድጋፍ በተመለከተ የሰጠችውን ማረጋገጫ" እንደሚያደንቁ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጽሑፋቸው አመልክተዋል።

አያይዘውም "የሁለትዮሽ ትብብራችንን ለማጠናከር እንዲሁም በቀጣናዊ እና ባለብዙ ወገን መድረኮች ቅድሚያ በምንሰጣቸው የጋራ ጉዳዮች ላይ አብረን ለመሥራት ያለንን ቁርጠኝነት አረጋግጣለሁ" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሩቢዮ ጋር የስልክ ውይይት ያካሄዱት በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ጦርነት ባገረሸበት እንዲሁም ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወደ ጦርነት ሊገቡ ይችላሉ እየተባለ ባለበት ወቅት ነው።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ፤ ማርኮ ሩቢዮ "ሁሉም የአፍሪካ ቀንድ አገራት የጎረቤቶቻቸውን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማክበር አለባቸው" ማለታቸው ተጠቅሷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለውም አገራቱ "ድንበር ተሻጋሪ ወረራ እንዳይፈጽሙ" አሳስበዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ባደረጉት ውይይት "ቀጣናው ሌላ ግጭት መቋቋም አይችልም" ማለታቸው ተገልጿል።

ሁለቱ ባለሥልጣናት ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ማብቂያ ላይ "የአፍሪካ ቀንድ ሰላም" እና "ቀጣናዊ መረጋጋትን" በተመለከተ የስልክ ውይይት ማድረጋቸው መገለጹ ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከማርኮ ሩቢዮ ጋር መወያየታቸው የተሰማው በአሜሪካ ጥያቄ የመንግሥታቱ ድርጅት በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ስላላው ወቅታዊ ሁኔታ በዝግ ከተወያየ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።

በኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ግጭት እንዲቆም እንዲሁም በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረው ውጥረት ረግቦ ውይይት እንዲጀመር አሜሪካን ጨምሮ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በተደጋጋሚ ሲያሳስቡ ቆይተዋል።

በኢትዮጵያ፣ በግብፅ እና በኤርትራ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማቋረጡን እንዲሁም የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው መግባታቸው መዘገቡን ተከትሎ፤ ጦርነቱ ቀጣናዊ እንዳይሆን ስጋት ተፈጥሯል።

ጦርነቱ ዳግመኛ በተነሳበት ማግሥት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ የህወሓት አመራሮችን "መጠነ ሰፊ ጥቃት በመክፈት" መክሰሳቸው አይዘነጋም።

ኢትዮጵያ በኤርትራ "ወረራ" እንደተፈጸመባት እና ራሷን ከመከላከል ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌላት በመግለጽ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በደብዳቤ አሳውቃለች።

ኤርትራ በምላሹ ለምክር ቤቱ በጻፈችው ደብዳቤ "ኢትዮጵያ ራስን በመከላከል ስም ጦርነትን ምክንያታዊ ልታደርግ ነው" ስትል ከስሳለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከትናንት በስተያ በተመሳሳይ ከእስራኤሉ አቻቸው ቤንያሚን ኔታኒያሁ ጋር የስልክ ውይይት ማድረጋቸውን ማስታወቃቸው ይታወሳል።

ሁለቱ መሪዎች የስልክ ውይይት ከማድረጋቸው ከቀናት በፊት የአገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተመሳሳይ የስልክ ንግግር ማድረጋቸው አይዘነጋም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከኔታኒያሁ ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሳወቁበት ጽሑፍ ላይ እንዳሉት "በሁለቱ አገራት ግንኙነት እና በቀጣናዊ ጉዳዮች" ላይ ተነጋግረዋል።

ሁለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሮች "በጋራ ጉዳዮች ላይ" የሚያደርጉትን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር በድጋሚ ማረጋገጣቸውንም ጠቅሰዋል።

ባለፈው ሳምንት የእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳዓር ከኢትዮጵያው አቻቸው ጌዲዮን ጤሞቲዮስ (ዶ/ር) ጋር በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ በስልክ መወያየታቸውን አሳውቀው ነበር።

በውይይታቸው ስለኢትዮጵያ አንድነት እና መረጋጋት አስፈላጊነት እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና መረጋጋትን ለሁለቱ አገራት ስላለው የጋራ ጥቅም መነጋገራቸውን አመልክተዋል።

በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ የቅርብ አጋር የሆነችው ኢትዮጵያ በምጣኔ ሀብት፣ በወታደራዊ እና በሌሎችም ዘርፎች ጥብቅ ግንኙነት አላት።