ትራምፕ ሆርሙዝ እንዲከፈት የጊዜ ገደብ ሲያስቀምጡ ኢራን ደግሞ ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የኢነርጂ ጣቢያዎች ለማጥቃት ዛተች

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥን እንድትከፍት የ48 ሰዓት የጊዜ ገደብ አስቀመጡ። ኢራን በበኩሏ በኃይል ማመንጫዎቿ ላይ ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ በባሕረ ሰላጤው የሚገኙ እና ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የኢነርጂ ጣቢያዎች እንደምታጠቃ አስጠንቅቃለች።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ለዓለማችን የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት ወሳኝ የሆነው የሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ

    የአሜሪካ የኢነርጂ መረጃ አስተዳደር (ኢአይኤ) በ2023 የመጀመሪያ አጋማሽ በቀን 20 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ እንዳለፈ ይገምታል።

    ይህም በዓመት ወደ 600 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የነዳጅ ንግድ በባሕር መስመሩ ላይ ይተላለፋል ማለት ነው።

    በባሕር ወሽመጡ ላይ የሚከሰት ማንኛውም ዓይነት መስተጓጎል በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ መዘግየትን ሊያስከትል ይችላል፤ ይህም ወዲያውኑ በዓለም ዙሪያ የዋጋ ንረት እንዲፈጠር ያደርጋል።

    ይህ ከባሕረ ሰላጤው አገራት በሚገባ የነዳጅ ዘይት ላይ ጥገኛ በሆኑት ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ በሌሎችም አገራት ላይ ከፍተኛ ጫና ሊኖረው ይችላል።

    የሆርሙዝ የባሕር ክፍል በኢራን እና በኦማን መካከል የሚገኝ መተላለፊያ ወሽመጥ ነው። መግቢያው እና መውጫው 50 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፣ በመሃል ላይ ደግሞ በጣም ጠባብ የሆነው ቦታ 40 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው።

    ወሽመጡ በማዕከላዊው ክፍል ብቻ ትላልቅ መርከቦች ለማሳለፍ የሚሆን ጥልቀት አለው።

    የባሕር አሳሾች መግቢያ እና መውጫው ለትልልቅ መርከቦች ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆኑን ያረጋገጡ ሲሆን፣ በመካከልም ክብደት ያለውን ነዳጅ ጭነው ለሚጓዙ ምቹ መሆኑን ይገልጻሉ።

    እነዚህ ግዙፍ መርከቦች ወደ 10 ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው የሰርጡ ክፍል ላይ መቅዘፍ ይኖርባቸዋል።

    ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ሲያልፉ በኢራን እና በአረብ አገራት መካከል አወዛጋቢ በሆኑት የቱንብ ደሴቶች አቅራቢያ ያልፋሉ።

    በወሽመጡ ላይ የሚተላለፉ የንግድ መርከቦችን የሚያስተጓጉሉ ካሉ ወታደራዊ እርምጃ ከግምት እንደሚገባ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

    ይህ ደግሞ በአውሮፓውያኑ 1980 እስከ 1988 ድረስ በተካሄደው የኢራን እና የኢራቅ ጦርነት ወቅት ተከስቷል።

    ዶናልድ ትራምፕ ከሦስት ሳምንት በላይ በዘለቀው የኢራን ጦርነት ምከንያት የተዘጋው ይህ ወሽመጥ እንዲከፈት የ48 ሰዓት የጊዜ ገደብ ሰጥተው ያ የማይሆን ከሆነ ግን የቴህራን የኃይል ማመንጫዎችን ለማውደም ዝተዋል።

  2. በሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲያልፉ የተፈቀደላቸው መርከቦች የትኞቹ ናቸው?

    ኢራን በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የጭነት መርከቦች ላይ በየጊዜው ጥቃት ብትሰነዝርም ከመጋቢት ወር መጀመሪያ ጀምሮ 100 የማይሞሉ መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ አልፈዋል።

    አንዳንድ የነዳጅ እና የዕለት ተዕለት ፍጆታ እቃዎች አሁንም በወሽመጡ እየተጓዙ ቢሆንም፤ የኢራን ጦርነት ከተጀመረበት የካቲት 21 ጀምሮ ዕለታዊው የመርከብ ፍሰት 95 በመቶ ቀንሷል።

    ከጦርነቱ በፊት በየዕለቱ ወደ 138 የሚጠጉ መርከቦች ወሽመጡን አቋርጠው እንደሚያልፉ ዓለም አቀፉ የንግድ መርከሞች መረጃ ማዕከል አስታውቋል። ይህም ከዓለም አቀፍ የነዳጅ አቅርቦት አንድ አምስተኛውን የሚይዝ ነው።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ኢራን ወሽመጡን ሙሉ በሙሉ አንድትከፍት ቢያስጠነቅቁም ኢራን ግን የተዘጋው "ለጠላቶቼ" ብቻ ነው ስትል አቋሟን ግልጽ አድርጋለች።

    ለመሆኑ በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ እንዲያልፉ የተፈቀደላቸው አገራት እነማን ናቸው? በሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲያልፉ የተፈቀደላቸው መርከቦች የትኞቹ ናቸው?

