ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"የለንደን ማራቶን ክብረወሰንን ድጋሚ ወደ ራሴ እመልሰዋለሁ" - አትሌት ትዕግሥት አሰፋ
እሁድ ሚያዚያ 18 2018 ዓ.ም. በሚካሄደው በ46ኛው የለንደን ማራቶን የምትወዳደረው አትሌት ትዕግሥት አሰፋ ዓላማዋ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት መሆን እንደሆነ ለቢቢሲ ተናገረች።
ትዕግሥት አሰፋ በለንደን ለሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ በሰጠችው ቃለ ምልልስ፤ በዚህ ውድድር ዳግመኛ ማሸነፍ እንደምትፈልግ ተናግራለች።
ለውድድሩ በቂ ዝግጅት እንዳደረገች የተናገረችው ትዕግሥት "ድጋሚ በማሸነፍ ደስታዬን ማጣጣም ነው የምፈልገው" ብላለች።
እሁድ ዕለት በለንደንን የሚካሄደው የማራቶን ውድድር አዲስ ክብረ ወሰን ይመዘገብበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ባለፈው ዓመት ለ45ኛ ጊዜ በተደረገው የለንደን ማራቶን አትሌት ትዕግሥት አሰፋ 2 ሰዓት 15.50 በመግባት እና ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ውድድሩን በአሸናፊነት አጠናቅቃለች።
ከዚህ ቀደም በለንደን ማራቶን በማሸነፏ ትልቅ ደስታ እንደተሰማት ለቢቢሲ የተናገረችው ትዕግሥት፣ "የለንደን ማራቶን ትልቅ ውድድር ነው። እርሱን ሻምፒዮን መሆን ድጋሚ ሻምፒዮን መሆን ነው" ብላለች።
ውድድሩን በማሸነፏ ደስተኛ እንደነበረች ያስታወሰችው ትዕግሥት "በጣም ትልቅ ክብር እና ደስታ ነው የተሰማኝ" ስትል ለቢቢሲ የለንደን ዘጋቢ ተናግራለች።
ትዕግሥት "አሸናፊ ሆኜ እዚህ በመምጣቴ ትልቅ በራስ መተማመን እና ትልቅ 'አድቫንቴጅ' ይዣለሁ" ብላለች። "አሁንም ደግሞ በድጋሚ በማሸነፍ ደስታዋን ማጣጣም" እንደምትፈልግ አክላለች።
የባለፈው ዓመት የለንደን ማራቶን አሸናፊዋ ትዕግሥት አሰፋ በእሁዱ ውድድር ከባድ ተፎካካሪዎች እንደሚጠብቋት ከወዲሁ ተገምቷል።
እሁድ ሚያዚያ 18 በሚደረገው የለንደን ማራቶን ላይም ትዕግሥት የማሸነፍ ቅድሚያ ግምት ካገኙ አትሌቶች መካከል አንዷ ናት።
ከጥቂት ወራት በፊት በለንደን ማራቶን እንደምትወዳደር ይፋ ሲሆን "ባለፈው ዓመት የተካሄደውን የለንደን ማራቶን ማሸነፍ እና በሴቶች ብቻ የዓለም ክብረ ወሰን ማስመዝገቤ በሕይወቴ ከኮራሁባቸው ጊዜያት መካከል አንዱ ነበር፤ ይህንንም በዚህ ዓመት መድገም እፈልጋለሁ" ብላ ነበር።
"ይህን ለማድረግ እንደ ፔሬስ እና ሲፋን ያሉ ታላላቅ ሻምፒዮኖችን ማሸነፍ እንዳለብኝ አውቃለሁ። እነሱ ለእኔ ከባድ ተፎካካሪዎች ነበሩ እና አንዳንድ ታላላቅ ፍልሚያዎችን አድርገናል። በዚህ አመት አንደኛ እንደምወጣ ተስፋ አደርጋለሁ" ስትል አክላለች።
