ልጆችን በተለይ የሚያጠቃ ነው የተባለው አዲሱ የኮቪድ ዝርያ ምን ያህል አሳሳቢ ነው?

መሀረብ በእጇ ይዛ እያስነጠሰች ያለች ታዳጊ ልጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሕፃናት ከአዋቂዎች ይልቅ ቫይረስ የመከላከል አቅማቸው ዝቅተኛ ነው
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በ23 አገራት የተገኘው እና በከፍተኛ ሁኔታ እየተዛመተ ያለው የኮቪድ-19 ዝርያ በዓለም የጤና ድርጅት ክትትል እየተደረገበት ነው።

ዝርያው በይፋ 'ቢኤ.3.2' በሚል የሚጠራው ሲካዳ አሜሪካ፣ ሆንግ ኮንግ፣ ሞዛምቢክ እና ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ተገኝቷል።

ምንም እንኳ ይህ ዝርዝያ ከሌሎች በበለጠ አደገኛ ስለመሆኑ የሚያሳምን ምክንያት ባይኖርም ባለሙያዎች ሕፃናት ከአዋቂዎች ይልቅ በዚህ ቫይረስ እንደሚያዙ ጠቁመዋል።

ስለዚህ ምን ያህል መጨነቅ አለብን?

የሲካዳ ዝርያ ምንድን ነው?

ተህዋሱ 'ቢኤ.3.2' ዝርያ ሲካዳ ተብሎ የተሰየመበት ምክንያት በተመሳሳይ ስም እንደምትጠራው ትንኝ ቫይረሱ መጀመሪያ ከተገኘ በኋላ ለረጅም ጊዜ ተደብቆ የሚቆይ በመሆኑ ነው።

በአውሮፓውያኑ ኅዳር 2024 በደቡብ አፍሪካ መጀመሪያ ላይ የተገኘ ቢሆንም ክስተቶቹ የጨመሩት ግን ከዓመት ገደማ በኋላ ነው።

ባለፈው መጋቢት ወር የአሜሪካ የበሽታ ቁጥጥር ማዕከል (ሲዲሲ) በ25 ግዛቶች ቫይረሱ እንደተገኘ አስታውቋል።

ማዕከሉ ቫይረሱ ከአራት መንገደኞች አፍንጫ በተወሰደ ፈሳሽ፣ ከአምስት ታካሚዎች ናሙና እና ከቆሻሻ ውሃ ከተወሰዱ ናሙናዎች ውስጥ መገኘቱን ገልጿል።

የዓለም የጤና ድርጅት ቫይረሱን "ክትትል" ውስጥ እንዲገባ ያደረገ ሲሆን፤ ይህም ማለት "ቅድሚያ ትኩረት እንዲሰጠው" እና ለዓለም የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ይደቅናል የሚለው በአሁኑ ጊዜ እየተመረመረ ነው።

ሲካዳ ቅርንጫፍ ላይ ሆና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አዲሱ የኮቪድ ዝርያ ሲካዳ ከተባለችው ትንኝ ስያሜውን ወስዷል

ሕፃናት የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው?

የኮቪድ ዝርያዎች ተመራማሪ የሆኑት ራየን ሂስነር በኒው ዮርክ በበሽታውን ክስተት ትንተና መሠረት ሕፃናት ከአዋቂዎች በበለጠ በ'ቢኤ.3.2' ዝርያ የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑን ያመላክታል።

በኬምብሪጅ የጥናት ተቋም የተላላፊ በሽታዎች ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ራቪንድራ ጉብታ "በአቻ የተገመገመ ወይም የታተመ አይደለም፤ ነገር ግን እውነት ይመስላል" ሲሉ ስለ ትንተናው ተናግረዋል።

ይህ ለምን እንደሆነ የሚጠቁሙ የተለያዩ ፅንሰ ሀሳቦች አሉ። አንደኛው ሲካዳ እስካሁን አይተነው የምናውቀው ዝርያ ባለመሆኑ ለየትኛውም ሰው በሽታ የመከላከል ሥርዓት ከባድ መሆኑ ነው።