  3. ኢራን የኃይል ማመንጫዎቿ ዒላማ ከሆኑ ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን 'በማይቀለበስ' መልኩ ታወድማለች ሲሉ የፓርላማ አፈ ጉባዔ አስጠነቀቁ

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ መሐመድ ባገር ጋሊባፍ አሜሪካ እና እስራኤል የአገሪቱን የኃይል ማመንጫዎች ካጠቁ በባህረ ሰላጤው አካባቢ ያሉ ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን "በማይቀለበስ መልኩ" እንደሚያወድሙ ዛቱ።

    ጋሊባፍ በኤክስ ገጻቸው ላይ በለጠፉት መልዕክት በቀጠናው ውስጥ የሚገኙ ወሳኝ መሠረተ ልማቶች፣ የኢነርጂ እና የነዳጅ ዘይት ተቋማት እንደ “ሕጋዊ ዒላማዎች” ይቆጠራሉ ብለዋል።

    አፈ ጉባዔው ይንን ያሉት ፕሬዚዳንት ትራምፕ የሰጡትን የ48 ሰዓታት የጊዜ ገደብ ተከትሎ ነው።

    ዶናልድ ትራምፕ ኢራን በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ ነዳጅ ጫን መርከቦች ያለምንም ስጋት መንቀሳቀስ እንዲችሉ በ48 ሰዓት ውስጥ ክፍት ካላደረገች የኃይል ማመንጫዎቿን ለማውደም ዝተዋል።

    ቴህራን በበኩሏ ወሽመጡ "ለጠላቶቼ" እንጂ ለሌሎች ክፍት ነው ስትል ተናግራለች። ቀደም ሲል የኢራን የፓርላማ አባል በባሕር ወሽመጡ የሚያልፉ መርከቦች 2 ሚሊዮን ዶላር እየከፈሉ መሆኑን ተናግረው ነበር።

    ቢቢሲ የፓርላማ አባሉን ንግግር ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።

    አፈ ጉባዔው በመቀጠልም የነዳጅ ዘይት ዋጋ "ለረዥም ጊዜ" እንደሚጨምር አስጠንቅቀዋል።

    የካቲት 21 2018 ዓ.ም አሜሪካ እና እስራኤል በቴህራን ላይ ጦርነት መክፈታቸውን ተከትሎ የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ መተላለፊያ የሆነው ወሽመጥ በመዘጋቱ የነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ ዋጋ አሻቅቧል።

  4. በኳታር ሄሊኮፕተር ተከስክሶ ስድስት ሰዎች መሞታቸውን የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ገለጸ

    በኳታር ባጋጠመ የሄሊኮፕተር አደጋ ስድስት ሰዎች መሞታቸውን የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።

    ሄሊኮፕተሩ እሑድ ዕለት "በመደበኛ ሥራ" ላይ እያለ የቴክኒክ ችግር እንደገጠመው ኳታር ገልጻለች።

    “በተደረገው ፍለጋ በሄሊኮፕተሩ ላይ ከነበሩት ከሰባት ሰዎች ውስጥ የስድስቱን ለማግኘት ተችሏል” ሲል ሚኒስቴሩ በኤክስ ላይ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

    ሚኒስትሩ በኋላ ላይ ባወጣው መግለጫ ከሟቾቹ መካከል ሁለት የቱርክ ሲቪሎችን እና አንድ የቱርክ ወታደር እንዳሉበት ይፋ አድርጓል።

    ኳታር ባለፉት ሳምንታት ውስጥ በኢራን ጥቃቶች የደረሰባት ሲሆን ዋናው የነዳጅ ማመንጫ ጣቢያዋ ደግሞ በያዝነው ሳምንት ውስጥ ተመትቷል። የአሁኑ የሄሊኮፕተር አደጋ ከኢራን ጦርነት ጋር የተያያዘ ስለመሆኑን ግልጽ አልተደረገም።

  5. ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥ እንድትከፍት ትራምፕ ያስቀመጡትን የ48 ሰዓት የጊዜ ገደብ እንዴት ትመልስ ይሆን?

    ኢራን የትራምፕ ማስጠንቀቂያ እንደተሰማ ያለቸው በአሜሪካ ጋር ግንኙነት ያላቸው የኢነርጂ መሠረተ ልማቶች ላይ የአጸፋ ምላሽ እሰጣለሁ ነው።

    ከዚህ በተጨማሪም የሆርሙዝ ወሽመጥ “ከጠላቶች” መርከብ ውጪ ለሌሎች ክፍት መሆኑን ተናግራለች።

    የአገራቸውን ሁኔታ በቅርበት የሚከታተሉ ኢራናውያን ግን ኢራን በባህረ ሰላጤው ላይ በምትፈጽመው ጥቃትም ሆነ ወሽመጡን በመዝጋቷ አልተደነቁም።

    የአገሪቱ መንግሥት ይወድቃል ብሎ ተስፋ የሚያደርግ አንድ ኢራናዊ “ምን ካርድ ቀራቸው አሁን?” ሲል ይጠይቃል።

    ኢራን የባሕር ወሽመጡን ከፈተች ማለት አንድ ያላትን መከላከያ አጣች ማለት ነው።

    ዶናልድ ትራምፕ እንደዛቱት የኃይል ማመንጫዎችን የሚያጠቁ ከሆነ ለኢራን ከፍተኛ ኪሳራ ነው የሚሆነው።

    ነገር ግን ለአስርት ዓመታት የኢራን መንግሥት በምጣኔ ኃብቱ ላይ የሚደርስ ጉዳትን እንዲሁም የሕዝቡን ስቃይ “አብዮታዊ እሴቶችን ለመጠበቅ” በሚል ተቀብሎ እና ተቋቁሞ ሲቀጥል ነው የኖረው።

