ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ስለ ፖለቲካ ማውራት በሕግ የተከለከለባት አሜሪካ ውስጥ የተደበቀችው አዲሷ 'አገር'
ስሎውጃማስታን ሲባል ቀድሞ ወደ አዕምሯችሁ የሚመጣው ከቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት ተፈረካክሰው የወጡት አገራት ሊሆኑ ይችላሉ - እነ ኡዝቤኪስታን፣ ታጃኪስታን፣ ኪርጂስታን . . .
ነገር ግን ስሎውጃማስታን ከእነርሱ ጋር የሚያዛምድ ታሪክ የላትም።
ከተመሰረተች ገና አስር ዓመት እንኳን አልሞላትም። የዓለማችን በዕድሜ እምቦቀቅላዋ 'አገር' ናት። የተባበሩት መንግሥትታት የአገርነት እውቅና ባይኖራትም መስራቾቿ 'አገር' ናት ይላሉ።
እውቅና ካላቸው የዓለማችን ትንንሽ አገራት የበለጠ የተመዘገቡ ዜጎችም አሏት።
የራሷ የገንዘብ ኖት፣ ፓስፖርት፣ ብሔራዊ መዝሙር፣ የፖሊስ ኃይል እና የድንበር ፍተሻ ጣቢያዎች አላት።
ፖለቲካ ያንገሸገሻቸው የሌሎች አገራት ዜጎችን ትኩረት እየሳበች ነው ። ምክንያቱም በግዛቷ ስለፖለቲካ ማውራት በሕግ የተከለከለ ነው።
ለመሆኑ ይህች የቆዳ ስፋቷ ቢበዛ ሰባት የእግር ኳስ ሜዳ የሚሆን 'አገር' የት ነው የምትገኘው? እንዴትስ ተመሰረተች? ማንስ ፈጠራት?
ይህች ራሷን በአገርነት ያወጀች አገር የምትገኘው በካሊፎርኒያ ኮቼላ ሸለቆ በሚገኘው የቴምር እርሻዎች እና በሜክሲኮ ድንበር መካከል በሚገኝ የበረሃ ሥፍራ ነው።
በረሃው እንደምንም ባደጉ ቁጥቋጦዎች እና እርስ በእርስ በተሳሰሩ ቅርንጫፎች የተሞላ ነው። በአየሩ 'ዝዝዝ. . . ' በሚሉ የነፍሳት ጩኸት ይሰማል። ከርቀት ሰርጓጅ ጀልባዋ ይታያል።
ይህች 'ሪፐብሊክ ኦፍ ስሎውጃማስታን የተባለችው የዓለማችን በዕድሜ ትንሽ አነስተኛ አገር አስራ አንድ ሄክታር ስፋት አላት። የቆዳ ስፋቷ አነስተኛ ቢሆንም ወደ ውስጥ ሲዘልቁ ከዓለም እጅጉን ይርቃሉ።
በዚህች አገር የፕላስቲክ ነጠላ ጫማ መጫመት በሕገ መንግሥት የተከለከለ ነው። እነዚህ በተለምዶ 'ኤርገንዶ' የምንላቸው ነጠላ ጫማዎች የአካባቢውን ፋሽን ያበላሻሉ፤ ሥነ ሥርዓትን ያጓድላሉ ተብሎ ይታመናል።
ይህ ብቻም አይደለም። ይህች ራስ ገዝ አገር በአንድ ጊዜ ለብዙ ሰው የኢሜይል መልዕክት መመለስ [ሪፕላይ ኦል] ማድረግንም በሕግ ትከለክላለች።
ይህን ማድረግ አላስፈላጊ ጫጫታ ይፈጥራል ይላሉ። ለብዙ ሰው በአንድ ጊዜ የቡድን መልዕክት መላክ የሚቻለው ልክ እንደ ጦርነት ያሉ ወሳኝ የሆኑ መልዕክቶችን ብቻ ነው። ሕጉን ጥሶ የተገኘም ቅጣት ይጠብቀዋል።
እርጋታ እና ተዝናኖት መገለጫዋ ነው። ጥድፊያ የሚፈቀደው 'ታኮ' የተባለውን ምግብ ሳይቀዘቅዝ ለመመገብ ነው።
የዚህ ሁሉ ፈጣሪ ራንዲይ ዊሊያምስ ይባላል።
