የካቶሊኩ ሊቀ ጳጳስ የሳንባ ካንሰር ቀዶ ሕክምና ተደረገላቸው

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በሮም በሚገኘው አጎስቲኖ ጀሜሊ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ከቀኝ ሳንባቸው ላይ የተወሰነ እብጠት ለማስወገድ ቀዶ ሕክምና እንደተደረገላቸው ቫቲካን አስታወቀ።

የ71 ዓመቱ ሊቀ ጳጳስ ማክሰኞ ጥቅምት 3/2019 ዓ.ም. በሮም በሚገኘው አጎኦስቲኖ ጀማሊ ሆስፒታል በሳምባቸው ላይ የተገኘውን ካንሰር ለማስወገድ 90 ደቂቃ የፈጀ ቀዶ ሕክምና ተደርጎላቸዋል።

ቫቲካን "ቀዶ ሕክምናው ውጤታማ ነበር። ምንም ዓይነት የተፈጠረ የጎንዮሽ ጉዳት የለም" በማለት አስታውቋል።

"ከቀዶ ህክምናው በኋላ ሊቀ ጳጳሱ በሚገባ የነቁ ሲሆን ለተወሰነ ደቂቃ ክትትል ከተደረገላቸው በኋላ ተኝተው ወደሚያገግሙበት ክፍል ተወስደዋል" ።

ሳምባቸው ላይ ያለው እብጠት ለመጀመርያ ጊዜ የተገኘው "መደበኛ የጤና ምርመራ ሲደረግላቸው" መሆኑን ቫቲካን አስታውቋል።

ሊቀ ጳጳሱ በሆስፒታል ለአንድ ሳምንት ተኝተው ክትትል ይደረግላቸዋል።

ቀደም ብሎ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በሆስፒታል ደጃፍ ሆኖ ሊቀ ጳጳሱን ሲጠብቅ ታይቷል።

ሊቀ ጳጳሱ ደርሰው ወደ ሆስፒታል በገቡበት ወቅት ሰላምታ እየሰጧቸው መልካም ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል።

ሆስፒታል ከደረሱም በኋላ የሕክምና ተቋሙ ባልደረቦች የተቀበሏቸው ሲሆን አንዱ "አዝናለሁ" ካላቸው ቧኀላ "እዚህ ያለነው ለእርስዎ ነው" ሲል አበረታቷቸዋል።

ሊቀ ጳጳሱ ለሕዝቡም ሆነ ለሕክምና ባለሙያዎች በፈገግታ አጸፋውን መልሰዋል።

ቫቲካን በመግለጫው የሊቀ ጳጳሱ ቀኝ ሳንባ ላይ የተገኘው እብጠት በሙሉ እንዲወገድ መደረጉን ገልጿል።

የቫቲካን ምንጮች ለፈረንሳይ ዜና ወኪል (ኤኤፍፒ) እየተስፋፋ ያለ ካንሰር ካለ በሚል ተጨማሪ ምርመራዎች መደረጋቸውን ተናግረዋል።

እሁድ ዕለት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ራሳቸው ናቸው ስለ ቀዶ ህክምናው የተናገሩት።

በዚህ ንግግራቸው ወቅት በሳንባቸው ላይ እያደገ ላለ እብጠት ሕክምና ቢደረግላቸውም "ከመስፋፋቱ በፊት" መገኘቱን እና ዶክተሮቹ መወገድ እንዳለበት እነደነገሯቸው ገልጸዋል።

ምንም እንኳ ሊቀ ጳጳሱ በጥሩ ጤንነት ላይ አንደሚገኙ ቢገለጹም በመላው ዓለም የሚገኙ የእምነቱ ተከታዮች በስጋት ውስጥ ከርመዋል።

"እጨነቃለሁ? አዎ፣ ምክንያቱም እንደዚህ ዓይነት ነገር አልጠበቅኩም ነበር" ሲሉ የቫቲካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካርዲናል ፓሮሊን ማክሰኞ ዕለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

የመታመማቸው ዜና አስደንጋጭ እንደነበር የተናገሩት ሚኒስትሩ ነገር ግን ካርዲናሎቹ በሊቀ ጳጳሱ "መረጋጋት" ተደንቀው በፍጥነት እንደሚያገግሙ እምነት ማሳደራቸውን ተናግረዋል።

በርካታ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳትን ያከመው እና የጆን ፖል ዳግማዊ ትልቅ ሐውልት የሚገኝበት የጄሜሊ ሆስፒታል አካባቢ ሊቀ ጳጳስ ሊዮ ለሕክምና ከገቡ በኋላ ተሰባስበው ታይተዋል።

ካርላ በተለይ ቅርብ መሆን ፈልጋ እንደነበር ትናገራለች።

"የተረጋጉ ይመስላል፣ ስለዚህ እኛም ተረጋግተናል፤ ምንም እንኳን ሕመም ሁልጊዜ ደስ የማይል ቢሆንም" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች። "እዚህ እንጠብቃለን እና እንጸልያለን።"

"ስለ ቀዶ ህክምናው ሲናገሩ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ነበርኩ፣ እናም በጣም አዝኛለሁ" ያለችው ደግሞ ኤልሳነች። "በጣም ደንግጩ ነበር" ካለች በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ሲመረጡ ወጣት እና ጤናማ ጳጳስ እንደሆኑ እንዳሰበች ገልጻለች።

"እርሳቸውም ተጋላጭ እንደሆኑ ታወቀ" ስትል አክላለች።