    ለበርካታ ዓመታት በምዕራባውያን ማዕቀቦች ስር የኖረው የኢራን መንግሥት ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተው የነበሩ ኢራናውያን ላይ ከፍተኛ የኃይል እርምጃ በመውሰድ ዝም ለማሰኘት ጥሯል።

    ከጥር ወር ጀምሮ በነበረ ሕዝባዊ ተቃውሞ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተገድለዋል።

    በዚህ ሳምንት መጀመርያ ላይም የፖሊስ መኮንን ገድለዋል የተባሉ ሦስት ወጣቶች በስቅላት ተገድለዋል።

    ወጣቶቹ በደረሰባቸው ስቅይት የተነሳ ወንጀሉን መፈጸማቸውን አምነዋል ሲሉ የመብት ተሟጋቾች ይናገራሉ።

    የኢራን ባለሥልጣናት የትራምፕን ዛቻ እንደ ተራ ድንፋታ ቆጥረው በባህረ ሰላጤው አገራት ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት ይቀጥሉ ይሆናል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ አገራት መፍትሄ ለመፈለግ እንዳናገሯቸው ተናግረዋል።

    ኦማን ዲፕሎማሲ መፍትሄ ነው በሚል በተደጋጋሚ ትናገራለች።

    ሁኔታዎች በዚሁ ከቀጠሉ የምጣኔ ኃብታቸው በነዳጅ ዘይት እና ቱሪዝም ላይ በተመሠረተው የባህረ ሰላጤው አገራት በርካታ ነገሮች አደጋ ላይ ይወድቃሉ።

    ከእነዚህም መካከል ከደህንነት ጋር ተያይዞ የገነቡት ስም አንዱ ነው።

    ኢራን የአገራቱ ሕይወት ዘይቤ ቀንደኛ ስጋት ሆናለች፤ ጦርነቱ እየቀጠለ ሲሄድ አገራቱ ለዚህ ስጋት የሚሰጡት ምላሽ ወሳኝ ነጥብ ይሆናል።

  6. በኢራን ጥቃት የተጎዱ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን የእስራኤል ባለሥልጣናት ተናገሩ

    በኢራን የሚሳኤል ጥቃት ምክንያት በዲሞና እና በአራድ ከተሞች የተጎዱ ሰዎች ቁጥር ከ160 በላይ መድረሱን የእስራኤል የአደጋ ጊዜ ባለሥልጣናት ተናገሩ።

    ቅዳሜ ምሽት ላይ በባለስስቲክ ሚሳዔሎች በኒውክሌር ተቋም አቅራቢያ በሚገኙት ከተሞች ላይ ከተፈጸመው ጥቃት በኋላ በአራድ 84 በዲሞና ደግሞ 78 ሰዎች ተጎድተው ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

    ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (አይኤኢኤ) ከዲሞና 13 ኪሜ ርቀት ላይ በሚገኘው የኒውክሌር ምርምር ተቋም ጉዳት ስለመድረሱ መረጃ እንደሌለው አሳውቋል።

    ጥቃቶቹ ቅዳሜ ዕለት በኢራን ናታንዝ የኒክሌር ተቋም ላይ ለተፈጸመው ጥቃት የአጸፋ ምላሽ ለመስጠት የተወሰዱ መሆናቸውን የኢራን የመንግሥት ቴሌቪዥን ቀደም ሲል ዘግቧል። አይኤኢኤ “በአካባቢው የጨረር መጠን መጨመር ምልክት የለም" ብሏል።

  7. ኢራን በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦችን 2 ሚሊዮን ዶላር እያስከፈለች ነው - የኢራን የፓርላማ አባል

    የኢራኑ የፓርላማ አባል አላዲን ቦሮጅርዲ ዛሬ በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦች "2 ሚሊዮን ዶላር እየከፈሉ ነው" ብለዋል።

    በባህረ ሰላጤው ውስጥ “አዲስ የአስተዳደር ስርዓት” እየተተገበረ መሆኑን እና “ጦርነት ዋጋ ያስከፍላል” ሲሉ ተናግረዋል። ይህ ደግሞ “የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ያለውን ሥልጣን እና መብት” ያሳያል።

    የዓለም 20 በመቶ የነዳጅ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ መተላለፊያ አሜሪካ እና እስራኤል በአገሪቱ ላይ ጥቃት ከከፈቱበት ጊዜ አንስቶ ተዘግቷል።

    ኢራን ወሽመጡ የተዘጋው 'ለጠላቶቼ" ብቻ ነው ብትልም ምዕራባውያን ግን ከ90 በመቶ የሚሆነው የመርከቦች እንቅስቃሴ መስተጓጎሉን ይፋ አድርገዋል።

    የወሽመጡ መዘጋት ተከትሎም የዓለም ነዳጅ ዘይት ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።

    ቢቢሲ የኢራኑ ፓርላማ አባላት የሰጡትን መረጃ በገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።

    ኢራን በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ በኩል የሚተላለፉ መርከቦች የአገልግሎት ክፍያ እና ታክስ ለአገሪቱ እንዲከፍሉ የሚያስገድድ ሕግ በአገሪቱ ፓርላማ አባላት መነጋገሪያ የሆነው በዚህ ሳምንት ነበር።