ዊሊያምስ የስሎውጃማስታን ሱልጣን ወይም ንጉስ በመባልም ይታወቃል።
ንጉሱ በአገሪቷ የሚገኘውን እና ራኮን የተባለውን ቀበሮ መሳይ እንስሳ፣ የበረሃ እንሽላሊቶች እና በረሃውን 'የአምባገነን ቤት' እያሉ የሚጠሩትን ወደ 25 ሺህ የሚጠጉ ዜጎችን ብቻ አይደለም የሚያስተዳድረው።
ዊሊያምስ በሳንዲያጎ የዜድ90 እና ማጅክ 92.5 የራዲዮ ጣቢያ ዳይሬክተር ነው።
'አር ዳብ' በሚለው የመድረክ ስሙ የሚታወቀው ዊሊያምስ ከአውሮፓውያኑ 1994 ጀምሮ 'ሰንደይ ናይት ሾው ጃምስ' የተሰኘ የራዲዮ ፕሮግራሞችን ያዘጋጅ ነበር። ይህ ፕሮግራም አሁን ላይ በዓለም ላይ ባሉ ከ250 በላይ ጣቢያዎች ይተላለፋል።
ለጉዞ ልዩ ፍቅር ያለው ዊሊያምስ በተባበሩት መንግሥታት እውቅና የተሰጣቸውን እያንዳንዱን አገራት ለመጎብኘት ጥረት ሲያደርግ ዓመታትን አሳልፏል። በአውሮፓውያኑ 2020 መጀመሪያ ላይ ታዲያ ወደ አንድ የመጨረሻው አገር ለመሄድ ተነሳ - ወደ ቱርኬሜኒስታን። ሆኖም ዓለም በድንገት የእንቅስቃሴ ገደብ ውስጥ ገባች።
በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት እንቅስቃሴ ተገደበ። ዊሊያምስ አንድ ሥፍራ መቀመጥን አይወድም ነበር። እረፍት አጣ ። ብዙ ጊዜ አለው፤ ግን የሚሄድበት አልነበረውም።
አዕምሮው እንደ ጄት ነበር በሃሳብ ይበር የነበረው። አንድ ሃሳብ መጣለት። " ሌላ አገር ሄጀ መጎብኘት ካልቻልኩ። ለምን አንድ አገር አልፈጥረም?" የሚል።
ሐሰተኛ አምባገነን እንዴት መሆን ይቻላል?
"ሕፃን እያለሁ የፈጠራ ሥራዎችን መስራት እወድ ነበር። መፃፍም ወይም ሥዕል መስራት ወይም የክፍል ውስጥ ሥራዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ይህ ግን ትልቁ ፈጠራ ይመስላል" ይላል ንጉስ ዊሊያምስ ቆንስላውን ወይም በሬድዮ ጣቢያው የሚገኘውን ቢሮውን ለቢቢሲ ዘጋቢ ሲያስጎበኝ።
በራዲዮ ጣቢያው ከመላው ዓለም የተውጣጡ አምባገነናዊ ሥርዓቶች ፕሮፖጋንዳን ያከማችበታል። " ሁሉንም የፈጠራ አቅሜን በዚህ ላይ ማዋል እችላለሁ" ይላል።
ዊሊያምስ በወቅቱ ምን ያስብ እንደነበር እንዲገልጽልን የቅርብ ጓደኛውን ማርክ ኮሮናን ጠራው። ኮሮና እየሳቀ ዊሊያምስ እፈጥረዋለሁ ያለውን አገር የት እንደሚፈጥረው በመገረም እንደጠየቀው ያስታውሳል።
" 'ቤትህ ውስጥ ነው የምትፈጥረው?' አልኩት" ይላል።
ዊሊያምስ ግን በአቋሙ ፀና። የቤት ግንባታ የሚካሄድበት ቦታ በማሰስ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ዝርዝር መያዝ ጀመረ።