ትዕግሥት አርብ ዕለት ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቃለ ምልልስ "የዓለም ሕዝብ ፈገግታዬን እና ሳቄን እንደሚጠብቅ ፈጣሪ ስለሚያውቅ ድጋሚ የለንደን ከተማ ላይ ሳቄን ለምወዳቸው የስፖርት አፍቃሪ እና የስፖርት ቤተሰቦች ስቄ ደስታዬን ከቤተሰቦቼ ጋር አጣጥማለሁ" ስትል ተስፋዋን ተናግራለች።
ትዕግሥት በ2016 ዓ.ም. በጀርመን በርሊን ከተማ 48ኛው የሴቶች ማራቶን ውድድር የዓለም የሴቶች ማራቶን ክብረወሰንን ከ2 ደቂቃ በላይ በማሻሻል አሸንፋለች።
ትዕግሥት ዓላማዋ ባለፈው ዓመት በቺካጎ በተካሄደው ውድድር በኬንያዊቷ ሯጭ ሩት የተነጠቀችውን ክብረ ወሰን መልሳ ከእጇ ማስገባት እንደሆነ ተናግራለች።
"ዓላማዬ እና ከዚህ በኋላ ዒላማዬ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት መሆን ነው" በማለት በለንደን ማራቶን በድጋሚ ክብረ ወሰኑን በእጇ ለማስገባት እንደምትሮጥ ተናግራለች።
"እሁድ ዕለት የምሮጠውን የለንደን ማራቶን ድጋሜ [ክብረወሰኑን] ወደ ራሴ እመልሳለሁ ብዬ ከእግዚአብሔር ጋር ሙሉ እምነት አለኝ።"
ትዕግሥት ክብረ ወሰኑን በእጇ እንደምታስገባ እርግጠኛ መሆኗን ስትናገርም "ደግሞም አደርገዋለሁ፤ ጠንካራ ሠራተኛ ነኝ። በጥሩ ዲሲፕሊን እና በጥሩ ጤንነት ነው ከእግዚአብሔር ጋር ልምምዴን ሠርቼ የመጣሁት። ድጋሚ ሪከርዱን ወደ ራሴ እመልሰዋለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" ብላለች
የዓለም ሻምፒዮና ለመሆን ስላላት ዕቅድ የተጠየቀችው ትዕግሥት በሎስ አንጀለሱ የዓለም ሻምፒዮና ላይ የተሟላ ጤንነት ኖሯት ለመወዳደር የምትበቃ ከሆነ "እዚያ ላይ ወርቅ ማምጣት እፈልጋለሁ። ምክንያቱም የእኔ ብዙ ደጋፊዎች የእኔ አድናቂዎች ስላሉ እነርሱን ማስደሰት እፈልጋለሁ። ቤተሰቦቼን ማስደሰት እፈልጋለሁ" ብላለች።
እናቴ ሁልጊዜም "የአገር ውድድር፣ ኦሎምፒክ አሸናፊ እንድሆን ትመኛለች" ስትል ለቢቢሲ የተናገረችው ትዕግሥት፤ "[ለእናቴ] እርሱን ማሳየት እና ማሳካት እፈልጋለሁ" ብላለች። "እግዚአብሔር ደግሞ ቸር ነው፤ ይፈቅድልኝ እና አሸንፋለሁ። ያ ነው ዓላማዬ" ስትል ተስፋዋን አጋርታለች።
ለኔዘርላንድስ የምትሮጠው የኦሊምፒክ የማራቶን አሸናፊዋ ሲፋን ሃሰን፣ ኬንያውያኑ ፔርስ ጄፕቺርቺር፣ ጆይስሊን ጄብጎስኪ እና ሄለን ኦብሪ በለንደኑ ውድድር የሚጠበቁ አትሌቶች ናቸው።
ትዕግሥት አሰፋ ከዚህ ቀደም አገሯን በወከለችባቸው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና ኦሊምፒክ ውድድሮች የብር ሜዳልያ አስገኝታለች።
በ2016 ዓ.ም. በበርሊን በነበራት የማራቶን ውድድር 2:11:53 በመግባት ሰዓቱ እስኪሻሻል ድረስ የዓለም ክብረወሰንን በእጇ አስገብታ እንደነበር ይታወሳል።
ከዚህ ውጪ በለንደን ማራቶን በሴት አሯሯጮች ብቻ ያስመዘገበችው 2:15:50 የዓለም ክብረወሰን ሆኖ ተመዝግቦላታል።