    በኢራን ፓርላማ (መጅሊስ) ውስጥ የዋና ከተማዋ ቴህራን ተወካይ የሆኑት ሶማያህ ራፌ የሆርሙዝ ወሽመጥ ደኅንነቱ ተጠብቆ የመርከቦች፣ የነዳጅ እና የምግብ ምርቶች መተላለፊያ እንዲሆን ከተፈለገ ኢራን አስፈላጊውን ጥቅም እንድታገኝ የሚያደርግ ሕግ ላይ እየተሠራ መሆኑን ተናግረው ነበር።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ወሽመጡ በ48 ሰዓት ውስጥ ክፍት እንዲሆን ካለበለዚያ ግን በኢራን የኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ ከባድ ጥቃት ለመፈጸም ዝተዋል።

  8. የባሕረ ሰላጤው አገራት ዛሬ ማለዳም ከኢራን ሚሳዔሎች እና ድሮኖች እየተተኮሰባቸው መሆኑን ተናገሩ

    የባሕረ ሰላጤው አገራት ከኢራን የተከፈተባቸውን ጥቃት ዛሬ ማለዳም በማክሸፍ ተጠምደው ማርፈዳቸውን ተናግረዋል።

    በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ዛሬም የነዋሪዎቻቸውን ሕይወት ስጋት ላይ እንደጣለ ነው።

    ዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ እና ሳዑዲ አረቢያ ዛሬ ማለዳ ከኢራን የተተኮሱባቸውን ሚሳዔሎች ማክሸፋቸውን ተናግረዋል።

    በሳዑዲ አረቢያ ሁለት ሚሳዔሎች “ሰው በማይኖርባቸው አካባቢዎች” መውደቃቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    ዩኤኢ ስለ ጥቃቶቹ በይፋዊ መንገድ ከሚገለፁ ውጭ ምንም ዓይነት መረጃ እንዳይወጣ ጥብቅ ቁጥጥር ታደርጋለች።

    ማንኛውንም ጥቃት ወይንም የደረሰን ጉዳት መቅረጽ ሕገ ወጥ ሲሆን አብዛኛዎቹንም ማክሸፏን የአገሪቱ መንግሥት ተናግሯል።

    ኢራን በኢነርጂ መሠረተ ልማቶች ላይ የምትፈጽመውን ጥቃቶች እንደምትቀጥል ያስጠነቀቀች ሲሆን የአገራቱ መሪዎች ያላቸውን አማራጭ እየተመለከቱ ነው ተብሏል።

    ሳዑዲ አረቢያ ለሚፈጸሙባት ጥቃቶች ወታደራዊ ምላሽ እንደምትሰጥ አስጠንቀቅቃለች። ይህ ግን ከፍተኛ አደጋ የያዘ መሆኑን ቀጣናውን የሚያውቁ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

    ጦርነቱ የበለጠ ሊባባስ እና በምጣኔ ሃብታቸው ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ተናግረዋል።

    ኢራን ለመካከለኛው ምሥራቅ የውሃ ደኅንነት አስፈላጊ የሆኑትን ከውሃ ውስጥ ጨውን የሚያጣሩ ተቋማት ላይ ይቃት ለመሰንዘር ዝታለች።

    የባሕረ ሰላጤው መሪዎች ጦርነቱ የኢነርጂ አቅርቦትን አደጋ ላይ በጣለበት በአሁኑ ወቅት ለዲፕሎማሲ በር አለመዘጋቱን ተናግረዋል።

  9. የኢራን ባለሥልጣን የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ከኢራን "ጠላቶች" በስተቀር ለሁሉም ክፍት ነው አሉ

    በተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ ማሪታይም ድርጅት የኢራን ተወካይ የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ከ"ኢራን ጠላቶች" ጋር ግንኙነቶች ካላቸው መርከቦች በስተቀር ለሁሉም ክፍት ማለታቸውን የኢራኑ ሜህር የዜና ወኪል ዘገበ።

    አሊ ሙሳቪ የተባሉት እኚህ ባለሥልጣን በዚህ ጠባብ የውሃ መስመር በኩል ማለፍ የሚቻለው ከቴህራን ጋር የጸጥታ እና የደህንነት አሰራር ጋር በመተባበር ብቻ ነው።

    "ዲፕሎማሲ ኢራን ቅድሚያ የምትሰጠው ጉዳይ ነው። ሆኖም ግን፣ ሙሉ በሙሉ ጠብ አጫሪነትን ለማስቆም፣ የጋራ እምነት እና መተማመን የበለጠ አስፈላጊ ናቸው" ሲሉ ሙሳቪ ተናግረዋል። እስራኤል እና አሜሪካ በኢራን ላይ የሚሰነዘሩት ጥቃቶች "በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ውስጥ ያለው የአሁኑ ሁኔታ መነሻ" እንደሆነ አክለው ገልጸዋል።

    ከየካቲት 21 2018 ዓ.ም. ጀምሮ አሜሪካ እና እስራኤል ከቴህራን ጋር የሚያደርጉትን ጦርነት ተከትሎ ኢራን በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ላይ በሚያልፉ መርከቦች ላይ ጥቃቶች እየሰነዘረች ነው።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝን ወሽመጥ እንድትከፍት የ48 ሰዓት የጊዜ ገደብ ሰጥተዋል። ይህ የማይሆን ከሆነ ግን በአገሪቱ የኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት እንደሚፈጽሙ ዝተዋል።

  10. በእስራኤል የኒውክሌር ጣቢያ አቅራቢያ ስለደረሰው ጥቃት ምን እናውቃለን?