ከአምስት ሄክታር መሬት በላይ ያስፈልጋል። ይህ ቦታ ደግሞ በየብስ ከሌሎች ግዛቶች ጋር መገናኘት የሚችል እና ሳንዲያጎ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ብዙም የማይርቅ እንዲሆን አሰበ።
አንድ ቦታ አገኘ። መሬቱ ምንም ያልለማ፣ በአሸዋ እና በድንጋይ የተዋጠ ነበር። ዋጋው ደግሞ 19 ሺህ 500 ዶላር።
ዊሊያምስ እንደሚለው መጀመሪያ እንዳየው ነበር የወደደው። ከዚያም መሬቱን እንደ አውሮፓውያኑ በ2021 ገዛው።
ዊሊያምስ ጓደኛው ኮሮና የበርካታ አገራት ፕሬዚደንቶች የሚገለገሉበት ዓይነት 'ፕሬዚደንታዊ የሚመስለውን ጠረጴዛ እንዲያመጣ ነግሮት ወደ ደቡባዊ ካሊፎርኒያ ወሰዱት።
ከዚያም በበረሃው መሃል አራግፈው የግዛታቸውን ምልክት አስቀመጡ። በካሊፎርኒያ ግዛት መስመር 78 የመንገድ መልክቶችን አቆሙ - 'ሪፐብሊክ ኦፍ ስሎውጃማስታን' የሚል።
ስያሜውን የሰጠው ከሙዚቃ ሙያው ጋር አያይዞ ነው። ሰዎች መጥተው የሚዝናኑበት እና የሚረጋጉበት 'የለስላሳ ሙዚቃ ምድር' ወይም 'ላንድ ኦፍ ስሎው ጃምስ' ከሚለው ሃሳብ የተወሰደ ሲሆን ቀደም ብሎ እንደ ቀልድ ያወጣው ነበር።
የአካባቢው ባለሥልጣናት የመንገድ ምልክቶቹን ለማየት ጊዜ አልፈጀባቸውም። ምልክቱ የተቀመጠው ለመንገዱ ቅርብ በሆነ ሥፍራ ነበር። ዊሊያም ቀስ ብሎ ምልክቶቹን ወደ ግዛቱ አስገባቸው። ከዚያም አዲሷን 'አገር' አወጀ።
" ሰዎች ምን እንደተፈጠረ እየተገረሙ እየነዱ ይመጡ ነበር" ይላል ወዳጁ ኮሮና። " ምን አልባት ሽብርተኞች እንደሆንን ያስቡ ይሆናል። ይህም ጉዳዩን አቀጣጠለው። ትኩረት እንዲያገኝ አደረገ"
የመንገድ ምልክቶችን ማስቀመጥ ገና የሥራቸው መጀመሪያ ነበር። ከዚያ ግን የድንበር መግቢያ ቦታዎችን አዘጋጁ። ሰንደቅ ዓላማ እና ፓስፖርት ተከተለ። ብዙም ሳይቆይ ሪፐብሊክ ኦፍ ስሎውጃማስታን "የአገር መልክ" ያዘች።
" በድንገት የፖሊስ መኪናዎች እና ሳንቲሞች እና ኢሚግሬሽን ድንኳኖችን ገዛሁ" ይላል ዊሊያምስ።
ዊሊያምስ ራሱን ሱልጣን ወይም ንጉስ ብሎ አወጀ። ከዚያም ጥቁር መነጽር ማድረግ፣ የተጌጠ የደንብ ልብስ መልበስ፣ የሊቢያው ሙአመር ጋዳፊ ይለብሱት የነበረውን የጦር ልብስ ዓይነት መልበስ ያዘ። ድምጹንም ወደ ሌላ አገር ጄነራል ድምጸት ለወጠ።
ከአምስት ዓመታት በኋላ ስሎውጃማስታን ለጎብኝዎች ፓስፖርት መስጠት ጀመረች። ዜጋ ሆኑ ። የመገበያያ ገንዘቡን መጠቀም እንዲሁም በዝግጅቶች ላይ ሰንደቅ ዓላማውን መያዝ ጀመሩ። ትንሿ መሬት ወደ ግዛት ተከፋፈለች- ደበላንዲያ፣ ቡክስይልቫኒያ እና ኩዊንደም ኦፍ ሆትዳምናስታን ወደሚሉ።
ሱልጣኑ ብሔራዊ መዝሙር ፃፈ።ብሔራዊ መዝሙሩ ስሎውጃማስታን ልዩ ቦታ እንደሆነች የሚያወድስ ነው። መዝሙሩ ሲዘመር ነዋሪዎች ቀጥ ብለው ቆመው አብረው መዘመር ይጠበቅባቸዋል።
