ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ እና የኢራን የተኩስ አቁም እንዳይጸና ያደረጉ አራት ምክንያቶች
ባለፈው ሚያዚያ በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት በቀጣናው አዲስ ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ በከባድ ጫና ውስጥ ይገኛል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጥቃቶቹን ተከትሎ ሊወስዷቸው ስለሚችሏቸው እርምጃዎች ዛቻ እየተለዋወጡ ነው።
ረቡዕ ዕለት አሜሪካ ሂሊኮፕተሯ ተመትቶ ከወደቀ በኋላ በኢራን ወታደራዊ እና የደኅንነት ተቋማትን ዒላማ አድርጋ መምታቷንን ገልፃለች።
የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በባህሬን፣ ኩዌት እና በዮርዳኖስ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ ጥቃት በመፈጸም ምላሽ መስጠቱን አስታውቋል።
ይህ የግጭት መጋጋል የመጣው ባለፈው እሑድ ኢራን እስራኤል ላይ ሚሳኤል መተኮሷን ተከትሎ፤ እስራኤል ምዕራብ እና ማዕከላዊ ኢራንን ዒላማ አድርጋለች።
ይህም የተኩስ አቁሙ ከጀመረ ወዲህ በሁለቱ አገራት መካከል የተኩስ ልውውጥ ሲደረግ የመጀመሪያው ነው።
ትራምፕ ሁለቱም ወገኞች የሚፈጽሟቸውን ጥቃቶች እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ምንም ዝርዝር ውስጥ ሳይገቡ ኢራን አሁን "ዋጋ ትከፍላለች" ብለው ነበር። ፕሬዝዳንቱ ኢራን "ሙሉ ለሙሉ ተሸንፋለች፤ ወሬ ብቻ እንጂ አቅም የላትም" ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ አገራቸው "የትኛውንም ጥቃት ወይንም ስጋት ምላሽ ሳትሰጥ አትቀርም" በሚል ካስጠነቀቁ በኋላ ነው። አባስ አራግቺ አሜሪካ "በጦርነት ሜዳ ተሸንፋለች" ብለዋልም።
ለአሁኑ ሁለቱም ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነቱን በይፋ አፍርሰናል አላሉም። ይሁን እንጂ ከዚህ በላይ የሚደረጉ ግጭቶች ጦርነቱን ለማስቆም በዋሽንግተን እና በቴህራን መካከል ሰፊ ስምምነት ለመድረስ የሚደረጉ ጥረቶችን ያደናቅፋል የሚል ስጋት አለ።
ለምን ይሆን ስምምነቱን ለማፅናት ከባድ የሆነው? እንደ ባለሙያዎች ከሆነ አራት ምክንያቶች አሉ።
1. ለኢራን ቀላል ያልሆነ ስምምነት
በዋሽንግተን መቀመጫውን ያደረገው የዓለም አቀፍ ፖሊስ ባልደረባ የሆኑት ሲና ቶሲ አንዱ ምክንያት በኢራን በኩል የተኩስ አቁም ስምምነቱ የግጭቱን "ዋነኛ ጉዳይ አለመፍታቱ" ነው ይላሉ።
ለዚህም በቴህራን ላይ የወደብ እግድ እና ማዕቀቦችን ጨምሮ ከቀጠለው የአሜሪካ የወታደራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ጫና ጎን ለጎን እስራኤል በሊባኖስ እያካሄደች ያለቸው ወታደራዊ ዘመቻ መቀጠልን አንጥረው ያነሳሉ።