    ኢራን በቴል አቪቭ የኒውክሌር ጣቢያ አቅራቢያ በፈጸመችው ጥቃት ከሰላሳ ሰዎች በላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል። እስራኤል እስካሁን ድረስ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳላት በይፋ ተናግራ አታውቅም።

    ጥቃቱ ቅዳሜ ዕለት በኢራን ናታንዝ የኒውክሌር ተቋም ላይ ለተፈጸመው ድብደባ ምላሽ እንደሆነ የኢራን የመንግሥት ቴሌቪዥን ዘግቧል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከጥቃቱ በኋላ አገራቸው “ስለ መጻዒው ጊዜ ስንዋጋ ያሳለፍነው አስቸጋሪ ሌሊት” ብለውታል።

    ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (አይኤኢኤ) ከዲሞና ከተማ 13 ኪሜ ርቀት ላይ በሚገኘው የኒውክሌር ምርምር ተቋም ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ መረጃ እንደሌለው ገልጿል።

    የአይኤኢኤ ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮስ "በተለይም በኒውክሌር ተቋማት አቅራቢያ ከፍተኛ ወታደራዊ ጥንቃቄ መደረግ አለበት" ብለዋል።

    በቅርብ ርቀት በምትገኘው አራድ ከተማ በተፈጸመ ሌላ ጥቃት ከ80 በላይ ሰዎች ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጿል። ከእነዚህም ውስጥ 47ቱ ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን 10ቱ ደግሞ አስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ሲል አሳውቋል።

    ለመሆኑ ስለ እስራኤል የኒውክሌር ተቋማት ምን እናውቃለን?

  11. ከሦስት ሳምንት በላይ በዘለቀው ጦርነት በቴህራን የደረሰው ውድመት

    ቅዳሜ ዕለት በቴህራን ሻህራክ-ኢ- ጋርስ አቅራቢያ የተነሳ ምስል እአአ መጋቢት 16 በመኖሪያ እና በንግድ ሕንጻዎች ላይ የተፈጸመ ጥቃትን ተከትሎ የደረሰ ውድመትን ያሳያል።

    የካቲት 21 2018 ዓ.ም. አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ በጋራ ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ዋና ከተማዋ ቴህራን ከባድ የአየር ጥቃቶችን እና ከባድ ውድመትን አስተናግዳለች።

    የእስራኤል ጦር ሌሊቱን የአየር ድብደባዎቸን መፈጸሙን ተናግሯል።

  12. ኢራን በእስራኤል ላይ በፈጸመችው የሚሳዔል ጥቃት ከ100 በላይ ሰዎች ጉዳት እንደረሰባቸው ተገለጸ

    ቅዳሜ ዕለት ኢራን በደቡባዊ እስራኤል በምትገኘው አራድ በፈጸመችው ጥቃት 88 ሰዎች ተጎድተው ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን የአገሪቱ የድንገተኛ ጊዜ አገልግሎት አስታውቋል።

    ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች ውስጥ 10 ሰዎች ከባድ ጉዳት ማስተናገዳቸውን ጨምሮ ገልጿል።

    ከዚህ በተጨማሪም በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል በምትገኝ ሌላ ከተማ ዲሞና ጥቃት ተፈጽሟል። ቴህራን በዲሞና በፈጸመችው ጥቃት ተጨማሪ 30 ሰዎች ጉዳት እንደ ደረሰባቸው የአገሪቱ ድንገተኛ ጊዜ አገልግሎት አስታውቋል።

    ከተማዋ ከእስራኤል የኒውክሌር ተቋም 13 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ናት።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አገራቸው “በጣም አስቸጋሪ ሌሊት” ማሳለፏን ተናግረዋል። ኢራን በእስራኤል የኒውክሌር ተቋም አቅራቢያ ጥቃት ፈጸመች

  13. በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ሌሊቱን ምን ተከናወነ?

    • በመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄደውን ጦርነት ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በ48 ሰዓት ውስጥ የማትከፍት ከሆነ የኃይል ማመንጫዎቿን “እንደሚያወድሙ” ዝተዋል።
    • ኢራን በበኩሏ የኃይል ማመንጫዎቿ ላይ ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ በባሕረ ሠላጤው ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የኢነርጂ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት እፈጽማለሁ ስትል አስጠንቅቃለች።
    • ቅዳሜ ዕለት ትራምፕ ያስቀመጧቸውን የጦርነት ግቦች ማሳካታቸውን እና “ከእቅዳችን በሳምንታት ቀድመናል” ሲሉ ተናግረው ነበር፤ ፕሬዚዳንቱ አክለውም ምንም እንኳ ኢራን ድርድር ብትፈልግም እኛ ግን ፈቃደኞች አይደለንም ብለዋል።
    • በደቡብ እስራኤል በሚገኙት ዲሞና እና አራድ ከተሞች በደረሰ ጥቃት ከ100 በላይ ሰዎች መጎዳታቸው ተዘግቧል። ጥቃቱ ዒላማ ያደረገው ከዲሞና ከተማ 13 ኪሜ ርቀት ላይ የሚገኝ የኒውክሌር ተቋም ነው ተብሏል።
    • ጠቅላይ ሚኒሰስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል የተጸጸመውን ጥቃት ተከትሎ ለእስራኤል “በጣም አስቸጋሪ ምሽት” እንደነበር ተናግረዋል። አክለውም “ጠላቶቻችንን በሁሉም ግንባር ማጥቃታችንን ለመቀጠል ቁርጠኞች ነን” ብለዋል።
    • የእስራኤል ጦር ኢራን ናታንዝ የኒውክሌር ተቋም ላይ ጥቃት ከሰነዘረች በኋላ ሌሊቱን በቴህራን ላይ ተከታታይ ድብደባዎች መፈጸሙን አስታውቋል።
    • ዩናይትድ አረበ ኤሚሬትስ የኢራንን የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶች ማክሸፏን ስታስታውቅ የኳታር መከላከያ ሚኒስቴር ደግሞ “በመደበኛ ስምሪት” ላይ ሳለ የተከሰከሰ ሂሊኮፕተርን ለማግኘት አሰሳ እየተደረገ መሆኑን አስታውቋል።
  14. ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በ48 ሰዓታት ውስጥ የማትከፈት ከሆነ የኃይል ማመንጫዎቿን “እንደሚያወድሙ” ዛቱ

