ያልተለቀቀ የቢዮንሴን ሙዚቃ ከተሽከርካሪ ውስጥ የሰረቀው ግለሰብ በእስራት ተቀጣ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ከታዋቂዋ አሜሪካዊት አቀንቃኝ ቢዮንሴ ያልተለቀቁ የሙዚቃ ፋይሎችን ተሽከርካሪ በመስበር የሰረቀው ግለሰብ በሁለት ዓመት የእስር ቅጣት ተፈረደበት።
የ41 ዓመቱ ኬልቪን ኤቫንስ ባለፈው ዓመት በአትላንታ፣ ጆርጂያ መኪና ሰብሮ ያለፍቃድ መግባትን ጨምሮ ሌሎች ክሶች ጥፋተኝነቱን አምኗል።
እስካሁን በግልጽ የማይታወቅ ምክንያት፣ ኤቫንስ 2025 ቢዮንሴ የሙዚቃ ዝግጅቷን ለማቅረብ ወደ አትላንታ ባቀናችበት ወቅት የድምፃዊቷ የዳንስ አዘጋጅ እና ዳንሰኛ ተከራይተው የሚያሽከረክሩትን 'ጂፕ ዋገን' ተሽከርካሪን ሰብሮ መግባቱ ታውቋል።
ዳንሰኞቹ የተሽከርካሪው የኋላ መስኮት ተሰብሮ እና ንብረታቸው ተዘርፎ ማግኘታቸው ተነግሯል። መርማሪዎች እስካሁን የድምፃዊቷን ሙዚቃ የያዘውን 'ሃርድ ድራይቭ' ወይም ሌሎች የተሰረቁ ንብረቶች አልመለሱም።
የፉልተን ካውንቲ አቃቤ ሕግ ኤቫንስ በዚህ ሳምንት ሊካሄድ ከነበረው ፍርድ ቀደም ብሎ ከአቃቤ ሕግ ጋር የጥፋተኝነት አመኔታ ስምምነት ውል መግባቱን ለቢቢሲ አረጋግጧል።
የተከሳሹ ጠበቃ ለዳኛው "ደንበኛዬ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ገቢ ማግኘት እና የማህበረሰብ ክፍል መሆን ይፈልጋል" ሲሉ ተናግረዋል።
በክሱ ላይ ብይን የሚሰጡ የሕዝባዊ የዳኞች ምርጫ ሰኞ ዕለት ተጀምሮ የነበረ ሲሆን፣ አቃቤ ህግ ኤቫንስ የሚያሽከረክረው ቀይ ሃዮንዳይ መኪና ወደ ተጊጂዎች ተሽከርካሪ ሲቀርብ የሚያሳይ የካሜራ ምስል በማስረጃነት አቅርቧል።
ሌላ የካሜራ ምስል ደግሞ የተከሳሹ ቀይ ተሽከርካሪ ወደ አፓርታማ ሕንፃ ሲደርስ እና ኤቫንስ የሻንጣ እቃዎችን ሲያነሳ ያሳያል።
ዳንሰኞቹ ለፖሊስ እንደተናገሩት፣ ከተሽከርካሪያቸው የተሰረቁት ንብረቶች ሁለት 'ማክቡክ' ላፕቶፖች፣ አፕል የጆሮ ማዳመጫዎች፣ ውድ ልብሶች እና ጌጣጌጦች እንዲሁም የቢዮንሴ ያልተለቀቁ ሙዚቃዎችን የያዙ 'ሃርድ ድራይቮች' ነበሩ።
ግራንት የተባለው ዳንሰኛ ከእነዚህ ንብረቶች በተጨማሪም የቢዮንሴ የግል እና ሚስጢራዊ መረጃ ያካተተ "መረጃ" ይዞ እንደነበር ለባለሥልጣናት ተናግሮ ነበር።
አቃቤ ሕግ እንደገለፀው፣ የተሰረቁት ላፕቶፖች በተገጠመላቸው የመከታተያ ቴክኖሎጂ መሰረት በሁለተኛው የማስረጃ ተንቀሳቃሽ ምስል በተገለፀው አድራሻ መታየታቸውን አመልክቷል።
የፍርዱ አካል ኤቫንስ ከተጎጂዎች እና ስርቆቱ ከተፈጸመበት መኪና ማቆሚያ ስፍራ እንዲርቅ መታዘዙም ታውቋል።
የ41 ዓመቱ ኬልቪን ኤቫንስ ካለፈው የነሐሴ ወር ጀምሮ በእስር ቤት ውስጥ ይገኛል።