ማክሰኞ ዕለት ኢራን እንዲህ ዓይነት ጥቃቶች እንዲቆሙ ጥሪ ካደረገች ከአንድ ቀን በኋላ የእስራኤል ጦር የደቡብ ሊባኖሷን ታየር ከተማን ደብድቧል።
ይህን ቴህራን ዋሽንግተን "ጉልህ ኃይል" እንድትይዝ የሚያደርግ የድኅረ ጦርነት ስምምነት አድርጋ ማየቷ ከፍ ያለ ሲሆን፤ ምንም እንኳ ሙሉ ለሙሉ የሚፈነዳ ጦርነትን ቢያስቆምም የኢራን ባለሥልጣናት "ያልተረጋጋ እና ተቀባይነት የሌለው" አድርገው ይመለከቱታል ይላሉ ቶሲ።
ኢራን አሜሪካ ላይ የምታደርገው ወታደራዊ ጫና እና በቀጣናው አጋሮቿን ዒላማ ማድረጓን በዝቅተኛ ዋጋ መቋቋም እንደምትችል ስጋት አላት ነው ሲሉ ያክላሉ።
እንዲህ ዓይነት እርምጃዎች በቀጣናው "መደበኛ ሁኔታ" ሊሆኑ የሚችሉ ሲሆን፤ ይህም የኢራንን አቋም በጊዜ ሂደት ሊሸረሽር የሚችል ነው።
ባለሙያዎች የኢራን ባለሥልጣናት ቴህራን ትዕግሥተኛ ሆና ባላንጣዎቿ ወታደራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ጫና እንዲያደርጉባት የሚፈቅድ ስምምነት ላለመፈረም በአገር ቤት ጫና አለባቸው ይላሉ።
2. የእስራኤል ሚና
ተንታኞች የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለማፅናት የሚደረገውን ጥረት እስራኤል በእርምጃዋ አያወሳሰበችው መሆኑን ያነሳሉ።
በዩናይትድ ኪንግደም የሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር አለየር "እስራኤል ኢራን ቀጣናዊ ኃያል ሆና የሚያስቀጥላትን የአሜሪካ-ኢራን ስምምነትን ለማደናቀፍ መሠረታዊ ፍላጎት አላት" ይላሉ። እስራኤልን ሊካሄድ የሚችልን የዲፕሎማሲ ጥረቶች "ረባሽ" አድርገው ይገልጿታል።
"ምንም እንኳ የአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ቢቀጥልም ስምምነቱን ለማበላሸት እርምጃ ይወስዳሉ።"
ከእሑዱ ጥቃት በኋላ ቴል አቪቭ ኢራን ላይ ጥቃት እንዳትፈጽም ፕሬዝዳንት ትራምፕ ቢያስጠነቅቁም እስራኤል ትራምፕን አሻፈረኝ ስለማለቷ አንዳንድ ክርክሮች ተካሂደዋል።
በእስራኤል ኢንስቲቲዩት የብሔራዊ ደኅንነት ጥናት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት የሽዋ ካልስኪ ለሮይተርስ "እስራኤል በዚህ ጦርነት ለረጅም ጊዜ ብቻዋን መጓዝ እንደማትችል ጥርጥር የለውም። ምክንያቱም መሣሪያ የሚበላ ስለሆነ" ብለዋል።
የወታደራዊ ታሪክ ባለሙያ የሆኑት ዳኒ ኦርባቺ እስራኤል ከኢራን ጋር ስምምነት ካልደረሰች የደኅንነት ስጋቷን ችላ ማለት እንደማትችል ምልክት ሰጥታለች።
"[ሊደረስ የሚችል ስምምነት] የእስራኤል ፍላጎትን ካረጋገጠ፤ እስራኤል ድርድሩን ትቀለብሳለች" ሲሉ ከሮይተርስ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።
ከቢቢሲ ጋር በስልክ በነበራቸው ቃለ ምልልስ ትራምፕ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያ አሻፈረኝ ብለው ኢራን ላይ የአፃፋ ጥቃት መፈማቸው አስተባብለዋል። ምንም እንኳ ትዕግሥት እንዲያሳዩ ቢወተውቱም።
