ከአሜሪካ ጋር ለሚደረገው ንግግር ቁልፍ ሰው እና ቀጣዩ መሪ ይሆናሉ የሚባሉት የኢራን አፈጉባኤ ማን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto via Getty Images
አሜሪካ እና እስራኤል የከፈቱት ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ መሐመድ ባገር ጋሊባፍ የሚጫወቱት ሚና እየጨመረ ነው። ከአሜሪካ ጋር በሚደረገው ንግግር ኢራንን ወክለው እንዲደራደሩ ኃላፊነት እንደተሰጣቸውም ተገልጿል።
አፈ ጉባኤው ጋሊባፍ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺ ከእስራኤል የግድያ ዝርዝር ውስጥ እንደወጡም የዜና ወኪሉ ሮይተርስ የፓኪስታን ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።
ምንጩ "እስራኤሎች ትክክለኛ አድራሻቸው አላቸው፤ ሊገድሏቸውም ፈልገው ነበር። እነርሱ የሚወገዱ ከሆነ ለንግግር የሚቀመተጥ ማንም ሰው እንደሌለ ለአሜሪካ ተናገርን። አሜሪካም እስራኤሎች እንዲተዉት ጠየቀች" ሲሉ ተናግረዋል።
በኢራን እና አሜሪካ መካከል የሚደረገውን ንግግር ከሚያሳልጡ አሸማጋዮች አንዷ ፓኪስታን ነች።
የ64 ዓመቱ አፈ ጉባኤ በኤክስ ገጻቸው፤ ጠላቶች "መሬታችንን የመከላከል ቁርጠኝነታችንን" እንዳይፈትኑ ሲያስጠነቅቁ እንዲሁም "የማያባራ ጥቃት" እንደሚፈጸመው ሲዝቱ ነው የከረሙት።
ይኸም ቢሆን ግን የተወሰኑ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ፖለቲከኛውን ለንግግር የሚያመቹ ሰው አድርገው እንደሚቆጥሯቸው የአሜሪካው የዜና ምንጭ ፖለቲኮ ዘግቧል።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ጋሊባፍ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ለፕሬዝዳንትነት ተወዳድረው አልተሳካላቸውም። ባለፈው አንድ ወር ውስጥ አሜሪካ እና እስራኤል በፈጸሟቸው ጥቃቶች በርካታ ከፍተኛ አመራሮች መገደላቸውን ተከትሎ ግን እየጎሉ መጥተዋል።
የእስላማዊ አብዮታዊው ዘብ አመራሮች ጋር ያላቸው የጠበቀ ግንኙነት፣ በተለያዩ የመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ ያካበተቱት ልምድ እንዲሁም ተማራጅ ወግ አጥባቂነታቸው ወደ አዲስ የሥልጣን ደረጃ ሊያሸጋግራቸው እንደሚችል ይገመታል።
ጋሊባፍ በአብዮቱ ውስጥ
ባለቤትነቱ የኢራን መንግሥታዊ ብሮድካስተር የሆነው አል ዓላም የአረብኛ ቋንቋ የቴሌቪዥን ጣቢያ ዘገባ እንደሚያሳየው፤ ጋሊባፍ ከሃይማኖተኛ እና ሠራተኛ ቤተሰብ የተወለዱት በሰሜን ምሥራቅ ቶርጋቤህ ከተማ ውስጥ ነው።
የትውልድ ከተማቸው የተወሰኑ የእስላማዊ አብዮቱ ስመ ጥር ግለሰቦች ለኖሩበት ማሻድ ከተማ ይቀርባል። 16 ዓመት ሲሆናቸው ማሻድ ውስጥ ወደሚገኙ ዋና ዋና መስኪዶች በመሄድ፤ ኋላ ላይ ጠቅላይ መሪ የሆኑትን አሊ ኻሜኔን ጨምሮ የሌሎችንም አብዮታዊ የሃይማኖት መምህራን ትምህርቶች ተከታትለዋል።
ጋሊባፍ በአውሮፓውኑ 1979 እስላማዊው አብዮት ከፈነዳ ከአጭር ጊዜ በኋላ በኢራቅ ጦርነት ተዋግተዋል። የኢራን አብዮታዊ ዘብን የተቀላቀሉትም በ20 ዓመታቸው ነው።
ከሁለት ዓመት በኋላ የአብዮታዊ ጦሩ አንድ የውጊያ ክፍል አዛዥ ሆነዋል። ጦርነቱ በ1988 እስከሚጠናቀቅ ድረስም በዚህ የኃላፊነት ደረጃ ላይ አገልግለዋል።