'በአገሪቷ' ውስጥ በይፋ መሳተፍ የሚፈልጉ ሰዎች ሊኖራቸው የሚገባም ማዕረግ አለ።
" ምን አልባት አንተ ከሰሜን ካሮላይና የመጣህ ነህ። ግንኙነትህን ማጠናከር ከፈለክ ይህንን ማድረግ ትችላለህ። ትንሽ መክፈል ከዚያም የፓርላማ አባል ትሆናለህ" ይላል ዊሊያምስ።
ምንም እንኳ በአምባገነን ሥርዓት የሚሰጡ ኃላፊነቶች ዋጋ የሚከፈልባቸው ቢሆንም አምባሳደሮች በወር ከ10 እስከ 25 ዶላር ይከፍላሉ። ዜግነት ግን ለሁሉም ነፃ ነው። 'ትንሿ አገር' አሁን ላይ ከ120 አገራት 25 ሺህ የተመዘገቡ ዜጎች አሏት። በተባበሩት መንግሥታት እውቅና ከተሰጣቸው አንደ ቫቲካን ፣ ቱቫሉ እና ፓላው ያሉ አገራት የተሻለ የሕዝብ ብዛት አላት።
ምንም እንኳን ብዙዎች ከስሎጃማስታን ጋር የሚገናኙት በማኅበራዊ ሚዲያ ከርቀት ቢሆንም ማኅበረሰቦቿ ግን በአካል ይገናኛሉ።
ለምሳሌ ግዛቷን ለመጠበቅ የተሰራችው 'ኤስኤስ ባዳሲን' ሰርጓጅ ጀልባ ስትመረቅ በተካሄዱ ዝግጅቶች ላይ ተገኝተዋል።
በኦንላይን የተቀመጠን ቅፅ በመሙላት የሚገኘው ሙሉ ዜግነትም ሰዎች ይበልጥ እንዲገናኙ አስችሏል።
የመጨረሻው ማምለጫ
እንደ ንጉሱ ከሆነ ሰዎች በተለያየ ምክንያት ስሎውጃሚስታናዊ መሆን ይፈልጋሉ። አንዳንዶች ምን እንዳለ ለማወቅ ይጓጓሉ። አንዳንዶች ደግሞ ይደነቃሉ። አንዳንዶች ደግሞ ከሌላው ዓለም ሆነው ዝም ብለው ይመለከታሉ።
"ሁሉም ነገር ከፋፋይ እንደሆነ መንገር አያስፈልገኝም " የሚለው ንጉሱ፣ "ፌስቡክ በከፈትክ ቁጥር ሰዎች በፖለቲካ ምክንያት ጓደኞቻቸውን እና የቤተሰብ አባላቸውን እያጡ ነው። ይህ መጥፎ ነው። ስሎውጃማስታን ከዚህ ሁሉ የማምለጫ ቦታ ነው። በተጨባጭ ካለው ፖለቲካ በተጨማሪ ስለፖለቲካ ማውራት የተከለከለ ነው" ይላል።
አሁን ላይ ስለ አገራቸው ፖለቲካዊ ሁኔታ የሚጨነቁ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። በዚህም ምክንያት ሌሎች ፓስፖርቶችን እያማተሩ ነው" የሚለው ዊሊያምስ ከስሎውጃማስታን ዜጎች 50 በመቶውን የሚይዙት የአሜሪካ ዜጎች እንደሆኑ ይናገራል።
ንጉሱ እንደሚለው የአገሪቷ እድገት ፖለቲካዊ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ነው። ለዚህም በቅርቡ ከባንግላዴሽ ለዜግነት የሚያመለክቱ ሰዎች ቁጥር መበራከት " ምንም ዓይነት ድንበር እንደሌለ" ያስረዳል ብሏል።
ስቴፋኒ ሂደን መጀመሪያ ላይ ስለ ስሎውጃማስታን የሰማችው 'ጂኦፓርዲይ' በተባለ ፕሮግራም ላይ አንድ ተወዳዳሪ 'አገሪቷን' ከጠቀሰ በኋላ ነበር። በኋላ ላይ ዊሊያምስን በጉዞ ፕሮግራም ላይ አየችው።
አሁን ላይ የአገሪቷ ዜጋ የሆነችው ሂዴን " ወደ ሕይወቴ ለመጣው ደስታ ሱልጣኑን ማመስገን እፈልጋለሁ" ብላለች።