ፕሮፌሰር ጉብታ "በደፈናው ሕፃናት ከአዋቂዎች ያነሰ በሽታ የመከላከል አቅም አላቸው። ምክንያቱም የተለያዩ ቫይረሶች እና የኮቪድ ኢንፌክሽን አይተው ስለማያውቁ። እናም ለቫይረሱ ደካማ የመከላከል አቅም እንዳላቸው እንጠብቃለን" ብለዋል።

አዋቂዎችን ከቫይረስ የሚከላከሉ ፀረ እንግዳ አካላትን የሚያመርተው ዕጢ በጊዜ ሂደት ይጠነክራል እና ይህም የመከላከል አቅማቸውን ለማጠናከር ያግዘናል።

"ሕፃናት በዚህ የብስለት ሂደት ውስጥ ጥቂት ዓመታት ብቻ አሳልፈዋል። ስለዚህ ለቫይረሱ የበለጠ ለምን ተጋላጭ እንደሆኑ ይህ ሊያስረዳ ይችላል" ሲሉ ያክላሉ።

ሌሎች ተመራማሪዎች ደግሞ በሲካዳ ውስጥ ያለው በጣም ከፍተኛ የተለወጠ ፕሮቲን በልጆች ላይ ከሚከሰተው ኢንፌክሽን ጋር ሊያያዝ ይችላል ይላሉ።

ፕሮፌሰር ጉብታ እና ቡድናቸው ቫይረሱ ሕፃናትን በበለጠ ለምን እንደሚያጠቃ ለመለየት የሕፃናት ናሙናን ለጥናት እየፈለጉ ነው።

ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?

እስካሁን ባለው ሁኔታ ሲካዳ ከሌሎች የቫይረሱ ዝርያዎች በተለየ ሰዎች ከባድ ህመም እንዲሰማቸው ስለማድረጉ ምንም ማስረጃ የለም።

በዩናይትድ ኪንግደም ኢስት አንግሊያ ዩኒቨርስቲ የበሽታዎች ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ፖል ሀንተር "የተለመዱ የሚመስሉ ልዩ ምልክቶች የሉም" ብለዋል።

ትኩሳት፣ ሳል፣ የጉሮሮ ህመም፣ ጭንቀት፣ ድካም፣ ራስ ምታት፣ ትንፋሽ ማጠር፣ ተቅማጥ እና ሌሎችም ህመሞች የኮቪድ-19 ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ።

በዩኬ በሬዲንግ ዩኒቨርስቲ የቫይረስ ተመራማሪ ሆኑት ኢን ጆንስ "ቫይረሱ ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይኖረው ተመሳሳይ ህዋሶችን (ሴሎችን) ዒላማ እያደረገ ነው። . . . ስለዚህ ምልክቶቹም ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ናቸው የሚሆኑት" ሲሉ ያብራራሉ።

ለምን በጣም ተለዋዋጭ ሆነ?

ሁሉም ቫይረሶች በጊዜ ሂደት ይለወጣሉ። እንደ ኮቪድ-19 ያሉ ቫይረሶች ደግሞ በበለጠ በፍጥነት ይለወጣሉ።

የአሜሪካው የበሽታዎች ቁጥጥር ማዕከል (ሲዲሲ) 'ቢኤ.3.2'ን "በጣም ተቀያያሪ" ሲል ገልፆታል። ይህም ማለት ከመጀመሪያው የኦሚክሮም ዝርያ በጣም የተለየ ነው።

እነዚህ መለዋወጦች በሽታ የመከላከል ሥርዓታችን ቫይረሱን እንዳያውቅ ሊያግድ ይችላል። እናም "በተወሰነ ደረጃ" የገነባነውን የመከላከያ ሥርዓት አምልጦ እንዲገባ እንደሚፈቅድ ኢን ጆንስ ይናገራሉ።

"ቫይረሱ በሕብረተሰቡ ዘንድ እንግዳ አካላትን የሚከላከለውን ክፍል እያመለጠ ነው፤ ስለዚህም ቀስ እያለ እየተሠራጨ በመሆኑን በግልፅ ስኬታማ ነው" ሲሉ አክለዋል።

የተሰባሰቡ ቫይረሶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እንደ ኮቪድ-19 ያሉ ቫይረሶች በጊደት ይለወጣሉ

ክቱባቱ አሁንም ይሠራ ይሆን?