ጋሊባፍ ትዳር የመሠረቱት የአብዮታዊ ዘብ አዛዥ በሆኑበት ዓመት ነው። የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱን የመሩት የመጀመሪያው ጠቅላይ መሪ ሩሆላ ኻሜኒ እንደሆኑ የአል ዓላም ዘገባ ያመለክታል። በዚህ ትዳራቸው ሦስት ልጆችን አፍርተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Pacific Press/LightRocket via Getty Images
ከጦርነቱ በኋላም በወታደራዊ ሥልጣን እርከኑ ላይ ከፍ እያሉ መሄዳቸውን አላቆሙም። በአውሮፓውያኑ 1997 የአብዮታው ጦር አየር ኃይል አዛዥ ሆነዋል።
የተራማጆች ጋዜጣ በመዘጋቱ የተቀሰቀሰውን የተማሪዎች ተቃውሞ ሐምሌ 1999 ላይ እስላማዊው ሪፐብሊኩን አናወጠ።
የተቃውሞ እንቅስቃሴው በኃይል እንዲታፈን የተደረገ ሲሆን፣ በተወሰደው እርምጃም በርካታ ሰዎች ተገድለዋል። ጋሊባፍ ራሳቸው በዚህ የአፈና እርምጃ ውስጥ ተሳታፊ እንደነበሩ ይታመናል።
ሾልኮ በወጣ እንድ የድምጽ ቅጂ ላይ ጋሊባፍ "ይሄ 1,000 ሲሲ ያለው ሞተር ሳይክል ላይ ሆኜ እና ዱላ ይዤ የሚያሳይ ፎቶ ነው…ወደ ጎዳና መውጣት እና ዱላ መጠቀም አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሥራውን ከሚያከናውኑት መካከል ነኝ። በዚህም እንኮራለን" ሲሉ ተደምጠዋል።
ከተቃውሞ በኋላ 24 ወታደራዊ አዛዦች የአብዮታዊ ዘቡ ጣልቃ እንደሚገባ የሚዝት በጠንካራ ቃላት የተሞላ ደብዳቤ በወቅቱ የኢራን ፕሬዝዳንት ለነበሩት ተራማጁ መሐመድ ኻታሚ ጽፈው ነበር።
ጋሊባፍ ደብዳቤውን ከጻፉ እና ፊርማ ካሰባሰቡ ሁለት ወታደራዊ አዛዦች አንዱ እንደነበሩ ተናግረዋል።
በርካቶች ይህንን ደብዳቤ የእስላማዊ አብዮታዊ ዘቡ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ያለው ተፅዕኖ በግልጽ የታየበት እንደሆነ ይናገራሉ። ከዚያ ጊዜ በኋላም ተፅዕኖው ጨምሯል።
ከፖሊስ አዛዥነት ወደ ቴህራን ከንቲባነት
የተማሪዎች ተቃውሞ ከተካሄደ አንድ ዓመት በኋላ ጋሊባፍ በ39 ዓመታቸው የፖሊስ አዛዥ ሆነው ተሾሙ።
ለአምስት ዓመታት በቆየው የሥልጣን ዘመናቸው ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ ፖሊስ የስልክ መስመር እንዲከፈት አድርገዋል። በፖሊስ መኮንነኖች ላይ ቅሬታ የሚቀርብበትን አሠራርም ቀልጣፋ አድርገዋል።
የፖሊስ ኃይሉ ከውጭ የገቡ ተሽከርካሪዎችን እንዲታጠቅ ማድረጋቸውንም ከሚኮሩባቸው ስኬቶች መካከል ይጠቅሳሉ። ተቺዎች ግን የወጣው ገንዘብ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ይናገራሉ።
በአውሮፓውያኑ 2005 ጋሊባፍ የፖሊስ አዛዥነት ሥልጣናቸውን ለቅቀው ለኢራን ፕሬዝዳንትነት ተወዳድረዋል።
በምርጫ ከተሸነፉ በኋላ የቴህራን ከንቲባ እንዲሁኑ በከተማ ምክር ቤቱ ተመርጠዋል። በዚህ የሥልጣን ቦታ ለ12 ዓመት የቆዩ ሲሆን፣ የኢራኗን መዲና ለረጅም ጊዜ ከመሩ ከንቲባዎች ቀዳሚው ናቸው።
በከንቲባነት ሥልጣናቸው የከተማዋን የባቡር ሥርዓት በማስፋት እንዲሁም እንደ ሳድር የፍጥነት መንገድ ያሉ የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶችን በመገንባት በከተማዋ ያለውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ለመቅረፍ ላደረጉት ተግባር እውቅና ይቸራቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የጋሊባፍ ዝና እጅጉን የናኘው ግን በአውሮፓውያኑ 2016 "የአስትሮኖሚካል ፕሮፐርቲስ' ቅሌት በወጣበት ወቅት ነው። የቴህራን ከተማ ምክር ቤት በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን በገበያው ዋጋ እስከ 50 በመቶ በቀነሰ ገንዘብ ለባለሥልጣናት እና ለደኅንነት ሰዎች ሸጧል የሚል ክስ ቀርቦበት ነበር።