እርሷ ደስታ የምታገኘው 'ትንሿ አገር' በተደጋጋሚ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ስለተለዩት ሕጎቿ እና በኩራት የስሎውጃማስታን ፓስፖርት የሚያሳዩ አዳዲስ ዜጎችን በተመለከተ በምታጋራው ልጥፍ በመሳተፍ ነው።
" ሁሉም ነገር ያስደስተኛል እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ስሎውጃማስታን ዜጎች በዚህ ይስማማሉ። ይህ ለሁላችንም አስቸጋሪ ጊዜ ነው [በአሜሪካ]፣ እዚህ የሆነ ደስታ አለ" ትላለች።
ከበረሃ ወደ ዓለም አቀፋዊ መድረክ
በዓለም በመቶዎች የሚቆጠሩ ትንንሽ አገሮች እንደሚኖሩ ይገመታል። የተወሰኑት የሚገኙት በዓለም አቀፍ የውሃ ክፍሎች ላይ ነው። ሌሎች ደግሞ በጣም በራቁ የአገር ዳርቻዎች።
በሚቀጥለው ዓመት ስሎውጃማስታን ማይክሮኮን 2027 ታዘጋጃለች። ይህ የትንንሽ አገራት ስብስብ ነው። ከቦምበር ሪፐብሊክ እስከ ድራጎን ኢስሌ ከ43 በላይ ራስ ገዝ ግዛቶች የተውጣጡ ተወካዮች ከጂኦፖለቲካዊ ሉዓላዊነት ወታደር እስከመፍጠር ይወያያሉ።
ንጉሱ ምንም እንኳን ጎብኝዎች ወደ በረሃማዋ ግዛት እንዲገቡ ቢፈቅድም አዳራቸውን በዚያው ለሚያደርጉ ጎብኝዎች በቂ ቦታ የለውም።
የጄት መንደርደሪያ ቦታ ምልክት ቢኖረውም እና ዊሊያምስ 'ራንዲ ዊሊያምስ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ በቅርብ ቀን " የሚል መልዕክት ቢያጋራም ለጎብኝዎች የተሟላ ሁኔታ የለም።
በዚህም ምክንያት ማክሮኮን 2027 በሳንዲያጎ ፔንትሃውስ ስካይ ክራፐር ይካሄዳል ተብሏል።
ለዊሊያምስ አነስተኛ አገራት ሁል ጊዜም ከጉዞ ጋር ነው መያያዝ ያለባቸው።
ለዚህም ኡዝቤኪስታን ከሚገኘው ዜጋው የተላለፈውን መልዕክት ይጠቅሳል።
"ሰላም፣ አገርህ መጥቼ ነበር አልኩት። ፎቶ አሳየኋቸው። ልክ እንደዛ። ወዲያው ነበር የተግባባነው " ይላል።
ስሎውጃማስታንን መገንባት የሚፈልገውም በዚሁ መሠረት ነው። የማይመች ነገር ግን በዓለም ዙሪያ ያለ ሕዝብ የሚጎበኛቸው እና የሚገናኝባቸው ማድረግ።
ዊሊያምስ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ያልጎበኛትን ቱርኬሜኒስታንን ግንቦት 2023 ጎብኝቷታል። በዚህም ሁሉንም የዓለም አገራት የመጎብኘት ዓላማውን አሳክቷል።
ያኔ እንቅስቃሴው በተገደበበት ወቅት የፈጠራት ስሎውጃማስታን ይህንን ክፍተት ለመሙላት አትችልም ነበር። ነገር ግን ከሰዎች ጋር ለመገናኘት ሌላኛዋ መንገድ ሆናው ነበር።
"ስሎውጃማስታን የእኔ ብቻ አይደለችም. . . ዌል፣ አምባገነን ነኝ ። ሆኖም የሁሉም ናት። ስሎውጃማስታን ለእያንዳንዱ ሰው የተለየ ትርጉም አላት" ብሏል።