3. ጥቃቶችን ጫና ለመፍጠር መጠቀም
ሦስተኛው ምክንያት ግጭት ማገርሸት የድርድሩ ስልት አካል ሆኖ መታየቱ ነው።
ምንም እንኳ በአሜሪካ እና በእስራኤል ወታደራዊ ጫና፣ ማዕቀብ እና የወደብ እግድ ቢደረግባትም የኢራን መሪዎች በቦታቸው፤ የፀጥታ መዋቅሩም ሳይበታተን ይገኛል። በተቀናቃኞች እንደተተነበየው የውስጣዊ አለመረጋጋት እምብዛም እክል አልሆነም።
ተንታኞች ይህ የኢራንን የአይበገሬነት መንፈስ አጠናክሮታል ይላሉ። የቱንም ዋጋ ከፍሎ ግጭትን ከማስወገድ ይልቅ ኢራን አሁን ራሷን ጫና ተቋቋሚ አድርጋ እንድታይ አድርጓል። እናም አዲስ ቀይ መስመሮችን ለማስከበር ፍላጎት ይኖራታል።
በተመሳሳይ ጊዜ ባለሙያዎች ወታደራዊ ጫና እና ዲፕሎማሲ መሳ ለመሳ መሄድ የሚችሉ እንደሆነ አመልክተዋል።
ቶሲ "ኢራን ዲፕሎማሲን እየተወች አይደለም" ይላሉ።
በሊባኖስ፣ በባሕረ ሰላጤው እና በሌሎችም አካባቢዎች በቅርቡ የነበሩ በአብዛኛው በኢራን የሚደገፉ ቡድኖችን ያሳተፉ እንቅስቃሴዎች ሰፊ ጦርነትን ለመቀስቀስ ዒላማ ያደረጉ አይደሉም በማለት ይከራከራሉ። ይሁን እንጂ የኢራንን አሁናዊ ቁመና እና የድርድር አቋም ለማጠናከር የሚከፈል ዋጋ ነው።
ዶ/ር ሀልየር ይህን ሀሳብ ያጠናክራሉ "አመክንዮው ቀላል ነው። ለእስራኤል እና ለአጋሮቿ ኢራንን ማጥቃት ዋጋው ነፃ ከሆነ፤ በቀጣነው ሰፊው የአሜሪካን የደኅንነት መዋቅር ላይ በማነጣጠር ዋጋውን ውድ ማድረግ ነው።"
4. የአሜሪካ ድጋፍ
የመጨረሻው ምክንያት አሜሪካ ሚና እና ጫናዋን የት ድረስ ለመውሰድ ፈቃደኛ ናት የሚለው ነው።
እንደ እስራኤል ዋነኛ ወታደራዊ ደጋፊ ዋሽንግተን መሣሪያ፣ ገንዘብ እና የዲፕሎማሲ ድጋፍ ታቀርባለች። ይህም በግጭቱ ሂደት በሙሉ ከፍተኛ የኃይል ምንጭ እንድትሆን አድርጓታል።
ሀለየር ይህ የኃይል ሚዛን ደካማውን የተኩስ አቁም ለመረዳት ሁነኛ ነው ብለው ይሞግታሉ።
"ዋሽንግተን ቴል አቪቭ አቋሟን እንድትለውጥ ከፈለገች፤ እንድትለውጥ የሚያስገደድ ኃይል አላት" ይላሉ። ድጋፉ ገደብ እንዳለው ማመልከቷ ብቻ እንኳ "የእስራኤልን ትኩረት ወዲያው ይገዛል" በማለት ያክላሉ።
"ይህን የኃይል ሚዛን በዚህ መልኩ ለመጠቀም ካልፈለገች ይወሳሰባል። የኃይል ሚዛኑ አለ፤ ነገር ግን ለመጠቀም ፍላጎቱ የለም።"
የሚጠብቁ ስጋቶች
ተንታኞች እነዚህ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንዳይጸና ከባድ ፈተና ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።
ለአሁኑ በርካታ ባለሙያዎች ብቸኛ መውጫ መንገዱ ዲፕሎማሲ እንደሆነ ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ ሀለየር ዲፕሎማሲ "ለወታደራዊ እርምጃ ሽፋን" ሆኖ መታየቱ ከቀጠለ ኢራን ዋጋ ለማስከፈል ወደ ጥቃት መንገዷን ልትቀይር ትችላለች ይላሉ።
እንዲህ ዓይነቱ ለውጥ እንደ ባለሙያው በሁለቱም ወገኖች ግጭቱ እንዲባባስ እና የበለጠ አደገኛ እንዲሆን ያደርጋል።