ሳዑዲ ውስጥ የአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላን በኢራን ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት እንደ ደረሰበት ቢቢሲ አረጋገጠ

ጥቃት የተፈጸመበት ኢ-3 ኤንትሪ የማዘዣ እና የመቆጣጠሪያ ወታደራዊ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Facebook

የምስሉ መግለጫ, ጥቃት የተፈጸመበት ኢ-3 ኤንትሪ የማዘዣ እና የመቆጣጠሪያ ወታደራዊ አውሮፕላን
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በቢቢሲ የተረጋገጡ ፎቶዎች እንደሚያሳዩት የአሜሪካ ወታደራዊ የዕዝ እና የቁጥጥር አውሮፕላን በሳዑዲ አረቢያ በሚገኝ የአየር ኃይል ሰፈር ውስጥ በኢራን በተፈጸመበት ጥቃት ተመትቶ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል።

ፎቶዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጋሩት የአሜሪካን ወታደራዊ ዜና በሚያጋራ የፌስቡክ ገጽ ላይ የነበረ ሲሆን፣ ፎቶዎች እንደሚያሳዩት የኢ-3 ሴንተሪ የተባለው ወታደራዊ አውሮፕላን በተፈጸመበት ጥቃት ለሁለት ተገምሶ ይታያል።

የቢቢሲ መረጃ ማጣሪያ ቡድን ቢቢሲ ቬሪፋይ ፎቶዎቹ የተነሱት ከሳዑዲ አረቢያ ዋና ከተማ ሪያድ በስተደቡብ ምሥራቅ 100 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በሚገኘው የልዑል ሱልጣን የአየር ኃይል ሰፈር መሆኑን አረጋግጧል።

በፎቶዎቹ ላይ የሚታዩት ምልክቶች፣ ምሰሶዎች፣ የማከማቻ ክፍሎች እና የተጠረጉ መንገዶች ላይ የሚታዩ ምልክቶች ላይ በተደረገው ማጣራት ከሳተላይት ምሥሎች ጋር ተመሳሳይነት አላቸው።

የአሜሪካ ጦር ኃይል ማዕከላዊ ዕዝ እስካሁን ድረስ በአውሮፕላኑ ላይ ስለደረሰው ጉዳት አስካሁን በይፋ አስተያየት አልሰጠም። ቢቢሲ ዕዙ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ጠይቋል።

አርብ ዕለት አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ለሮይተርስ ዜና ወኪል እንደተናገሩት 12 የአሜሪካ ወታደሮች በአየር ኃይል ሰፈሩ ላይ በተፈጸመው የኢራን ጥቃት መቁሰላቸውን እና ከመካከላቸውም ሁለቱ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የአሜሪካው ዎል ስትሪት ጆርናል ጋዜጣ በበኩሉ ቢያንስ ሁለት የአሜሪካ የጦር ጄቶችን አየር ላይ ሳሉ ነዳጅ መሙላት የሚችሉ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ጉዳት እንደደረሳባቸው ዘግቧል።

የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ያለው ፋርስ የዜና ወኪል እሁድ ዕለት እንደዘገበው አንድ የሻሂድ አጥፍቶ ጠፊ ድሮን ኢ-3 አውሮፕላንን መትቷል ብሏል።

ኢ-3 ኤንትሪ የማዘዣ እና የመቆጣጠሪያ ወታደራዊ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኢ-3 ኤንትሪ የማዘዣ እና የመቆጣጠሪያ ወታደራዊ አውሮፕላን
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቢቢሲ ቬሪፋይ ከሁለት ሳምንት በፊት በተነሳ የሳተላይት ምሥል ላይ አውሮፕላኑ በተመታበት ቦታ ላይ ኢ-3 አውሮፕላን የተመለከተ ሲሆን፣ ውድመቱ የደረሰበት ተመሳሳይ አውሮፕላን ይሁን ወይም ሌላ ለማወቅ አልቻለም።

በቢቢሲ ከተጣሩት ፎቶዎች መካከል በአንዱ ላይ የአውሮፕላኑ የጭራ ቁጥር ይታያል። ይህንን በመጠቀምም የበረራ መከታተያ ድረገጽ በሆነው ፍላይትራዳር24 ላይ በመመልከት አውሮፕላኑ ከጦር ጀፈሩ አካባቢ በበረራ ላይ እንደነበረ ለማወቅ ተችሏል።

አርብ ዕለት የተነሳ የሳተላይት ምሥል ጉዳት ከደረሰበት ኢ-3 አውሮፕላን በስተምሥራቅ 1,600 ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የአየር ኃይሉ ሰፈር ውስጥ የእሳት ቃጠሎን ያሳያል። ነገር ግን ይህ እሳት በፎቶዎች ላይ የሚታየው አውሮፕላን የተጎዳበት ተመሳሳይ ጥቃት አካል መሆን ወይም አለመሆኑ ግልጽ አይደለም።

የቦይንግ ኢ-3 አዋክስ የሚባለው በኢራን ጥቃት የተመታው አየር ላይ በመሆን የወታደራዊ የማዘዣ እና የመቆጣጠሪያ ማዕከል በመሆን የሚያገለግል ወሳኝ አውሮፕላን ነው።

ቦይንግ 707 አውሮፕላንን የተመሠረተ በማድረግ የተሠራ ወታደራዊ አውሮፕላን ሲሆን፣ በጀርባው ላይ የሚሽከረከር የራዳር መቆጣጠሪያ ሳህን የተገጠመለት የመቆጣጠሪያ እና የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ማዕከል ነው።

ይህ አውሮፕላኑ የተገጠመለት ራዳር በረጅም ርቀት ላይ ያሉ ዒላማዎችን ለመለየት እና ለመከታተል ያስችለዋል፣ በተጨማሪም በጦርነቶች ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ ስጋቶችን አስቀድሞ በመለየት ማስጠንቀቂያን ማስተላለፍ የሚችል ወሳኝ አውሮፕላን ነው።

የአሜሪካ አየር ኃይል ድረገጽ ላይ በሰፈረው መረጃ መሠረት አውሮፕላኑ "የአየር ኃይል ዘመቻዎች በሚካሄዱበት ጊዜ ለአዛዦች መረጃዎችን በመስጠት ተልዕኮዎችን በበላይነት ለመምራት እና ለመቆጣጠር የሚያስችል" ወሳኝ ወታደራዊ የመረጃ አውሮፕላን ነው።

እንዲህ ዓይነቶቹ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ለመጀመሪያ ጊዜ አገልግሎት መስጠት የጀመሩት በአውሮፓውያኑ 1977 ሲሆን፣ ኢ-3 አውሮፕላኖች እስከ 2035 ድረስ በአሜሪካ አየር ኃይል ውስጥ በስምሪት ላይ እንደሚቆዩ ተነግሯል።