"ከሞስኮ እንደመጣ" የተገለጸ ግለሰብ በዩክሬን ዋና ከተማ በከፈተው ተኩስ ቢያንስ ስድስት ሰዎች ተገደሉ

የንባብ ጊዜ: 1 ደቂቃ

ቅዳሜ ዕለት ኪዬቭ ውስጥ አንድ ግለሰብ በከፈተው ተኩስ ቢያንስ ስድስት ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች መቁሰላቸውን የዩክሬን ባለስልጣናት ተናገሩ።

ክስተቱ የተፈጸመው በደቡባዊ ሆሎሲቭስኪ አውራጃ ነው። የዩክሬን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኢዮር ክላይንኮ በአካባቢው የሚኖር ሰው መንገድ ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ መተኮስ እንደጀመረ እና በአቅራቢያው በሚገኝ ሱፐርማርኬት በመግባት ሌሎች ሰዎችን ማገቱን ገልጸዋል።

ክላይንኮ ጥቃት አድራሹ በሱፐርማርኬት ውስጥ ከፖሊስ ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ መገደሉን ተናግረዋል። ግለሰቡ ድርጊቱን የፈጸመበት ዓላማ እስካሁን ግልጽ አልሆነም።

የተጎጂዎች ቁጥር በትክክል ባይገለጽም የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ 14 ሰዎች መቁሰላቸውን፤ ከተጎጂዎች መካከል የ12 ዓመት ልጅ እንደሚገኝበት ተናግረዋል፤።

አራት ሰዎች በመንገድ ላይ መገደላቸውን እና የ30 ዓመት ዕድሜ ያላት አንዲት ግለሰብ ሆስፒታል ውስጥ ህይወቷ ማለፉ ተነግሯል። አጥቂው አንድ ታጋችንም መግደሉ ተገልጿል።

የፖሊስ ተደራዳሪዎች ከግለሰቡ ጋር ለ40 ደቂቃዎች ያህል ለመደራደር ሞክረዋል ሲሉ ክላይሜንኮ ተናግረዋል። ግለሰቡ "ባልተረጋጋ መልኩ ሲንቀሳቀስ ነበር" ሲል ገልጸውታል።

"የተጎዳ ሰው እንዳለ በመገንዘብ ልናሳምነው ሞከረናል" ያሉት የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ አጥቂው ምንም አይነት ጥያቄ እንዳላቀረበ አክለዋል።

"ደም መፍሰሱን ለማስቆም የህክምና ቁሳቁስ እና የመሳሰሉትን እንዳቀረብ ጠየቅነው። ነገር ግን ምላሽ አልሰጠም። ከታጋቾቹ አንዱን ከገደለ በኋላ እሱን ለማስወገድ ትዕዛዝ ተሰጠ" ብለዋል።

ከዚያም አራት ታጋቾች መለቀቃቸውን ባለስልጣናት ተናግረዋል።

የዩክሬን ጠቅላይ አቃቤ ህግ ራስላን ክራቭቼንኮ ተኳሹን ከሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮ የመጣ የ58 ዓመት ሰው መሆኑን ገልጸው፤ ግድያውን ለማስፈጸም አውቶማቲክ መሳሪያ እንደተጠቀመ ገልጸዋል።

ባለስልጣናቱ አጥቂው የተጠቀመበት መሳሪያ በይፋ የተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል። ፈቃዱን ከመስጠት ጋር የተያያዙ ሁኔታዎች እንዲሁም ከጥቃት አድራሹ እየተመረመሩ ነው።

ዘሌንስኪ እንደተናገሩት ተኳሹ በምስራቅ ዶኔትስክ ክልል ይኖር ነበር ብለዋል።

ግለሰቡ ጥቃቱን ለመጀመር ከመሄዱ በፊት መኖሪያ አፓርታማውን በእሳት አቃጥሎ ነበር ብለዋል።

ኪየቭ ከሩሲያ ጋር በሚደረገው ጦርነት ወቅት ለብዙ ጥቃት የተጋለጠች ብትሆንም፤ እንዲህ አይነት ጥቃት ግን እምብዛም አልተለመደም።