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥን እንድትከፍት የ48 ሰዓት የጊዜ ገደብ አስቀመጡ።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ኢራን በ48 ሰዓታት ውስጥ የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥን ዳግም ክፍት የማታደርግ ከሆነ አገራቸው የኢራን የኃይል ማመንጫዎችን “እንደምታወድም” አስጠንቅቀዋል።

    የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ የሚተላለፍበት ይህ የባሕር መስመር አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱትን ዘመቻ ተከትሎ ተዘግቷል።

    በዚህም የተነሳ ባለፉት ሦስት ሳምንታት የነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ ዋጋ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አሳይተዋል።

    ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ እአአ መጋቢት 21 መልዕክቱን የለጠፉ ሲሆን ኢራን እስከ መጋቢት 23 እኩለ ለሊት ድረስ የጊዜ ገደብ ተሰጥቷታል ማለት ነው።

    ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፋቸው “ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ከዚህ ደቂቃ ጀምሮ በ48 ሰዓታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ የማትከፍት ከሆነ፣ ያለአንዳች ስጋት፣ አሜሪካ የተለያዩ የኃይል ማመንጫዎቿን በመደብደብ ሙሉ በሙሉ ታወድማቸዋለች፤ የምንጀምረው ከትልቁ ይሆናል” ብለዋል።

    ቴህራን ጥቃት የሚፈጸምባት ከሆነ በባሕረ ሰላጤው የሚገኙ እና ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የኢነርጂ ጣቢያዎችን ዒላማ በማድረግ ጥቃት እንድምትፈጽም መናገሯን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

  15. የኢራን ጦርነት፡ ኃያላን ያሻቸውን ማድረግ የሚችሉበት አዲሱ የዓለም ሥርዓት ጅማሬ?

    በዩናይትድ ስቴትስ፣ በእስራኤል እና በኢራን መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት በአዲሱ የዓለም ሥርዓት ውስጥ ከተካሄዱት ዋነኘው ሆኖ ሊታይ ይችላል።

    በዚህ ሥርዓት ውስጥ ለአስርተ ዓመታት የዓለም አቀፍ ባህሪን የሚቆጣጠሩት ሕጎች የነበራቸውን ተጽዕኖ እያጡ ነው።

    ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ ለረዥም ጊዜ፣ ጦርነት እና ዲፕሎማሲ የሚካሄዱት በዓለም አቀፍ ሕግ፣ በተባበሩት መንግሥታት እና በሌሎች ተቋማት በተቀረጹ ማዕቀፎች ውስጥ ነበር።

    እነዚህ ደንቦች እና ስምምነቶች ለሚፈለገው ዓላማ እንዲውሉ ተደርገው ቢተረጎሙም፣ መንግሥታት እንቅስቃሴዎቻቸውን በአጠቃላይ በዚያ ሥርዓት ውስጥ ለማሳየት ይጥሩ ነበር።

    ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች በተለምዶ በሕግ ክርክሮች፣ በዲፕሎማሲያዊ ምክክሮች ወይም በዓለም አቀፍ ጥምረት ምሥረታ የታጀቡ ነበሩ።

    በዚህ ጦርነት ግን እነዚህ ጉዳዮች በጣም ውስን ሚና ብቻ ያላቸው ይመስላሉ።

  16. የኢራን የኒውክሌር ጣቢያ ተመትቷል መባሉን ተከትሎ የተመድ ኒውክሌር ተቆጣጣሪ ተቋም ወታደራዊ እርምጃ እንዲቆም አሳሰበ

    የተባበሩት መንግሥታት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ተቋም፤ ኢራን በናታንዝ ኒውክሌር ተቋም ላይ ዛሬ ጠዋት ጥቃት እንደተፈጸመባት ከገለጸች በኋላ ባውጣው መግለጫ፤ “ማንኛውንም የኒውክሌር አደጋ ስጋት ለማስወገድ” ሲባል የጦርነቱ ተሳታፊ አካላት “ወታደራዊ እርምጃ ከመውስድ እንዲቆጠቡ” አሳሰበ።

    ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኤነርጂ ኤጀንሲ በኤክስ ገጹ ባወጣው መግለጫ፤ የኢራን የኒውክሌር ስፍራ “ዛሬ ጥቃት እንደተፈጸመበት” ከቴህራም መስማቱን ገልጿል።

    “ከጣቢያው ውጭ ያለው የራዲዬሽን መጠን ላይ ምንም ዓይነት መጨመር አልተመዘገበም። ኤጀንሲው መረጃዎችን እያጣራ ነው” ሲል አስፍሯል።

    አክሎም የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ “ማንኛውንም የኒውክሌር አደጋ ለማስወገድ ወታደራዊ ተዐቅቦ እንዲደረግ በድጋሚ ጥሪያቸውን ያቀርባሉ” ብሏል።