የኮቪድ ቫይረስ ክትባቶች ሲካዳ ዝርያ ተቀያያሪ በመሆኑ ሰዎችን በመከላከል ረገድ ያን ያህል ስኬታማ ላይሆኑ ይችላሉ።

ነገር ግን ባለሙያዎች ከዚህ ቀደም የነበሩት ክትባቶች ከአዲሱ ዝርያ የተወሰነ ጥበቃ ማድረግ ይችላሉ ሲሉ ጠቁመዋል።

ኢን ጆንስ "[በአዲሱ ዝርያ] ልትያዙ ትችላላችሁ፤ ነገር ግን መለስተኛ ኢንፌክሽን ብቻ ነው የሚሆነው" በማለት ያብራራሉ።

እንደ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ እስከ አሁን ድረስ 67 በመቶ የዓለም ሕዝብ የኮቪድ-19 ክትባት ወስዷል።

ይሁን እንጂ ከአዳዲስ ዝርያዎች ለመከላከል የዘመኑ ማጠናከሪያ ክትባቶች ወይም "ቡስተር" የሚባሉትን የተሻሻሉ ክትባቶች ማግኘት በመላው ዓለም የተለያየ ነው።

የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ቫይረሱ ከተዛመተ እና የክስተቶቹ ክብደት በከፍተኛ ሁኔታ ከጨመረ ብቻ ሲካዳን ለብቻው ዒላማ ያደረገ ክትባት ሊያመርቱ እንደሚችሉም ገልፀዋል።

ሊያስጨንቀን ይገባል?

ፕሮፌሰር ሀንተር የኮቪድ-19 አዳዲስ ዝርያዎችን ማየት መቀጠላችን የሚያስደነግጥ አይደለም ይላሉ።

"የሰው ልጆች በምድር ላይ መኖራቸውን እስከቀጠሉ ድረስ አዳዲስ የቫይረሱ ዝርያዎችን ማየት እንቀጥላለን። 'ሳርስ-ኮቭ-2' ይጠፋል የሚለው አጠራጣሪ ነው" ሲሉ አክለዋል።

የሲካዳ ክስተቶች መጨመራቸው የኪቪድ-19 ኬዞች ወይም የሞቱ ሰዎች ይጨምራል ማለት እንዳልሆነም አብራርተዋል።

"ዝርያዎች በመደበኛነት ይገኛሉ እና አዲስ የቫይረስ ማዕበል ላይ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። . . . ሆኖም ሞቶችን እና የበሽታዎችን ክስተት መቀነስ ማየታችን አይቀሬ ነው" ብለዋል።

ባለፈው ታኅሳስ የዓለም የጤና ድርጅት ከሲካዳ ጋር በተያያዘ ከባድ ህመም ወይም ሞትን የሚያመለክት ማስረጃ እንደሌለ ተናግሯል። እናም አነስተኛ የሕብረተሰብ ጤና ስጋት እንዳለው ገልጿል።

ኢን ጆንስ "[ኮቪድ-19] በክረምት የሚከሰት መደበኛ የመተንፈሻ አካል በሽታ ነው። እናም ሰዎች ይህን ብቻ ነው ማወቅ ያለባቸው" ብለዋል።

"ክትባቱን በመውሰድ እንጠቀማለን ብለው ካሰቡ መውሰድ ይችላሉ።"

ይሁን እንጂ ከ65 ዓመት በላይ የሆናቸው እና ስር የሰደዱ የጤና እክሎች ያሉባቸው ሰዎችን ጨምሮ ተጋላጭ የሆኑ ቡድኖች በኮቪድ-19 ክፉኛ ሊጠቁ ይችላሉ።

ፕሮፌሰር ጉብታ "ልጆቻችሁ የቆየ የመተንፈሻ፣ የልብ ህመም ወይም በሽታ መከላከል የአቅም እጥረት ካለባቸው አስቀድሞ የሕክምና እርዳታ ማግኘት አስፈላጊ ነው" ብለዋል።