ጋሊባፍ ከኃላፊነታቸው ከመልቀቃቸው ከወራት በፊት ከኢራን የመጀመሪያዎቹ ረጅም ሕንፃዎች አንዱ የሆነው ባለ 17 ፎቁ ፕላስኮ ሕንፃ የእሳት ቃጠሎ ከደረሰበት በኋላ ፈርሶ ነበር።
በዚህም ቢያንስ 20 የእሳት አደጋ ሠራተኞች ሞተዋል። ይህ አደጋ በጋሊባፍ የመሪነት ዘመን በከተማው መንግሥት ውስጥ የነበረውን ሥር የሰደደ ግድየለሽነትን አሳይቷል።
ይሁን እንጂ የቤቶቹ ሽያጭ ቅሌት ጋሊባፍ ከሥልጣናቸው እንዲባረሩም ሆነ በምክር ቤት እንዲከሰሱ አላደረግም፤ ከሁለቱም የተጠያቂነት እርምጃዎች አምልጠዋል።
ጋሊባፍ በ2020 በተካሄደው ምርጫ የፓርላማ አባል ሆነው የተመረጡ ሲሆን፣ ኋላም አፈ ጉባኤ ለመሆን በቅተዋል።
ያልተሳካላቸው ፕሬዝዳንትነት እና አፈ ጉባኤነት
ጋሊባፍ ሁሌም ቢሆን ዐይናቸው ያሳረፉት አራት ጊዜ ሞክረው ሊያገኙ ባልቻሉት የኢራን ፕሬዝዳንትነት ሥልጣን ላይ ነው። በአውሮፓውያኑ 2005፣ 2013፣ 2017 እና 2024 ምርጫዎች ተወዳድረው ማሸነፍ አልቻሉም።
ከአብዮታዊ ዘቡ ወጥተው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲወዳደሩ ትኩረት የሰጡት ወታደራዊ ልምዳቸው ላይ ነበር። ኋላ ላይ ደግሞ ስልታቸውን ቀይረው በፖለቲካ ጂኦግራፊ የዶክትሬት ዲግሪ መያዛቸውን እና በፓይለትነት መሠልጠናቸውን የብቃት መለኪያ አድርገው አቅርበዋል።
ራሳቸውን "ጂሃዲስት ሥራ አስከያጅ" አድርገው በማቅረብን ወታደራዊ ብቃት እና ትጋት እንዳላቸው አሳይተዋል።
ጋሊባፍ የተራማጆች ተጻራሪ ተደርገው የሚቆጠሩ ቢሆንም፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ከወግ አጥባቂው ቡድን ጋር ልዩነት እንዳላቸው የሚያሳዩ ምልክቶች ተስተውለዋል።
በ2024 በተደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በርካታ አባላት ያሉት የአክራሪዎች ቡድን በዕጩነት መቅረባቸውን ተቃውሟል። ከውድድሩ ራሳቸውን እንዲያገልሉ ለማድረግም ሞክረው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ጋሊባፍ በ2022 እንደገና ከሙስና ቅሌት ጋር በተያያዘ መነጋገሪያ ሆነው ነበር። ቤተሰቦች ወደ ቱርክ ተጉዘው ሲመለሱ አየር ማረፊያ ውስጥ የሕፃን ልጅ ጋሪን ጨምሮ በርካታ የሕፃናት ቁሳ ቁሶችን ይዘው የሚያሳዩ ፎቶግራፎች መውጣታቸው ሰፊ ቁጣ ቀስቅሶ ነበር።
ተቺዎች "በግብዝነት፣ በጭንብል ለባሽነት እና በሐሳዊ ሃይማኖተኝነት" ይወነጅሏቸዋል። ጋሊባፍ ግን የሚቀርቡባቸው ክሶች ፖለቲካዊ ምክንያት ያላቸው እንዲሁም ከኢራን የፖለቲካ መድረክ እንዲወጡ ለማድረግ የሚሰነዘሩ እንደሆኑ ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል።
ስማቸው ከቅሌት ጋር መያያዙ ተጽዕኖ ያሳደረባቸው የማይመስሉት ጋሊባፍ፤ በ2024 በድጋሚ ለፓርላማ አፈ ጉባኤነት ተመርጠዋል። ኢራን ወሳኝ ታሪክ እጥፋት ላይ በቆመችበት በዚህ ጊዜም የፖለቲካ ዕጣ ፈንታቸው ወሳኝ ሰው እያደረጋቸው ይመስላል።
ኢራን ላይ የተከፈተውን ጦርነት የማስቀጠል እንዲሁም በከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች እና በሦስቱ የመንግሥት ቅርንጫፎች መካከል ያለውን ግንኙነት የማሳለጥ አቅማቸው ፖለቲካዊ ሥልጣናቸው ከፍ እንዲል የማድረግ ዕድል ይኖረዋል።