    ኢራን ከቁልፍ የኒውክሌር ተቋማቷ አንዱ በሆነው ናታንዝ ላይ ጥቃቶች እንደተፈጸሙበት ያስታወቀችው ዛሬ ቅዳሜ ጠዋት ነው።

    ከመሬት ስር ከሚገኙት የኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች አንዱ የሆነው ይህ ስፍራ ባለፈው ሐምሌ ላይ በአሜሪካ ተደብድቦ ነበር።

    ቴህራን የኒውክሌር ፕሮግራሟ ሙሉ ለሙሉ ለሰላማዊ ጥቅም የሚውል መሆኑን በመግለጽ፤ ኒውክሌር መሳሪያ እየሠራች ነው በሚል የሚቀርብባትን ክስ ውድቅ ታደርጋለች።

    ይሁን እንጂ ኢራን ለሰላማዊ የኒውክሌር ኃይል ከሚያስፈልገው እጅግ በበለጠ መልኩ የጥራት ደረጃው 60 በመቶ የደረሰ ዩራኒየም አበልጽጋለች። የኢራን ዩራኒየም ለጦር መሣሪያነት ለመዋል ለሚያስፈልገው 90 በመቶ የጥራት ደረጃ የቀረበ ነው።

    ጦርነቱ ከመጀመሩ ሁለት ቀናት አስቀድሞ ዋሽንግተን እና ቴህራን ስለ ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም እየተደራደሩ ነበር።

  17. የኢራን ሚሳዔል የተወነጨፈበት የአሜሪካ እና ዩኬ የጦር ሰፈር ምን ያህል ወሳኝ ስፍራ ነው?

    ኢራን 3,800 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የአሜሪካ እና የዩናይትድ ኪንግደም የጋራ የጦር ሰፈር ዲዬጎ ጋርሺያ ላይ ሁለት ሚሳዔሎችን ማስወንጨፏን ቢቢሲ ተረድቷል። ይሁን እንጂ ሁለቱም ሚሳዔሎች የጦር ሰፈሩ ላይ አልደረሱም።

    የዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ ሚኒስትር ሚሳዔሎች ስለመወንጨፋቸው ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ አልሰጠም። ነገር ግን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ፤ በመላው ቀጣናው የሚፈጸሙት የኢራን ግድ የለሽ ጥቃቶች “ለብሪታኒያ ጥቅሞች እና ለብሪታኒያ አጋሮች ስጋት ናቸው” ብሏል።

    አሜሪካ ከዲዬጎ ጋርሺያ የጦር ሰፈር “የመከላከያ የቦንብ ድብደባ” እንድትፈጽም ዩናይትድ ኪንግደም ፈቃድ ሰጥታለች። አሜሪካ እስካሁን የዩኬ ሉዐላዊ ግዛት ከሆነው የጦር ሰፈር ጥቃት ስለመፈጸሟ የወጣ መረጃ የለም።

    በህንድ ውቅያኖስ ላይ ከሚገኙ የቻጎስ ደሴቶች ውስጥ ትልቁ የሆነው ዲዬጎ ጋርሺያ የአሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ጦር ኃይሎች በጋራ የሚጠቀሙበት ነው።

    ዲዬጎ ጋርሺያ ለአብዛኛዎቹ ሲቪሊያን ሰዎች ፈጽሞ ዝግ ሆነ ስፍራ ነው። ከደሴቱ ቅርብ የሆነው የመሬት ክፍል 1,609 ኪሎ ሜትር ይርቃል።

    ዩናይትድ ኪንግደም እና ሞሪሺየስ ለረጅም ጊዜ በዚህ ሩቅ ደሴት ሲወዛገቡ ቆይተዋል። ባለፈው ዓመት ግንቦት ላይ ዩናይትድ ኪንግደም ዲዬጎ ጋርሺያን ለ99 ዓመት በሚቆይ ሊዝ በዓመት 101 ሚሊዮን ፓውንድ እየከፈለች ለመከራየት ተስማምታለች።

    ዩናይትድ ኪንግደም ደሴቱን ለሞሪሺየስ መልሳ በድጋሚ ለመከራየት ማሰቧን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተቃውመው ነበር።

  18. ፕሬዝዳንት ፑቲን ሩሲያ "የኢራን ታማኝ ወዳጅ ሆና ትቀጥላለች" አሉ

    የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የኢራንን አዲስ ዓመት ምክንያት በማድረግ ለአገሪቱ መሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት ሞስኮ የቴህራን ታማኝ ወዳጅ ሆና ትቀጥለላች አሉ።

    የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ክሬምሊን እንዳለው ፑቲን ለጠቅላይ መሪው ሞጅታባ ኻሜኒ እና ለፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ባስተላለፉት የመልካም ምኞት መግለጫ “ኢራናውያን ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ በክብር ያልፉታል” ብለዋል።

    ሩሲያ ከዚህ ቀደም አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱት ጥቃት መላውን መካከለኛው ምሥራቅ ወደ ውድመት አፋፍ በመውሰድ ዓለም አቀፍ የነዳጅ ቀውስ ፈጥሯል ብለው ነበር።

    በተጨማሪም የሩሲያው ፕሬዝዳንት አሜሪካ እና እስራኤል የኢራኑን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒን ለመግደል የወሰዱትን እርምጃ በጽኑ አውግዘዋል።

