ትራምፕ የኢራን ጦርነት ወጪን ጨምሮ 87.6 ቢሊዮን ዶላር በምክር ቤት እንዲጸድቅላቸው ጠየቁ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ በአብዛኛው ከኢራን ጦርነት ጋር ለሚያያዝ ወጪ የሚውል 87.6 ቢሊዮን ዶላር በምክር ቤት እንዲጸድቅላቸው ጠየቁ።

"አጣዳፊ" ላሏቸው ከኢራን ጦርነት ጋር የተያያዙ ወጪዎች ገንዘብ እንዲፈቀድላቸው የጠየቁት ያለ ምክር ቤት ፈቃድ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ እንዳይቀጥሉ በተወሰነ በማግሥቱ ነው።

ሪፐብሊካኖች በአብላጫ የያዙት የአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት፤ ትራምፕ የኢራንን ጦርነት እንዲያቆሙ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ አጽድቋል።

ትራምፕ ምክር ቤቱ እንዲያጸድቅላቸው ከጠየቁት ፈንድ መካከል 67 ቢሊዮን ዶላር ለመከላከያ ሚኒስቴር፣ 21 ቢሊዮን ዶላር ለጦር መሣሪያ፣ 17.3 ቢሊዮን ዶላር ለሥራ ማስኬጃ እና 12.1 ቢሊዮን ዶላር ለምሥጢራዊ ክንውኖች መሆኑን ዋይት ሀውስ አስታውቋል።

የተቀረው ገንዘብ ከኢራን ጦርነት ጋር የሚያያዝ አይደለም። 11 ቢሊዮን ዶላር ለአርሶ አደሮች እና 1.4 ቢሊዮን ዶላር በማዕከላዊ አፍሪካ የኢቦላ ስርጭትን ለመቆጣጠር እንደሚውል ተገልጿል።

ትራምፕ ያቀረቡት ጥያቄ በቀላሉ በምክር ቤት ይሁንታ ላያገኝ ይችላል። ሪፐብሊካን እና ዴሞክራት እንደራሴዎችም በኢራን ጦርነት ደስተኛ አለመሆናቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።

በሚቀጥለው ኅዳር የአማካይ ዘመን ምርጫ ከመቃረቡ አንጻርም በጦርነቱ ላይ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ጥያቄዎች ተነስተዋል።

ዋይት ሀውስ ለምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ በላከው ደብዳቤ "አብዛኛው ጥያቄ ከኢፒክ ፊውሪ ኦፕሬሽን ጋር የተያያዙ ወጪዎችን ይመለከታል" ብሏል።

ዋይት ሀውስ ባቀረበው ዝርዝር ውስጥ በመካከለኛው ምሥራቅ እና ደቡብ እስያ የሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎች እና ዲፕሎማቲክ መቀመጫዎች ደኅንነት በተሻለ ሁኔታ ለማስጠበቅ የተመደበው 300 ሚሊዮን ዶላር ይገኝበታል።

ዋሽንግተን እና ቴህራን አሁን በተኩስ አቁም ስምምነት ሥር ቢሆኑም፤ አሜሪካ ካደረሰችው ወታደራዊ ጥቃቶች በኋላ "ግብዓቶቿን መልሳ ማደራጀት" እንዳለባት ፔንታገን ገልጿል።

በሰኔ ወር መባቻ ላይ የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትራምፕ በኢራን ላይ ተጨማሪ ጥቃት እንዳይፈጽሙ የሚያግድ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።

ትናንት ደግሞ ትራምፕ የኢራንን ጦርነት እንዲያቆሙ እና ያለ ምክር ቤት ፈቃድ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ እንዳይቀጥሉ ተወስኗል።

የምክር ቤቱ ውሳኔ ተምሳሌታዊ ሲሆን፤ በሁለቱም ኮንግረሶች ቢጸድቅም እንኳን ለትራምፕ ተልኮ እንደ ሕግ አይተገበርም።

ትራምፕ ግን የውሳኔ ሐሳቡ በመጽደቁ ቁጣቸውን ገልጸዋል። ውሳኔው ከመተላለፉ አስቀድመውም "ጊዜውን ያልጠበቀ እና ትርጉም አልባ" ሲሉም ተችተዋል።

ውሳኔው የጸደቀው በአብላጫ ድምጽ ሲሆን፤ አራት ሪፐብሊካኖች ጦርነቱን በመቃወም ዲሞክራቶችን ተቀላቅለዋል።

ትራምፕ አራቱን ሪፐብሊካኖች "የከሰሩ" በማለት አጣጥለዋል።

"አራቱ ሪፐብሊካኖእ እና ሁሉም ዴሞክራቶች በጦርነቱ መሸነፍ ነው የሚፈልጉት። ደደብ ናቸው" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

ባለፈው ወር የፔንታገን ኃላፊ ለምክር ቤት ባደረጉት ንግግር የጦርነቱ ወጪ ወደ 29 ቢሊዮን ዶላር ገደማ እንደሚደርስ ገልጸዋል።