ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በ34 ጨዋታዎች ያልተረቱት ሞሮኮዎች የዓለም ዋንጫ ተፎካካሪ የመሆን ዕድል አላቸው?
የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ግስጋሴውን እንደቀጠለ ነው። ቡድኑ ቅዳሜ ምሸት ከውበት ይልቅ የበላይነት በተጫነው ጨዋታ ካናዳ ላይ ድል ተቀናጅቷል።
የሰሜን አፍሪካው ቡድን ምንም እንኳ ማራኪ ጨዋታ ባያሳይም በዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ 3 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
አምስት የግብ ሙከራዎችን ብቻ አድርገው ያሸነፉት ሞሮኮዎች፤ በዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ታሪፍ አነስተኛ ቁጥር ያለው የግብ ሙከራ በማድረግ ያሸነፈ ቡድን ሆነዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ደግሞ ግብ ሙከራ የበለጠ ቁጥር ያለው ቢጫ ካርድ የተመዘዘበት የመጀመሪያው የዓለም ዋንጫ ጨዋታ ሆኗል።
ምንም ቢሆን ግን ሞሮኮ ተሻግራ ወደ ሩብ ፍጻሜ ማለፍ ችላለች፤ የአንድ ቡድን ታላቅነት የሚታየው ግን ብርቱውን ሲረታ መሆኑ ሳይዘነጋ።
አሁን ባለው ደረጃ የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ትልቅ ቡድን እንዲሁም የዓለም ዋንጫን የማሸነፍ እድል ያለው ተፎካካሪ መቆጠር ይኖርበታል።
ቡድኑ በዚህ የዓለም ዋንጫ ብቻ ሳይሆን፤ ባደረጋቸው ያለፉት 34 ጨዋታዎች አልተሸነፈም። ከሴኔጋል ጋር ተጫውተው፤ ኋላ ላይ ለሞሮኮ የተሰጠው እና በፍርድ ቤት ሙግት ላይ ያለው የ2026 የአፍሪካ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታም እዚህ ውስጥ ይካተታል።
የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን በነሀሴ 2025 በአፍሪካ አገራት ሻምፒዮና (ቻን) ውድድር በኬንያ 1 ለ 0 ከተሸነፈ በኋላ እስካሁን በምንም ጨዋታ አልተረታም።
የትናንቱ ጨዋታ ተጀምሮ 15 ደቂቃ ካለፈ በኋላ ሞሮኮ ካናዳን አሸናፊ የመሆኗ ጉዳይ እየጎላ መጥቷል። ካናዳ ሁለት የግብ ዕድሎችን አግኝታ የነበረ ቢሆንም የሞሮኮ ግብ ጠባቂ አክሽፏቸዋል።
ሞሮኮዎች መረጋጋት ውስጥ ከገቡ በኋላ ግን ጨዋታውን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረውታል። የካናዳው ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ፤ ጄሲ ማርሽ "ትንሽ ዘመም ብለው ነበር፤ ግን አልተሰበሩም" ሲሉ ከጨዋታው በኋላ ተናግረዋል።
የሞሮኮ አሰልጣኝ መሐመድ ዋህቢም በበኩላቸው ከጨዋታው በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "የመጀመሪያው አጋማሽ ፈታኝ ነበር" ብለዋል።
"በእረፍት ሰዓት ላይ መስተካከል የነበረባቸው ጥቂት ነገሮች ነበሩ" ያሉት አሰልጣኙ፤ "ዋናው ነገር ማንነታችንን አልቀየርንም፥ የጨዋታ ፍልስፍናችንንም አልቀየርንም" ሲሉም ተናግረዋል።
እስካሁን ድረስ ሞሮኮ በ2022 እና በዘንድሮው ዓለም ዋንጫ አራት የጥሎ ማለፍ ውድድሮችን አሸንፋለች። ይህ ቁጥር ሌሎች የአፍሪካ አገራት በጥሎ ማለፍ ካሸነፉት ጨዋታ ብዛት ድምር እኩል ነው።
በ2022 የዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ የግማሽ ፍፃሜ በመድረስ ታሪክ ሰርተዋል። አሁን አንድ ተጨማሪ ድል ካስመዘገቡ ያንን ውጤታቸውን ይደግሙታል።
ምንም እንኳ ቡድኑ እስካሁን ድረስ ሙሉ አቅሙን የሚፈትን ውድድር አልገጠመውም የሚል ስሜት ቢኖርም፤ ሞሮኮ የዓለም ዋንጫ ተፎካካሪ መሆኗን መካድ አይቻልም።
በዘንድሮው ዓለም ዋንጫ ከብራዚል ጋር ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ አቻ በመውጣት ተመልካቾችን አስደንቀዋል። ከዚያ በኋላ ደግሞ ስኮትላንድ እና ሄይቲን አሸንፈዋል።
በ32 ቡድኖች ጨዋታ ላይ ከኔዘርላድ የተሻሉ ሆነው ቢገኙም፤ ከመውደቅ የዳኑት ባለቀ ሰዓት ባስቆተሩት ግብ ነው። አሁን ደግሞ ከካናዳ ጋር በነበራቸው ግጥሚያ በምቾች ተጫውተዋል። ምንም እንኳ ሦስት ግብ አስቆጥረው ቢያልፉም በቀጣይ በሩብ ፍጻሜ ከፈረንሳይ ጋር ሊያደርጉ ለሚችሉት ጨዋታ ከወዲሁ ጥርጣሬ የገባቸው ተመልካቾች አሳማኝ ድል አልነበረም።