    ነገር ግን ሩሲያ እየተካደሄ ባለው ጦርነት ውሰጥ ለኢራን እደያረገች ነው በሚባለው ድጋፍ ዙሪያ አተስማማኝ መረጃ የለም።

    አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ግን ሩሲያ ለኢራን የመረጃ ድጋፍ እንደምትሰጥ ዘግበዋል። የአሜሪካው ጋዜጣ ዎል ስትሪት ጆርናል ሩሲያ ለኢራን የሳተላይት ምሥሎችን እና ዘመናዊ የድሮን ቴክኖሎጂ ታጋራለች ብሎ የዘገበውን የፕሬዝዳንቱ ጽፈህት ቤት አስተባብሎታል።

  19. አሜሪካ የኢራንን የኒውክሌር ቁሶች 'ለመቆጣጠር' እያሰበች ነው፤ ዛሬ አንድ ተቋም ተመትቷል

    የትራምፕ አስተዳደር፤ አሜሪካ የኢራን የኒውክሌር ቁሶችን ለመቆጣጠር ወይም ለማስወገድ የምትችበልትን መንገድ እየፈተሸ መሆኑ ሲነገር፤ ዛሬ ጠዋት ደግሞ አንድ የኒውክሌር ተቋም መመታቱን የኢራን መንግሥት አስታወቀ።

    የተለያዩ ምንጮች በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ኒውስ እንደተናገሩት ወሳኞቹን የኢራን የኒውክሌር ተቋማት ቁሶችን ከአገሪቱ እጅ ለማስወጣት ሃሳብ አለ።

    እየተዘጋጁ ያሉት ዕቅዶች “የልዩ ተልዕኮ ዕዝ” የተባለውን ልዩ የጦር ክፍል አባላትን ማሰማራት ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ሁለት ምንጮች ተናግረዋል። ይህ ዕዝ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልጉ ተልዕኮዎችን የሚወጣ የአሜሪካ ሠራዊት ክፍል ነው።

    ሌላ ምንጭ ደግሞ ፕሬዝዳት ዶናልድ ትራምፕ የኒውክሌር ቁሶችን ለመቆጣጠር የሚወሰደውን እርምጃ በተመለከተ በወጣው ዕቅድ ላይ አስካሁን ምንም ዓይነት ውሳኔ እንዳልሰጡ ገልጸዋል።

    በጉዳዩ ላይ አስተያየት የተጠየቁት የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ለሲቢኤስ በሰጡት ምላሽ፤ እንዲህ ያለው ኃላፊነት የሚመለከተው የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴርን (ፔንታገን) ነው ብለዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢራን አውቶሚክ ኤነርጂ ድርጅት በዛሬው ዕለት ናታንዝ የሚገኘው የአገሪቱ የኒውክሌር ተቋም በድጋሚ የጥቃት ዒላማ መሆኑን አስታውቋል።

    ጥቃቱን ተከትሎ የራዲዮአክቲቭ ንጥረ ነገር አፈትልኮ እንደሆነ ግምገማ ተደርጎ በአካባቢው ለሚኖሩ ሰዎች የሚያሰጋ ሁኔታ እንደሌለ መረጋገጡን ድርጅቱ እንዳስታወቀ በኢራን የዜና ምንጮች ላይ የቀረበው መግለጫ ያሳያል።

    የኒውክሌር ተቋሙ ከሁለት ሳምንት በፊት ጥቃት ተፈጽሞበት የነበረ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይም እንዲሁ ከሌሎች የአገሪቱ የኒውክሌርተቋማት ጋር በአሜሪካ ከባድ ቦምቦች ተመትቶ ነበር።

    በወቅቱ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም "ሙሉ ለሙሉ ከጥቅም ውጪ ሆኗል" ብለው ነበር።

  20. "አሜሪካ ጦርነቱን ለማቆም የተዘጋጀች አትመስልም" - የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን ላይ የሚካሄደውን ዘመቻ ለማጠናቀቅ እያሰቡ መሆናቸው መነገሩን ተከትሎ የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሜሪካ ግን ለዚያ የተዘጋጀች አትመስልም አሉ።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ "ይህ ጦርነት በኢራን ላይ የተጫነ" መሆኑን በመጥቀስ ጦርነቱን ሙሉ ለሙሉ የሚያስቆም "የትኛውንም ተነሳሽነት" እንደምትቀበለው ተናግረዋል።

    ሚኒስትሩ ኪዮዶ ለተባለው የጃፓን መገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት ኢራን ጦርነቱን ለማስቆም የሚቀርቡ "ሃሳቦችን ለመስማት እና ለማጤን ዝግጁ ናት" ብለዋል።

    ነገር ግን ምንም እንኳን አንዳንድ አገራት በመካከለኛው ምሥራቅ ለተከሰተው ጦርነት መፍትሄ እየፈለጉ ቢሆንም፤ "አሜሪካ ግን ጠብ ጫሪነቷን ለመተው የተዘጋጀች አትመስምልም" ሲሉ ተናግረዋል።

    አራግቺ ጨምረውም ኢራን የምትፈልገው ተኩስ ማቆም ሳይሆን "የተሟላ፣ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ የጦርነት ማቆም" ስምምነት መሆኑን አሳውቀዋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስሩ ከጃፓኑ መገናኛ ብዙኃን ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ በቴሌግራም አካውንታቸው ላይ የጋሩ ሲሆን፣ ከኢራን መንግሥት የፕሮፓጋንዳ ተቋማ ጋር ግንኙነት ያለው ሜህርስ የዜና ወኪል የቃለ ልምልልሱን የጽሁፍ ግልባጭ አትሞታል።